የአምነስቲ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ዘገባ | ዓለም | DW | 24.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአምነስቲ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ዘገባ

ድርጅቱ በዘገባው እንዳጠቆመው በ2015 በዓለማችን የደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከእስከ ዛሬው የከፋ ነው ። በዓመቱ ኢትዮጵያና ኤርትራን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪቃ አገራት በዜጎች ላይ የሚካሄድ አፈና ተጠናክሮ ቀጥሏል ሲል አምነስቲ ዘግቧል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:57
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:57 ደቂቃ

የአምነስቲ ዘገባ

በዘንድሮው የአምነስቲ ዘገባ ከዚህ ቀደም ለሰብዓዊ መብት በመቆም ቀዳሚ ቦታ የሚሰጠው የአውሮጳ ኅብረት የስደተኞችን መብት ባለማስጠበቅ ተወቅሷል ።
«የትምህርት ቦታ ያለአንዳች ማስጠንቀቂያ በዚህ አይነት መንገድ ሲመታ ሰብዓዊነት እንዳበቃለት ነው የሚሰማኝ »
አንዲት የመናዊት በቦምብ ተመቶ ወደ ፈራረሰ አንድ ትምህርት ቤት እያመለከተች የሰጠችው አስተያየት ነው። ዛሬ የወጣው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዓመታዊ ዘገባ። ከየመን ሌላ በሶሪያ በሊብያ እና በሌሎችም የመካከለኛ ምሥራቅ ሃገራት በጎርጎሮሳዊው 2015 ተመሳሳይ ጥፋቶች መድረሳቸውን ያስታውሳል። በነዚህ ሃገራት በታጠቁ ኃይሎች መካከል በሚካሄድ ግጭት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ። ይህም በዓለም ዙሪያ የስደተኞች ን ቀውስ ማባባሱን ድርጅቱ አስታውቋል ።የድርጅቱ ዋና ፀሃፊ ሳሊል ሼቲ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ 2015 ከሌሎቹ ዓመታት በባሰ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ የሰብአዊ መብት ጥሰት የታየበት ዓመት መሆኑን ተናግረዋል ።
«2015 ምናልባትም በዚህ ረገድ ከባድ ችግሮች የታዩበት ዓመት ሊባል ይችላል ።ሰብዓዊ መብትን ለማስጠበቅ የተዘረጋውና ባለፉት 70 ዓመታት እንዲጠናከር የተደረገው ስርዓት ራሱ አደጋ ላይ ነው »
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈፀም ያልተነሳ አካባቢ የለም ። ዘገባው በላቲን አሜሪካ እና በእስያ

München Sicherheitskonferenz - Salil Shetty, Amnesty International

ሳሊል ሼቲ

በመብት ተሟጋቾች ላይ ግድያና አፈና ጨምሮ ሌሎችም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈፀሙ አትቷል። ሚሊዮኖችን ባፈናቀሉት በአፍሪቃና በመካከለኛው ምሥራቅ በሚካሄዱ የርስ በርስ ጦርነቶችና ግጭቶች እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ የሚፈፀሙ ግድያዎችም ተጠቅሰዋል። ሃላፊው ዜጎቻቸውን በመጫን ከጠቀሱዋቸው የአፍሪቃ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያና ኤርትራ ይገኙበታል ።
«በርካታ የአፍሪቃ መንግሥታት ከኢትዮጵያ እስከ ኤርትራ ከጋምቢያ እስከ አንጎላ ህዝቦቻቸውን ማፈኑን አጠናክረው ቀጥለዋል ። በሲቪል ማህበራት በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በጋዜጠኞች ና ብሎገሮች ላይ ቁጥጥራቸውን አጥብቀዋል ።ለዚህም ብዙውን ጊዜ እንደ ምክንያት የሚያነሱት ስርዓትና ደንብ ማስከበርንና ፀረ ሽብር እርምጃን ነው ።»
የአምነስቲ ሃላፊ ሼቲ እንዳሉት 2015 መንግሥታት የፀረ ሽብር ህግን የመሳሰሉ ደንቦችን ሽፋን አድርገው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት መጣሳቸው ተጠናክሮ የቀጠለበት ዓመት ነበር። እንደ ሼቲ መንግሥታት የሚሉትና የሚወስዱት ርምጃ ደግሞ ርስ በርሱ የሚቃረን ነው ።
«በአንድ በኩል መንግሥታት ይበልጥ ጨቋኝ የሚጫኑ ሆነዋል ። የጅምላ ክትትልና አፈና ለማካሄዳቸው መከራከሪያ የሚያደርጉት ፀረ ሽብር እርምጃን ነው ። በዚህ መካከልም ሰብዓዊ መብት ይጥሳሉ ። በሌላ በኩል ደግሞ እርምጃውን የሚወስዱት ህዝቡ ለመብቱ ሲቆም ነው።»
ከዚህ ሌላ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን የተፈጠረውን የስደተኞች ቀውስ አስከፊ በማለት ይገልፀዋል ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በርካታ ስደተኞች ከአንዱ ሃገር ወደ ሌላው እየተሰደዱ ነው።

Amnesty International PK zur Lage der Menschenrechte 2015/2016 Selmin Çaliskan

ሴልሚን ሴሊስካን

አብዛኛዎቹም ከሶሪያው ጦርነት የሚሸሹ ናቸው። ምንም እንኳን በዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌና በጄኔቫው የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት መሠረት የእነዚህ ስደተኞች መብት መከበር ያለበት ቢሆንም አብዛኛዎቹ ግን ለተለያዩ አደጋዎች መጋለጣቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዘገባው አንስቷል። ሰብዓዊ መብትን በማስጠበቅና ለሰብዓዊ መብት በመቆም ብዙውን ጊዜ ቀዳሚው ቦታ የሚሰጠው የአውሮጳ ኅብረት በዘንድሮው የአምነስቲ ዘገባ የስደተኞችን መብት ባለማስጠበቅ ተወቅሷል። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጀርመን ቅርንጫፍ ሃላፊ ሴልሚን ሳሊስካን ።
«የአውሮጳ ኅብረት አሁንም ራሱን እያገለለ ነው። ድንበሮቹን መዝጋቱን በማጠናከር ስደተኞች ወደ አውሮጳ እንዳይመጡ የመከላከል ሙከራውን ይቀጥላል። ይህ እንደማይሰራ ሁላችንም እናውቃለን። ሆኖም አሁን ለስደተኞች ደህንነቱ አስተማማኝ እንዲሁም ህጋዊ መንገድ ከማመቻቸት እንዲሁም ስደተኞች ጥለዋቸው ከመጡት ከሊባኖስና ከዮርዳኖስ ወይም ቱርክን ከመሳሰሉት ሃገራት የተሻለ ሰብዓዊ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ ትኩረቱ ድንበር መዝጋቱ ላይ ሆኗል ።»
ሳሊስካን በአሁኑ ጊዜ ሰብዓዊነት ወደ ጎን እየተገፋ ዓለም ትክክል ነው ብሎ የሚከተለው ሌላ መንገድ አደገኛ መሆኑን አስጠንቅቀዋል። በርሳቸው አስተያየት ብልፅግናም ሆነ ደህንነት እውን ሊሆን የሚችለው ሰብዓዊ መብቶች ከተጠበቁ ብቻ ነው ።

ሒሩት መለሠ

አዜብ ታደሠ

Audios and videos on the topic