የአሜሪካ ፖለቲከኞች የምርጫ ዘመቻ | ዓለም | DW | 27.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የአሜሪካ ፖለቲከኞች የምርጫ ዘመቻ

አሜሪካ የተገራ ፖለቲካዊ ባሕል፤ለጋራ እስት የሚገዛ ማሕበረሰብ፤ ወጥ ስነልቡናዊ አስተሳሰብ አላት-የላትም ሐሳብ ብዙ ያከራክር ይሆናል።ሁለት ነገር ግን እዉነት ነዉ።የዴሞክራሲ ሐገር ናት።የዶላርም። እሳቸዉ ሁለተኛዉ ሞልቶ ተርፏቸዋል።4,5 ቢሊዮን ዶላር።የመጀመሪያዉንም በሁለተኛዉ ከመግዛት እኩል ሊቆጣጠሩት እየተፎካከሩ ነዉ።ዶናልድ ትራምፕ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:21

የአሜሪካ ፖለቲከኞች የምርጫ ዘመቻ

ሕዳር 1999 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የያኔዉ የቴክሳስ አገረ-ገዢ ጆርጅ ዳብሊዉ ቡሽ ለፕሬዝደንትነት ሲወዳደሩ የአራት ሐገራት መሪዎችን ማንነት እንዲጠሩ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ የሰጡት መልስ የዓለም መሪይቱ ሐገር የወደፊት መሪ ሥለዓለም ፖለቲካ የነበራቸዉን ዕዉቀት መስካሪ፤ከተመረጡ የዉጪ መርሐቻዉን መሠረት ጠቋሚ፤ምናልባት ለብዙዎች አስቂኝ ብጤም ነበር።ግን ተመረጡ።ካንዴም ሁሌቴ።በአስራ- ሰባተኛ ዓመቱ ዘንድሮ የቡሽን ፓርቲ ወክለዉ እንደ ቡሽ ለፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩት ዶናልድ ትራምፕ ብሪታንያ ከአዉሮጳ ሕብረት አባልነት ለመዉጣት መወሰኗን «እፁብ ድንቅ» አሉት።ትራምፕ ሥለ ብራስልስ መሸበር፤ ሥለ ኦርላንዶ ግድያ፤ሥለ ዘር ሐይማኖት የሚሉ፤ቃል የሚገቡት ብዙዎችን ያስቅ፤ ያሰቀቅም፤ ይሆናል።ከተቀናቃኛቸዉ ከሒላሪ ክሊንተን ጠንካራ አፀፋ ገጥሟቸዋልም።አይመረጡም ማለት ግን አይቻልም።የአሜሪካ ፖለቲከኞች የምርጫ ፉክክር መነሻ፤የዉጪ መርሐቸዉ መሠረት መድረሻችን ነዉ።

ዩናይትድ ስቴትስ መስከረም 2001 በአሸባሪዎች ከተጠቃች ወዲሕ በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዉ በሰዉ እጅ ሲገደልባት ከሁለት ሳምንት በፊት ኦርላንዶ-ፍሎሪዳ የተፈፀመዉ ግድያ የመጀመሪያዉ ነዉ።ዑመር ማቴን የተባለዉ አፍቃኒስታናዊ-አሜሪካዊ ወጣት ግብረ-ሰዶማዉያን በሚያዘወትሩት የምሽት ዳንስ ቤት ዉስጥ በከፈተዉ ተኩስ 49ኝ ሰዎችን ገድሎ-እራሱም ተገድሏል።

በግድያዉ ያልደነገጠ፤ ሐዘኑን ያልገለፀ፤ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ያልተመኘ የዓለም ፖለቲከኛ የለም።ለአሜሪካኖች ደግሞ ከሐዘን-ድንጋጤዉ በተጨማሪ የገዳዩን ዓላማ ለማወቅ የሚመረምሩበት፤ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ እንዳሉት ተመሳሳይ ግድያ እንዳይፈፀም መዉሰድ የሚገባቸዉን እርምጃ የሚያወጡ የሚያወርዱበት ወቅት ነዉ።

«ዛሬ በአሜሪካ ታሪክ በርካታ ሰዉ የተገደለበት ዕለት ነዉ።ገዳዩ ቀላል መሳሪያ እና የዉጊያ ጠመንጃ የታጠቀ ነበር ተብሎ ይታመናል።ይሕ ጭፍጨፋ፤ ሰዉ መግደል የሚፈልጉ ሰዎች ትምሕርት ቤት ዉስጥ፤ቤተ-እምነቶች ዉስጥ፤ ፊልም ቤቶች ዉስጥ የሚገኙ ሰዎችን መግደል ሲፈልጉ በቀላሉ ጠመንጃ እንደሚያገኙ ዳግም

ያስታዉሰናል።የምንፈልጋት የዚሕ አይነት ሐገር መሆን-አለ-መሆንዋን መወሰን አለብን።ምንም አለማድረግም በራሱ ዉሳኔ ነዉ።»

በመጪዉ ሕዳር ለሚደረገዉ ፕሬዝደነታዊ ምርጫ የዴሞክራቲኩን ፓርቲ ወክለዉ ይወዳደራሉ ተብለዉ የሚጠበቁት የቀድሞዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን የግድያዉን ዜና እንደሰሙ ዕለቱ የፖለቲካ አይደለም አሉ።የሐዘን እንጂ።«ዛሬ የፖለቲካ ቀን አይደለም።የኦርላንዶዉ አሸባሪ ሞቶ ይሆናል፤አዕሞሮዉን የመረዘዉ ተሕዋሲ ግን እንዳለ ነዉ።ሐገራችን ዉስጥና እሴቶቻችን መሐል በግልፅ አይን፤ በፅኑዕ እጅ እና በማያሻማ ዉሳኔ ልንዋጋዉ ይገባል።(ብመረጥ) እንደፕሬዝደንት የግድያ ምክንያቶችን መለየትና ማስቆምን ከፍተኛ ቅድሚያ እሰጠዋለሁ።ሕግ አስከባሪና የሥልላ ባለሙያዎቻችን ሥራዉን እንዲሰሩ የሚያስፈልጋቸዉን ነገር እንዲያገኙ አደርጋለሁ።የፀጥታ ሐይሎቻችን ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስፈልጋቸዉን መሳሪያ እንዲያገኙ ከማድረጋችን ጋር፤ አሸባሪዎች ጥቃት ለማድረስ የሚጠቀሙበትን መሳሪያ እንዳያገኙ ማድረግም አስፈላጊ ነዉ።በተለይ ኦርላንዶ እና ሳን በርነዲኖ ጥቃት የተፈፀመባቸዉ አይነት የዉጊያ መሳሪያን ማግኘት የለባቸዉም።»

ወይዘሮ ክሊንተን ዕለቱ የፖለቲካ አይደለም ይበሉ እንጂ ከፖለቲካ ዉጪ በርግጥ ሌላ አላሉም።አሁን ቃል የገቡትን የፕሬዝደንትነት ሥልጣን ሲይዙ (ከያዙ) ለማድረጋቸዉ ጊዜ ጠብቆ ከማየት ሌላ ማረጋገጥ አይቻልም።ከአሜሪካ የፖለቲካ ሥርዓት የወጣ ነገር ግን አላሉም።የአሜሪካኖችን ወይም በአሜሪካኖች በኩል የዓለም የሆነዉን ፖለቲካዊ ይትበሐል መጠበቃቸዉ ከዚሕ ቀደም ሞከረዉ ያጡትን የፕሬዝደትነት ስልጣን ለመያዛቸዉ ዋስትናም አይደለም።

አሜሪካ የተገራ ፖለቲካዊ ባሕል፤ ለጋራ እስት የሚገዛ ማሕበረሰብ፤ ወጥ ስነልቡናዊ አስተሳሰብ አላት-የላትም ሐሳብ ብዙ ያከራክር ያወዛግብም ይሆናል።ሁለት ነገር ግን እዉነት ነዉ።የዴሞክራሲ ሐገር ናት።የዶላርም። እሳቸዉ ሁለተኛዉ ሞልቶ ተርፏቸዋል።4,5 ቢሊዮን ዶላር።የመጀመሪያዉንም በሁለተኛዉ ከመግዛት እኩል ሊቆጣጠሩት እየተፎካከሩ ነዉ።ዶናልድ ትራምፕ።

የኦርላንዶዉን ግድያ እንደሰሙም እንዲሕ አሉ «ገዳዩን እኮ ግንባሩን የሚለዉ ቢገኝ ኖሩ----»«ከተቃራኒዉ አቅጣጫ የሚተኩሱ ቢኖሩ ኖሩ፤በዚሕ ወፈፌ አይኖች መሐል በርቅሳ የምትገባ ጥይት ትኖር ነበር።እኒያ ጥሩ ሰዎች እዚሕ ጋ፤ ወገባቸዉ ላይ ወይም ቁርጭምጭሚታቸዉ አጠገብ ሽጉጥ ቢኖራቸዉ ኖሮ---ይሕ---------(የእንትን) ልጅ መተኮስ ሲጀምር እዚያ ቤት ከነበሩት አንዳቸዉ ቡም፤ቡም፣ቡም ይሕ ዉብ ትዕይንት ይሆን ነበር።»

ልጅ ከማለታቸዉ በፊት ያሉትን መድገም አልፈለግንም።በእንትን ቀየርነዉ።ገዳዩ ግንባሩን ይመታ አይመታ አናዉቅም ግን ተገድሏል።ባለቤታቸዉ ባንድ ወቅት እንደ ፕሬዝደንት እንዲታዩ፤ እንደፕሬዝደንት እንዲናገሩ «መክሬዋለሁ» ብለዉ ነበር።«የእንትን ልጅ» ማለት ፕሬዝደንታዊ ይሆን ይሆን ?

ብቻ ቱጃሩ ፖለቲከኛ እንዲሕ ናቸዉ።ዶናልድ ትራምፕ።ብቻቸዉን ግን አይደሉም።በጣም ብዙ ሚሊዮን ደጋፊ አላቸዉ።

የሪፐብሊካኑን ፓርቲ እጩነት ለማግኘት ሲፎካከሯቸዉ የነበሩ በርካታ አንጋፋ ፖለቲከኞችን በቀላሉ አሸንፈዉ በፓርቲዉ ለመታጨት ብቸኛዉ ፖለቲካኛ ለመሆን የበቁትም ከሐብታቸዉ ጋር በደጋፊያቸዉ ብዛት ነዉ።ፓርቲያቸዉ በመጪዉ ሐምሌ አጋማሽ በሚያደርገዉ ጉባኤ እጩነቱ እንደሚፀድቅላቸዉ እርግጠኛ ናቸዉ።

የምረጡኝ ዘመቻቸዉ ግን ቢመረጡ ከሚሠሩት ይልቅ ተቀናቃኛቸዉን ወይዘሮ ክሊንተንን እና በሥልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዝደንት ኦባማን በማሳጣቱ ላይ ያተኮረ ነዉ።«ሒላሪ ክሊንተን እንደምታዉቁት፤ አብዛኛዉ ሰዉ እንደሚያዉቀዉ በዓለም የለየላት ዉሸታም ናት።የኢሜይል መዝገቧንና ማብራሪያዋን ብቻ ተመልከቱ፤ ወይም ደግሞ በአዉሮፕላን ስትጓዝ ቦስኒያ አረፍኩ እና ጥቃት ደረሰብኝ ብላ እንደነበር አስታዉሱ።ጥቃት አደረሱ የተባሉት ግን አበባ የሚሰጧት ልጃገረዶች ነበሩ።ይሕ እራስን ለመጥቀም ያለመ፤ ፍፁም ቅጥፈት ነዉ።»

የዴሞክራቲኩን ፓርቲ እጩነት ያገኛሉ ተብለዉ የሚጠበቁት የሒላሪ ክሊንተን አፀፋ ቀላል አይደለም።የሰባ ዓመቱ አዛዉንት ለዓለም ዓይደለም ለአሜሪካ ፖለቲካም እንግዳ ናቸዉ።ለምጣኔ ሐብቱ ግን አዲስ አይደሉም።ቢሊዮናት ዶላር አጋብሰዉበታል እና።ይሁንና ሒላሪ ክሊንተን እንደሚሉት ሰዉዬዉ በምጣኔ ሐብቱም ቢሆን የግል ሐብት ከማጋባስ ባለፍ የሐገርን ዉስብስብ ምጣኔ ሐብታዊ መርሕ መምርት አይችሉም።

«ጣቱን (በኑክሌር ቦምብ) ቀለበት ላይ ማሳረፍ እንደማይችል ሁሉ እጁን በምጣኔ ሐብቱ ላይ ማሳረፍ አይችልም።»ዶናልድ ትራምፕ የጀርመን ስደተኛ ልጅ ናቸዉ።ባለቤታቸዉ የስሎቬንያ ስደተኛ ናቸዉ።ቢመረጡ ግን ስደተኛ አሜሪካ እንዳይገባ ሐገራቸዉን ከሜክሲኮ ጋር የሚያዋስነዉን ድንበር በግንብ ለማሳጣር ቃል ገብተዋል።አሸባሪዎችን ለማጥፋት ከሌሎች መንግሥታት ጋር ተባብረዉ ለመስራት ማቀዳቸዉን ይናገራሉ።ግን በተቃራኒዉ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግስት

ብሎ የሚጠራዉ ቡድን ዩናይቴትድ ስቴትስን የሚያሰጋዉ ወይዘሮ ክሊንተንና ኦባማ ከሌሎች መንግስታት ጋር ባደረጉት ስምምነት ምክንያት ነዉ ይላሉ።

«ISIS ዛሬ እኛን የሚያሰጋዉ ክሊንተን ከፕሬዝደንት ኦባማ ጋር ባሳለፉት ዉሳኔ ምክንያት ነዉ።»ዩናይትድ ስቴትስ ባሸባሪዎች እንዳትጠቃ የትራምፕ እቅድ ከሐገራት መሪዎችና ዲፕሎማቶች በስተቀር አንድም ሙስሊም አሜሪካ እንዳይገባ ማገድ።ተደጋጋሚ መፈክራቸዉ አሜሪካ አንደኛ ወይም ትቅደም ነዉ።የኩባንያ ቁሳቁሶቻቸዉ ግን አንድም የቻይና አለያም የሕንድ ወይም የሜክሲኮ ምርቶች ናቸዉ።«በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራቸዉን አጥተዋል።ባለአክሲዮኖች ከስረዋል።ብዙ አነስተኛ ኮንትራክተሮች ከፍተኛ ኪሳራ አጋጥሟቸዋል።ዶናልድ ትራምፕ ግን ምንም አልሆኑም።»

የቦስተኑ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ የያኔዉን የቴክሳስ አገረ ገዢ ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽን ጠየቃቸዉ።የቼችንያዉ ፕሬዝደንት ማን ይባላሉ ብሎ።አላዉቀዉም አንተ ታዉቀዋለሕ? ጠየቁ ተጠያቂዉ-መልስ መሆኑ ነዉ።ሁለተኛ ጥያቄ፤-«የታይዋኑን ፕሬዝደንት ስም ሊነግሩኝ ይችላሉ? «እ----እ---አዎ ሊ----ሊ ነዉ።« እሺ ግማሽ ነጥብ አግኝተዋል።» ሊ ቴንግ ሁይ ናቸዉ።ሰወስተኛ ጥያቄ፤-«በቅርቡ የፓኪስታንን የመሪነት ሥልጣን የያዙት ጄኔራል ማን ይባላሉ።» የቡሽ መልስ፤-«ጄኔራል-----አዲስ የተመረጠዉ ጄኔራል---እ--እ--እንደሚመስለኝ ይሕ ሰዉዬ በሐገሪቱ መረጋጋት የሚያሰፍን ይመስላል።ይሕ ጥሩ ዜና ነዉ----» እያሉ ዘባረቁ። ግን ተመረጡ።በድጋሚም ተመረጡ።አሜሪካ ነዉ ሐገሩ። ትራምፕስ-ማን ያዉቃል።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች