የአምዓቱ የልማት ግብ ስለጤና | ጤና እና አካባቢ | DW | 08.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የአምዓቱ የልማት ግብ ስለጤና

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2000 ዓ,ም የታቀደዉ የአምዓቱ የልማት ግብ በዋነኝነት በ15ዓመታት ዉስጥ በመላዉ ዓለም ያለዉን ድህነትና ረሃብ በግማሽ ለመቀነስ ያለመ ነዉ። የተመድ እንደሚለዉ የተጀመረዉ ጥረት ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ አብዛኞቹ የታለሙት እቅዶች እስከ መጪዉጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ማብቂያ ድረስ ሊደረስባቸዉ ይችላል።

ከጤና አኳያ በተለይ ደግሞ ለወባ በሽታ፣ TB እና HIV መድሃኒትና ህክምናዉን የማግኘት እድሉ ከተስፋፋ በቀሪዉ ጊዜ የተሻለ ዉጤት ማምጣት ይቻል የሚል ተስፋዉንም ድርጅቱ ገልጿል። እንዲያም ሆኖ ግን ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ ሃገራት በሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ በግጭት መባባስና በዓለም ዓቀፍ ርዳታ መቀነስ ምክንያት እቅዱን በታሰበበት ጊዜ እዉን መደረጉ እንደሚያጠራጥር የድርጅቱ ዘገባ አመልክቷል። እንደዘገባዉ ከሆነም በእነዚህ ሃገራት ነዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1990ዓ,ም 290 ሚሊዮን የነበረዉ በከፋ የድህነት ደረጃ የሚኖሩ ወገኖች ቁጥር በዚሁ የዘመን ቀመር 2010ላይ 414 ሚሊዮን የደረሰዉ። በአንፃሩ ግን በርሃብ የሚሰቃየዉ ሕዝብ 33 በመቶ ወደ 25 በመቶ ቀንሶ መታየቱ ተጠቅሷል። ይህ ቢባልም ግን አሁንም 842 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፍተኛ ርሃብ የተጋለጠ ነዉ። በዚያ ላይ አሁንም የተመጣጠነ የምግብ የማያገኙ ሕፃናት ቁጥር ከ27 ሚሊዮን ወደ32 ሚሊዮን ከፍ ብሎ ታይቷል። የመንግስታቱ ድርጅት የአምዓቱን ግብ የተመለከተዉ ዓመታዊ ዘገባ ከሞላ ጎደል ሲታይ የድህነትና የረሃብ ሁኔታዉ መቀነሱን ቢገልፅም በሃይንሪሽ በል ተቋም የአካባቢ ተፈጥሮና የልማት ጉዳዮች ባለሙያ ባርብራ ዑንሙሲሽ ስኬቱን በተወሰነ አካባቢ ሊታይ እንደሚችል ነዉ ያመለከቱት፤

«በዓለም ደረጃ የተሰጠዉ አማካኝ ቁጥር በአካባቢና በሃገራት ደረጃ ተለይቶ መታየት ይኖርበታል። የተባለዉ ስኬት ቻይናንና ጥቂት የምሥራቅ እስያ ሃገራትን ይመለከት ይሆናል፤ ሆኖም አፍሪቃንና ምሥራቅ አዉሮጳን ስንመለከት ግን የድሃና የድሃ ድሃዉ ቁጥር ከመቀነስ ይልቅ ጨምሯል።»

የአምዓቱ የልማት ግብ ስምንት ነጥቦች ቢዘረዝርም በጥቅል ሲታይ በጤና በትምህርትና ድህነትን በተመለከተ የተሻለ እድል ለሁሉም ኅብረተሰብ ማዳረስን የሚመለከት ነዉ።

በእቅዱ መሠረት የተሻለ ዉጤት ከተመዘገበባቸዉ ዘርፎች አንዱ ጤናን ይመለከታል። በዚህ ረገድ ዘገባዉ እንደሚለዉ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2000 እስከ 2012 ድረስ በወባ ምክንያት ሊጠፋ የሚችል 3,3 ሚሊዮን ሕዝብ ህይወትን መታደግ ተችሏል፤ አብዛኞቹም ሕፃናት ናቸዉ። ይህን መከላከል ያስቻለዉ ደግሞ ከወባ ትንኝ ንክሻ መከላከል የሚያስችለዉ አጎበር መዳረስ ነዉ። በወባ በጣም ከሚጎዱ አካባቢዎች ዋነኛዉ በሆነዉ ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉ ሃገራት ብቻም በያዝነዉና ባለፈዉ ዓመት ብቻ 700 ሚሊዮን አጎበር ተከፋፍሏል። የእናቶችና ሕፃናትን ሞት በመቀነሱ ረገድ የመንግስታቱ ድርጅት ዘገባ የተሻለ ዉጤት መታየቱን አመልክቷል። በኢትዮጵያ የብሔራዊ የጤና ልማት ማዕከል ማለትም / /ሴንተር ፎር ናሽናል ኸልዝ ዴቨሎፕመንት/ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ዶክተር ሃይላይ ደስታ ይህ ዉጤት ኢትዮጵያ ዉስጥም እንደሚታይ ነዉ የገለፁልን። እንዲህ ቢባልም በሌላ በኩል በወሊድ ጊዜ ህይወታቸዉ የሚያልፍ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ የሚደረገዉ ጥረት እንዳለ ሆኖ ቀላል የማይባል ፈተና እንደሆነ አመልክተዋል። ዶክተር ሃይላይ እንደሚሉትም ይህን ሁኔታ ለመቀየር የተደረጉ ጥረቶች በአንዳንድ አካባቢ ፍሬ እያሳዩ ነዉ።

እንደባለሙያዉም የሰለጠነ አዋላጅ በሌለበት ቤት ዉስጥ መገላገሉ እንዲቀር ኅብረተሰቡን በማስተማር፣ ተገቢዉን አገልግሎትና ጥራቱንም በማስተካከል ጥረቱ በየቦታዉ ከቀጠለ የአምዓቱን የልማት ግብ በዚህ ረገድ ማሳካት የማይቻልበት ምክንያት አይኖርም። የተመድ ይፋ ያደረገዉ ዘገባ በመላዉ ዓለም ዛሬም ወደ300,00 ገደማ እናቶች በእርግዝናቸዉ ወራት ወይም በወሊድ ጊዜ ህይወታቸዉ እንደሚያልፍ አመልክቷል። መከላከልና ማዳን በሚቻሉ በሽታዎች ማለት እንደየሳምባ ምች ወይም ተቅማጥ ምክንያት ደግሞ በርካታ ጨቅላ ሕፃናት እንደሚቀጠፉም ጠቅሷል።

ከታቀደለት የጊዜ ገደብ ሊደርስ 17 ወራት የቀረዉን የአምዓቱን የተመድ የልማት ግብ ለማሳካት በተለይ ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሃገራት እንቅፋት የሆነዉ ለዚህ የታሰበዉ የገንዘብ ርዳታ አለመሟላት መሆኑን የድርጅቱ ዘገባ አመልክቷል። በቀሪዉ ጊዜም ይህ ከተሟላ በተለይ የወባ፤ የTB እንዲሁም HIV ቫይረስ በደማቸዉ ለሚገኝ ወገኖች የሚሰጠዉ የህክምና አገልግሎትና መድሃኒት በተገቢዉ መንገድ የሚደርስበት አጋጣሚ እንደሚኖር ይህም የተሻለ ዉጤት ለማየት እንደሚያስችል ነዉ የተገለፀዉ።

MDG Tadschikistan Müttersterblichkeit

የአምዓቱ የልማት ግብ ሲታለም እያንዳንዱ ሀገር ያለዉን አቅም አስተባብሮ ከዉጭም የለጋሾችን ድጋፍ ይዞ ለመሥራት መታለሙን ያስታወሱት ዶክተር ሃይላይ ከታለመዉ ግብ ለመድረስ ለጋሾችም ሆኑ እያንዳንዱ መንግስት ቃላቸዉን ጠብቀዉ መሥራት እንሚኖርባቸዉ ሳይጠቅሱ አላለፉም። በዚህ ባለዉ አቅምም በተለያዩ ሃገራት ዉጤት መታየቱንም ዶክተር ሃይላይ ደስታ የብሔራዊ ጤና ልማት ማዕከል የኢትዮጵያ አስተባባሪ አብራርተዋል።

የተመድ ከጤና ጋ ከተያያዙ መሠረታዊ ነገሮች ማለትም የመጸዳጃ ቤትና የንፅህና መጠበቂያ ስልቶችን ከማግኘት አኳያ በተሠሩ ሥራዎችን አሁንም የረካ አይመስልም እንደዘገባዉ። እንደዘገባዉ ከዓለም ጠቅላላዉ ሕዝብ 64 በመቶ የሚሆነዉ ብቻ ነዉ መፀዳጃ ቤት የማግኘት እድሉ ያለዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic