የአሜሪካ ጦር መዉጣትና ኢራቅ | ዓለም | DW | 23.08.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአሜሪካ ጦር መዉጣትና ኢራቅ

አራት ሺሕ አራት መቶ አስራ-ስድስት የአሜሪካ ወታደሮች ሕይወታቸዉን ለኢራቅ በረሐ ገብረዋል።ከሠላሳ-እስከ አርባ ሺሕ የሚገመቱ ቆስለዋል።ሌሎች የአዕምሮ በሽተኛ ሆነዋል።

default

ወታደሮቹ ሲወጡ

23 08 10

«እና የምናደርገዉ ከዚሕ ቀደም የገባዉን ቃል፥ በተያዘዉ የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ገቢር ማድረግ ነዉ።»

ኢራቅ የሠፈረዉ የአሜሪካ ጦር ወደ ሐገሩ መመለሱ ለፕሬዝዳት ኦባማ በርግጥ ከምርጫ ዘመቻ ጊዜ ጀምሮ የገቡትን ቃላቸዉን-ገቢር የማድረጋቸዉ ማረጋገጪያ ነዉ።ለወታደሮቹ ደግሞ፥-
«እንደምን ዋቃችሁ።ወደ ሐገራችሁ ለመሔድ ተዘጋጅታችኋል።»
ደስታ።
የመግደል-ማሸነፉ ድል-ፌስታ በመሞት መሸነፉ ክስረት-መርዶ ሲጣፋበት፥ ሰባት አመት ተመንፈቅ ያስቆጠረዉ ጦር አባላት ከዚያች ሐገር ሲወጡ የማይደሰቱበት ምክንያት በርግጥ የለም።ቃል የመከበሩ ዋቢ፥ ሐገር የመግባቱ ደስታ የወረራ-ዘመቻዉን አላማ መሳት እንጂ መሳካት አለማመልከቱ ነዉ አነጋጋሪዉ።ላፍታ እንነጋገር።
ሰባት አመት ከመንፈቅ።AntiWar (ፀረ-ጦርነት) የተሰኘዉ ተቋም እንደዘገበዉ በዚሕ ጊዜ ዉስጥ አራት ሺሕ አራት መቶ አስራ-ስድስት የአሜሪካ ወታደሮች ሕይወታቸዉን ለኢራቅ በረሐ ገብረዋል።ከሠላሳ-እስከ አርባ ሺሕ የሚገመቱ ቆስለዋል።ሌሎች የአዕምሮ በሽተኛ ሆነዋል።
ወታደር ማይክል ደሩሞንድ።የያኔዎቹ የዋሽንግተንና የለንደን መሪዎች ለድፍን አለም እንዳስታወቁት የኢራቅን ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ከፕሬዝዳት ሳዳም ሁሴን አረመኒያዊ መንግሥት ሊማርክ፥ የሳዳም አገዛዝን አስወግዶ ኢራቅን በልማት ፈጣን እንድገት፥ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የመካከለኛዉ ምሥራቅ ቀንዲል ሊያደርግ ቀድሞ የዘመተዉ የአሜሪካ ጦር አባል ነዉ።ጀግና ወታደር።

«ኢራቅ በገባሁበት የመጀመሪያዉ ሌሊት አንድ ቤተ-ሰብ በጥይት ደበደብኩ።ከዚያ በሕዋላ ደግሞ እኛን በBMW መኪና ሊገጨን የነበረ አንድ ሰዉዬን በጥይት መታሁት።»

ወጣቱ ወታደር ኢራቅ ዉስጥ አልሞተም።አልቆሰለምም።ግን ታመመ።
«እንቅልፍ ይነሳኝ ጀመር።ከዚያ በሕዋላ ደግሞ የሆነ የልዩ ሰዉ፥ ማንም የማይችለኝ አይነት ፍጡር’ የመሆን ስሜት አደረብኝ።ሁል ጊዜ በጣም አደገኛ ለሆነ ተልዕኮ የምታዘዝ ይመስለኛል»
ማይክል ብቻዉን አልነበረም።አይደለም።ኢራቅ ዉስጥ ከመሞት-መቁሰል ተርፈዉ ወደ ሐገራቸዉ ከተመለሱ ወታደሮች መካካል ከአርባ ከመቶ የሚበልጡት PTSD-በሚል ምሕፃረ ቃል በሚጠራዉ ጭንቀት ወይም የአእምሮ ሕመም ይሰቃያሉ።

የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ እና የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ጥቂት ታማኞቻቸዉን አስከትለዉ ኢራቅን ሲያስወርሩ ወረራዉ በወራት፥ ቢበዛ በአመት-እጅግ በጣም ቢበዛ ሁለት አመት እንድሜ፥ በትንሽ ኪሳራ ለድል እንደሚበቃ በተደጋጋሚ አስታዉቀዉ ነበር።

«ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅ ዉስጥ የጀመርነዉን ሥራችንን ታጠናቅቃለች።ኢራቅን ፈጥኖ ነልቀቅ አሸባሪዎች እንዲጠናከሩ ማድረግ ነዉ።እናም አሜሪካ ላይ ሊደርስ የሚችለዉን አደጋ የሚያባብስ ነዉ።እዚያዉ ለመቆየት፥ ለመዋጋትና ለማሸነፍ ቆርጠናል።የአሮጌዉ የባአዝ (ፓርቲ) አሸባሪዎች ይሸነፋሉ።ምክንያቱም አሜሪካና ተባባሪዎቻችን ግልፅ ሥልት አለን።ይሕ ሥልታችንም እየሠራ ነዉ።በመጀመሪያ ይሕን ዉጊያ ወደ ጠላቶቻችን (ሥፍራ) ወስደነዋል።እያሠስን፥ መሳሪያዎችና ሰዎችን እየማረክን፥ ገዳዮችን ለፍርድ እናቀርባለን።»

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ-ሕዳር 2003 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።)ቡሽና ብሌር ያዘመቱት ጦር የኢራቅ ባዓዝ ፓርቲ መስራችን፥ የእስከዚያ ዘመኑን ፕሬዝዳት ሳዳም ሁሴንን ከቤተ-መንግሥት አስወግዶ ጎሬ ለመዶል፥ ከተሸሸጉበት ጎሬ ለማዉጣት፥በተጣደፈ-ፍርድ ባግዳድ አደባባይ ለማስጠንልጠልም በርግጥ ጊዜ አልፈጀበትም። ወትሮም ያልነበረዉ የሳዳም ሁሴይን ጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ ግን ያኔ-ከያኔ እስከ ዛሬ አይደለም ከንግዲሕም ለምዕተ-አመታት ቢታሰስ ሊገኝ አይችልም።

Irak Anschlag auf Rekruten in Bagdad Mann im Krankenhaus

የሽብሩ ዉጤት

ኢራቅን ሠላም የሰፈነባት፥ ዲሞክራሲ የሰረፀባት፥ባለጠጋ ለማድረግ የዋሽንግተን-ለንደን መሪዎች እና የባግዳድ ተከታዮቻቸዉ የገቡት ቃልም-እንደ ጅምላ ጨረሹ መሳሪያ ሁሉ ወትሮም መሠረት አልነበዉምና ከዘመኑ ሒደት ጋር በነነ።ዘንድሮ በዚሕ ወር ሰባት አመት ከመንፈቁ።ኢራቅ በወረራዉና በመዘዙ፣-ያጠኑ እንደሚሉት ከአንድ ሚሊዮን ሰወስት መቶ ሺሕ በላይ ሕዝቧ ተገድሎበታል። የቆሰለዉን በትክክል የቆጠረዉ የለም።ከሞተ-ከቆሰለዉ ሌላ 2.3 ሚሊዮን ኢራቃዊ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል።2.2 ሚሊዮኑ ተሰዷል።የኢራቅ ሕዝብ ባጠቃላይ ሃያ-አምስት ሚሊዮን ነዉ።የጥንቷ ሥልጡን፥የነዳጅ ሐብታም፥ የአረቡ አለም ምሑራን መፍለቂያዋ ሐገር ዛሬም በቦምብ ትሸበራለች።

ያለፈዉ ሳምንት ሮብ ለፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የቃላችዉ ገቢራዊነት ማረጋገጫ-፥ኢራቅ ለነበሩት የአሜሪካ ወታደሮች ደግሞ ሐገራቸዉ የሚገቡበት የደስታ ዋዜማ ነበር።ለባግዳድ ግን ሰባት አመት ከመንፈቅ የለመደችዉ የሽብር-እልቂት ፍጅት ዕለት።ፕሬዝዳት ጆርጅ ዳብሊዉ ቡሽ ኢራቅን ከባአዚስቶች እና ከአሸባሪዎች እንደሚያፀዱ ቃል-በገቡበት ዘመን የተወለደ ልጅ ዘንድሮ አንደኛ ክፍልን አጠናቀቀ።

ባግዳድ ግን አሁንም ትሸበራለች።ሮብ።በአንድ የወታደሮች መመልመያ ቅፅር ግቢ አጥፍቶ ጠፊ ባፈነዳዉ ቦምብ በትንሽ ግምት ሥልሳ ሰዉ አጥፍቶ-ጠፋ።አብዛኞቹ ወደ ሐገራቸዉ የሚመለሱትን የአሜሪካ ወታደሮችን የሚተኩ የኢራቅ ወታደሮች ለመሆን የተሰለፉ ነበሩ።ሞቱ ቆሰሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ ዉጤቱ ቢያንስ እስካሁን በዉል ላልታወቀ ወረራ በሰዉ ሕይወትና አካል ከከፈለችዉ ኪሳራ በተጨማሪ በአለም ላይ የነበራትን ክብርና ሞገስ አጥታለች።የምጣኔ ሐብቱ ድቀት ደግሞ ቀላል አይደለም።የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የአብዛሐዉ መሪ ሐሪ ሬይድ በሁለት ሺሕ ስምንት እንዳስታወቁት አሜሪካ ኢራቅ ዉስጥ በየአንዳዱ ሴኮንድ አምስት ሺሕ ዶላር ታወጣለች።

በርግጥ አንድ የአሜሪካ ወታደርን ኢራቅ ዉስጥ ለአንድ አመት ለማቆየት 390,000 ዶላር ይወጣል። ባለፉት ሰባት አመት ከመንፈቅ ዘጠኝ መቶ ቢሊዮን ዶላር ወጥቷል።ከዚሕ ዉስጥ ግን ዘጠኝ ቢሊዮን ያክል ለምን አለማ እንደወጣ በትክክል አይታወቅም።ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉን ጦር ያዘመተችዉ ብሪታንያም ከፍተኛዉን መስዋዕትነት በመክፈል ሁለተኛዋ ሐገር ናት።አንድ መቶ ሰባ ዘጠኝ ወታደሮችዋ ተገድለዉባታል።በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።በቢሊዮን ፓዉንድ የሚቆጠር ገንዘብ አዉጥታለች።

የሕዝባቸዉን ተቃዉሞ ንቀዉ ወረራዉን ያፀደቁት፥ ጦሩን ያዘመቱት የያኔዉ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ሐገራቸዉ ይሕን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለችበትን ወረራ ዉጤት በትክክል መነጋር አልቻሉም።ወይም አልፈለጉም።ብሌር በወረራዉ ሰበብ በሕዝብ ዘንድ የነበራቸዉን ተወዳጅነት አጥተዋል። ሥልጣናቸዉን ለመልቀቅ ተገደዋል።የወረራዉን ሒደትና የብሪታንያ ተሳትፎ ለመመረመዉ አጣሪ ኮሚሽን እንዳሉት ግን በፈፀሙት ሁሉ የሚፀፅታቸዉ ነገር የለም።

ይሁንና ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ኢራቅ የሠፈረዉን ጦር ለማስወጣት የገቡትን ቃል ገቢር ማድረጋቸዉን ከዋሽግተን-ባስታወቁበት ፥የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ሐገራቸዉ የመመለሳቸዉ ደስታ ከባግዳድ በተሰማበት ዕለት ግን ቶኒ ብሌር ካሳተሙት መፅሐፍ ሺያጭ በኢራቅ ወረራ ለቆሰሉ፥ ለታመሙ ወታደሮች ማገገመያ፥ ለሞቱት ቤተሰቦች መደጎሚያ እንዲዉል መስጠታቸዉ ተዘገበ።

ብሌር 5.6 ሚሊዮን ዮሮ የሚገመተዉን የመፅሐፍ ሽያጭ ከአፍቃኒስታን ይልቅ በኢራቅ ወረራ ለተጎዱት ወታደሮች ማገገሚያ መስጠታቸዉ አንዳድ የፖለቲካ አዋቂዎች እንዳሉት የወረራዉን ዉጤት ከንቱነት የማመናቸዉ ምልክት ነዉ።ወታደር ልጃቸዉ ኢራቅ ዉስጥ የተገደለባቸዉ ብሪታንያዊ አባት እንደሚሉት ግን ብሌር የመፀሐፍ ሽያጭ ልስጥ ከሚሉ ይልቅ ይቅርታ ቢጠይቁ ያስከብራቸዉ ነበር።
«እሳቸዉ (ብሌር) የኢራቅን ወረራ ለመመርመር ከተሰየመዉ ጌታ ጆን ቺልኮት ከመሩት ኮሚሽን ፊት በቀረቡበት ወቅት የተጎዱትን ቤተሰቦች ይቅርታ ለመጠየቅ ጥሩ አጋጣሚ አግኝተዉ ነበር።ይሑንና ሥለዚሕ ጉዳይ ምንም የጠቀሱት ነገር የለም።»

አንድን ሐገር በሐሰት ወንጅሎ፥ የአለም ሕግን ጥሶ፥ የራስን ሕዝብ ተቃዉሞ ጥሶ የራስንም የሌላንም ሐገር ዜጎች ሕይወት፥ አካል ሐብት-ንብረት የሚያወድም ወረራ እንደ ስሕተት የሚታይበት-ይቅርታ የሚጠየቅበት ዘመን መቼነት በርግጥ ይናፍቃል።የአሜሪካ ጦር ወደ ሐገሩ መመለስ፥የብሪታንያ ወታደሮች የማገገሚያ ድጎማ ማግኘት፥የቶኒ ብሌር ይቅርታ-መጠየቅ አለመጠየቅ ለአብዛኛዉ ኢራቃዊ ላሁኑ የሚተክረዉ የለም።የሐገሪቱ ሕዝብ እንደ ዲሞክራሲያዊዉ ወግ ከስድስት ወር በፊት መሪዎቹን መርጦ ነበር።እስካሁን ግን መንግሥት አልተመሠረተም።ከሰባት መቶ ሺሕ የሚበልጥ ፀጥታ አስከባሪ አለ።ፀጥታ ግን የለም።አንድ የባግዳድ ነዋሪ እንደመሰከሩት ኢራቆች ሁሉም ተንዶባቸዋል።
«በዚች ሐገር ሁሉም ነገር ተመሰቃቅሏል።እዉነቱን ለመናገር ሁሉም ነገር መበለሻሸቱን መረዳት አይገድም።መንግሥት የለንም።ፀጥታም የለንም።»

No Flash Irak Gewalt Sicherheitskräfte

ፀጥታ አስከባሪዉ


ፀጥታን ለማስከበር ተስፋ ካለ እዚያዉ ኢራቅ የሚቆየዉ ስልሳ ሺሕ የአሜሪካ ወታደር የሚያሰለጠነዉ የኢራቅ ጦር ብቃት ነዉ-በያኙ።አስተማማኝ መንግሥት ለመመስረት ተስፋ-ካለ የሐገሪቱ ፖለቲከኞች ብልጠት ነፃነት ነዉ-መሠቱ። ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ


Audios and videos on the topic