1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ ድጋፍ በኢትዮጵያ

ሰኞ፣ መስከረም 20 2017

የዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለመተባበር ቁርጠኛ ሆና እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የአሜሪካው አምባሳደር ተናገሩ። አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ እንዳሉት ምክክር የሁሉንም ሰው ፍላጎት እና ምኞት የሚያከብር መፍትሔ ለማምጣት ብቸኛው መንገድ ነው ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4lEPH
የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአዲስ አበባምስል Seyoum Getu/DW

የአሜሪካ ድጋፍ በኢትዮጵያ

የዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለመተባበር ቁርጠኛ ሆና እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የአሜሪካው አምባሳደር ተናገሩ።

አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በአሜሪካ መንግሥት ሲሰጥ የቆየው ያለፉት የአምስት ዓመታት ሁሉን አቀፍ የኢትዮጵያ የድጋፍ መርሐ ግብር መጠናቀቁን አስመልክተው ባደረጉት ገለፃ፣ ምክክር የሁሉንም ሰው ፍላጎት እና ምኞት የሚያከብር መፍትሔ ለማምጣት ብቸኛው መንገድ መሆኑን በመጥቀስ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያንን ለማሳካት የምታደርገውን እገዛ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የሚደገፈው "የኢትዮጵያ ድጋፍ" ያለፉት ዓምስት ዓመታት መርሐ ግብር መጠናቀቁን በተመለከተ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ላይ አጭር ገለፃ ያደረጉት በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ መንግሥታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ግንኙነትን ማጠናከር፣ ንግግርን እና ምክክርን ማስቀጠልን መደገፉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ግጭት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የተናገሩት አምባሳደሩ፤ ከጦርነት እና ግጭቶች በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በጎ የኢኮኖሚ ለውጥ ይመዘገብ እንደነበር አሐዞችን ጭምር በመጥቀስ ተናግረዋል።

ኤርቪን ማሲንጋ የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ
ኤርቪን ማሲንጋ የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ ምስል Abebe Feleke/DW


በትግራይ ክልል በጦርነቱ ለችግር የተጋለጡ ሰዎች የድህረ ጦርነት የዓዕምሮ ማገገም እንዲያገኙ ጥረት መደረጉን፣ ግጭት በሕፃናት ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን፣ ለአብነት በቅርቡ በአማራ ክልል የደረሰውን የከፋ ሁኔታ እና በክልሉ 4178 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ሪፖርት መደረጉን በመጥቀስ የችግሩን አሳሳቢነት አመልክተዋል። ስለሆነም ሰላም ሕፃናትን ወደ ትምህርት ቤት እና ወደ ጤናቸው እንደሚመለሱ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን በአፅንዖት አንስተዋል።

«የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከእናንተ [የድጋፉ ተጠቃሚ አግልሮች] እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለመተባበር ቁርጠኛ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ምክክር የሁሉንም ሰው ፍላጎት እና ምኞት የሚያከብር መፍትሔ ለማምጣት ብቸኛው መንገድ ነው»።ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ግጭት ንፁሃንን ለሞት መዳረጉን፣ የጾታ ጥቃትን ጨምሮ  የከፋ የመብት ጥሰት ማስከተሉን በማብራሪያቸው ያመለከቱትአምባሳደር ማሲንጋ የፖለቲካ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ሀገራቸው እና ተልዕኳቸው ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የተራድኦ ድርጅት (USAID) የኢትዮጵያ መርሐ ግብር ታቅፈው የሚሠሩ ከ 170 በላይ ባለድርሻዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የምክክር ባህል እንዲያድግ ጥረት ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉም ጠይቀዋል።

ኤርቪን ማሲንጋ የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ
ኤርቪን ማሲንጋ የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ ምስል Seyoum Getu/DW


ከሳምንት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ኢትዮጵያ ውስጥ በየክልሎች የሚካሄደውን ግጭት ለማስቆም ውይይት ማድረግ እና በትግራይ ክልል  የጠመንጃ ላንቃ መዘጋቱን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ለማገዝ ወደ ኢትዮጵያ መጓዛቸውን ጉልፀው ነበር።

በወቅቱ ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትን እና ሕብረት ለመደገፍ ቁርጠኛ ነች ያሉት ባለሥልጣኑ፣ ይህ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት አጋርነት አንኳር ጉዳይ መሆኑንም አውስተው ነበር።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ሰለሞን ሙጨ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ