የአምስት ሚኒስትሮች ሹመት በአብላጫ ድምጽ ፀደቀ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 19 2017
በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት የቀድሞው የፍትሕ ሚኒስትር ጌድዬን ጢሞትዮስ ሹመት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገቢነት ጥያቄ አስነሳ።
ሹመታቸው ዛሬ ከፀደቀው አምስት ሚኒስትሮች መካከል አንዱ የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላይ አንድም ከልምድ አንፃር በሌላ በኩል የፍትሕ ሥርዓቱ የፖለቲካ መሣሪያ እንዲሆን አድርገዋል በሚል ነው ቅሬታ የቀረበባቸው።
በዛሬው መደበኛ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባኤ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የቦርድ አባል መሆን አይችሉም የሚለውን ድንጋጌ የሚያሻሽል ረቂቅ የቀረበ ሲሆን መሻሻያው የዘርፉን ገለልተኝነት የሚጋፋ ነው በሚል ጥያቄ ተነስቶበታል።//
ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው የፀደቀው ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የፍትሕ፣ የውጭ ጉዳይ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር፣ የቱሪዝም እና የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የሚመሩ ናቸው። ሹመቱ ተሰጥቶ ባለስልጣናቱ ሥራ ላይ ከቆዩ በኋላ ምክር ቤቱ ወደ ማጽደቅ የተኬደበት አሠራር ለምን የሚል ጥያቄ ቀርቦበታል።
በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ለዚህ በሰጡት ምላሽ በአንድ በኩል የምክር ቤቱ አባላት በስልጠና ላይ ስለነበሩ እንዲሁም አጣዳፊ ሥራ ስለነበር ቦታዎቹ ክፍት ሆነው መቆየት ስለሌለባቸው ነው ብለዋል።አንድ የምክር ቤት አባል ግን ይህንን አልተቀበሉትም።
"የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት የነበሩት ነገር ግን ከቦታ ቦታ ሲቀያየሩ ሹመታቸው እዚህ የማይፀድቅበት ምክንያት ምንድን ነው"?
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የጠየቅናቸው የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ ኃይለ ገብርኤል ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
"አንዳንድ ሕጎች በረቂቅ ደረጃ ሆነው ብዙ ሊቆዩ ይችላሉ፤ ፓርላማው እስከሚያፀድቃቸው። ልክ እንደዚያው ይሄ ሹመት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰጥቶ በፓርላማው ሳይፀድቅ ሊቆይ ይችላል"
የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት ችግር የሚሆነው ተሿሚዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጣቸው ደብዳቤ ብቻ እንደራሴው ምክር ቤት ሥልጣኑን ሳያፀድቀው ሥራ የጀመሩ እንደሆን ነው።
"ይህ ሹመት በፓርላማ ሳይፀድቅ እነዚህ ሰዎች እዚያ የተመደቡበት ቦታ ላይ ሄደው ያንን ተቋም መወከል ወይም ደግሞ በዚያ ተቋም መሠረት ሥራ መሥራት፣ ውሳኔ መስጠት እሱ ሕጋዊ ነው ብሎ ለማለት ያስቸግራል"
በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ጌድዮን ጢሞትዮስ ላይ የፍትሕ ዘርፉን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱ፣ የፖለቲካ መሣሪያም እንዲሆን ያደረጉ ናቸው በሚል ተቃውሞ ቀርቦባቸዋል።
"የፍትሕ ዘርፉን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱ ስለሆነ ለዚያ ስልጣን ብቁ አይደሉም፣ መቅረብ የለባቸውም"
በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ በሰጡት ምላሽ ግን ተሿሚው ውጤታማ አመራር መሆናቸው በመንግሥትም፣ በብልጽግና ፓርቲም ተገምግሞ የቀረቡ ናቸው።
"ዶክተር ጌድዮን ጠንካራ፣ ብቃት ያላቸው አመራር ናቸው"።
በዛሬው የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤየከተማ መሬትን የተመለከቱ ሁለት ረቂቅ አዋጆች ቀርበው ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርተዋል። የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባል እንዳይሆን ይከለክል የነበረው የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅም የቀረበ ሲሆን፣ ይህ የመገናኛ ብዙኃንን ገለልተኝነት የሚጋፋ እና ዘርፉ በተወሰኑ የፓርቲ አባላት እንዲሞላ የሚያደርግ ነው በሚል ተቃውሞ ቀርቦበታል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር