የአምባሳደር ዘውዴ ረታ ዜና እረፍት | ኢትዮጵያ | DW | 08.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የአምባሳደር ዘውዴ ረታ ዜና እረፍት

በቀዳሚዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በጋዜጠኝነትና በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አምባሳደር ዘውዴ ረታ በታላቋ ብሪታኒያ ዋና ከተማ ለንደን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። አምባሳደር ዘዉዴ በአዲሱ ትውልድ ዘንድም በታሪክ ፀሐፊነታቸውና ተመራማሪነታቸውም ይታወቃሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:04

የአምባሳደር ዘውዴ ረታ አጭር የህይወት ታሪክ


በአፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግሥት ‘ሥጋ ቤት ሠፈር‘ ተብሎ በሚጠራውና በአሁኑ ስሙ ‘ኦርማ ጋራዥ‘ በሚባለው አካባቢ ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም. ነበር የተወለዱት። ቀድሞው ደጃዝማች ገብረ ማርያም የአርበኞች ትምህርት ይባል የነበረው የአሁኑ ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ተማሪ ናቸው። ዛሬ ለንደን ላይ ከዚህ ዓለም በሞት መለያታቸው የተሰማው አምባሳደር ዘውዴ ረታ።
አምሳደር ዘውዴ ሥራ የጀመሩት በዘመኑ የጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት ተብሎ ይጠራ በነበረው ተቋም በጋዜጠኝነት ነበር። በጋዜጠኝነት ህይወታቸው የቤተ-መንግስት ዘጋቢ ሆነው ሠርተዋል። ወደ ፈረንሳይ ተጉዘው በጋዜጠኝነት ትምህርት ዲፕሎማም አግኝተዋል። የዕለታዊው የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣና የወርሃዊው መነን መጽሔት ዳይሬክተርም ነበሩ። የብሄራዊ ሬዲዮ የአማርኛ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር በመሆንም ሠርተዋል። የያኔውን የዜና አገልግሎት አቋቁመው በዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል።
ጋዜጠኛው ወደ ዲፕሎማሲ የሥራ መስክ ተሻግረው በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሚኒስትር ካውንስለር፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ም/ሚኒስትር፤ በሮም እና በቱኒዚያ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አምባሳደር ሆነው ሠርተዋል።
ከ 22ዓመታት አገልግሎት በኋላ የቀዳሚዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት በአዲስ ስርዓተ መንግስት ሲተካ ሥራቸውን ለመልቀቅ የተገደዱት አምባሳደር ዘውዴ ረታ እስከ ጡረታ ዘመናቸው ድረስ በዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ መሥሪያ ቤት የመንግሥታት ግንኙነትና የፖለቲካ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
በታሪክ ተመራማሪነታቸውና ፀሐፊነታቸው ሶስት መጻህፍትን ለአንባብያን አድርሰው ለአራተኛው በዝግጅት ላይ ነበሩ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሳታሚ (Addis Ababa University Press ) አርታዒው ብርሃኑ ደቦጭ «ተገቢውን ምንጭ በመጠቀም ህዝባዊ ታሪክ የሚጽፉ ባለሙያ» ሲሉ ይገልጿቸዋል። አቶ ብርሃኑ በቀዳሚነት ለህትመት የበቃው «የኤርትራ ጉዳይ» የተሰኘው የአምባሳደር ዘውዴ ረታ መጽሐፍ በኢትዮጵያና ኤርትራ የፖለቲካ ሐቲት ጉልህ ጠቀሜታ ካላቸው አንዱ መሆኑን ይናገራሉ።
አምባሳደር ዘውዴ ረታ የተፈሪ መኮንን ረጅሙ የሥልጣን ጉዞ እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ታሪክ የተሰኙ ሁለት ዳጎስ ያሉ መጻህፍትንም አሳትመዋል። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ የሚያተኩረውና አራተኛው መጽሐፋቸው የመረጃ ማሰባሰብ ሂደት ተጠናቆ ለህትመት በማዘጋጀት ላይ ነበሩ ተብሏል። አምባሳደር ዘውዴ ረታ ከፊውዳላዊው ስርዓት እና ከቤተ-መንግስቱ ጋር በነበራቸው ቤተሰባዊ እና የሙያ ቅርበት ታሪክን ከፍ ባለ ደረጃ ለመጻፍ የሚያስችል ምንጭ ማግኘት እንዳስቻላቸው የታሪክ ባለሙያው አቶ ብርሐኑ ደቦጭ ተናግረዋል።
አምባሳደር ዘውዴ ረታ በ1959 ዓ.ም ከባለቤታቸው ወ/ሮ ገሊላ ተፈራ ጋር ትዳር መስርተው ሦስት ልጆችንም ማፍራታቸውን በመጽሃፋቸው ጀርባ ያሰፈሩት የሕይወት ታሪካቸው ያወሳል። ለበርካታ ዓመታት በስደት የኖሩት አምባሳደር ዘውዴ ረታ ከጥቂት አመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በታሪክ ምርምር ሥራቸው ላይ ትኩረት አድርገው ነበር። አቶ ብርሀኑ ደቦጭ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አምባሳደር ዘውዴ ረታ በሥራዎቻቸው ወደ ፊትም ምሳሌ የሚሆኑ ሲሉ ይገልጿቸዋል።


እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic