የአሜሪካ ዴሞክራቶች የምርጫ ጉባዔ ታሪካዊ ፍጻሜ | ፖለቲካ | DW | 29.08.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ፖለቲካ

የአሜሪካ ዴሞክራቶች የምርጫ ጉባዔ ታሪካዊ ፍጻሜ

የአሜሪካ ዴሞክራቶች ፓርቲ ለመጪው ጥቅምት ወር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ዕጩውን ለመሰየም ሣምንቱን ያካሄዳው የልዑካን ጉባዔ ትናንት ማምሻውን በደመቀ ሁኔታ ተፈጽሟል። ፓርቲው ባራክ ኦባማን አንድነት በሰፈነበት መንፈስ ዕጩው አድርጎ ሲሰይም እርሳቸውም ምርጫውን በይፋ ተቀብለውታል።

በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ አንድ-አፍሮ-አሜሪካዊ ለፕሬዚደንትነት ሲታጭ የመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ባራክ ኦባማ ባለፈው ምሽት በጉባዔው መዝጊያ በዴንቨር ስታዲዮም ውስጥ ለተሰበሰቡ 85 ሺህ ገደማ የሚጠጉ የፓርቲው ልዑካንና ደጋፊዎቻቸው ያሰሙት ንግግርም ያንኑ ያህል ታሪካዊ የሚሰኝ ነበር። ባራክ ኦባማ የአሜሪካን ሕዝብ ሕልምና ራዕይ ባጎላ ንግግራቸው ትልቁን ፈተና እንዳለፉ ነው ታዛቢዎች የተናገሩት።

“ለሊቀ-መንበር ዲንና ለታላቅ ወዳጄ ዲክ ደርቢን፤ እንዲሁም ለመላው መሰሎቼ የዚህች ታላቅ አገር ዜጎች! ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንትነት መታጨቴን ባታላቅ ምሥጋናና በትሕትና ነው የምቀበለው”

ባራክ ኦባማ ከአርባ ደቂቃዎች በላይ የፈጀ ታሪካዊ ንግግራቸውን የጀመሩት እንዲህ ነበር። የዴንቨር ስታዲዮም አድማስ ምሽቱን በርችትና በትርኢት ሲያሸበርቅ የዴሞክራቱን ፓርቲ ጉባዔ ያደመቀው ግን ይህ ብቻ አልነበረም። ለውጥን ወይም ተሃድሶን መሪ መፈክራቸው አድርገው የተነሱት የኦባማ ታሪካዊ ንግግር ጭምር እንጂ! ኦባማ አሜሪካን የምንለውጥበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል። ሤናተር ኦባማ የአሜሪካን ማሐበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊና የውጭ ፖሊሲ አንስተው ራዕያቸውን ሲያብራሩ የእስካሁኑ የጆርጅ ቡሽ የአስተዳደር ዘመን የከሸፈ እንደነበር በማመልከት ቀጣይ ሊሆን እንደማይገባውም ነው ያስገነዘቡት።

“የተሰበሰብነው ወሣኝ በሆነ ወቅት ላይ ነው። ወቅቱ አገራችን በጦርነት ላይ የምትገኝበት ነው። ጊዜው ኤኮኖሚያችን የተናወጸበት፤ የአሜሪካ የተሥፋ ቃል-ኪዳንም እንደገና አደጋ ላይ የወደቀበት ነው። በዚህች ምሽትም ይበልጥ አሜሪካውያን ሥራቸውን ያጣሉ። ይበልጥ አሜሪካውያን ለትንሽ ገንዘብ ብዙ ይሰራሉ። ብዙዎቻችሁ ቤቶቻችሁን አጥታችኋል። ዕዳ መክፈል ተስኗችኋል። ይህ ሁሉ ደግሞ የዋሺንግተን፤ የተሳሳተው የጆርጅ ቡሽ ፖሊሲ ያስከተለው ውጤት ነው”
የዴሞክራቱ ፓርቲ ዕጩ አያይዘውም “አሜሪካ ሆይ! ካለፉት ስምንት ዓመታት የተሻልን ነን። የተሻልን አገር ነን” ብለዋል። ባራክ ኦባማ አብዛኛውን ጊዜ የጆርጅ ቡሽን ፖሊሲ ሲደግፉ የቆዩት ተፎካካሪያቸው የሬፑብሊካኑ ፓርቲ ዕጩ ጆን ማክኬይን መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣታቸው ዋስትና እንደሌለ በማስገንዘብ ፕሬዚደንት ሆነው ቢመረጡ ለሠራተኛው ቤተሰብና ለመካከለኛው የሕብረተሰብ ክፍል የሚጠቅም አጠቃላይ የማሕበራዊና የኤኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ እንደሚያካሂዱ ቃል ገብተዋል። ምርጫው ዜጎች በሙሉ እኩል ዕድል የሚያገኙበት የአሜሪካ የተሥፋ ቃል ኪዳን በ 21ኛው ምዕተ-ዓመትም ጸንቶ እንዲቀጥል መልካም አጋጣሚ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ኦባማ ታሪካዊ በሆነ ንግግራቸው ብቻ ሣይሆን በተለይ የሂላሪይና የቢል ክሊንተንን፤ እንዲሁም የቴድ ኬኔዲይን መሰል የዴሞክራቱን ፓርቲ ቀደምት ፖለቲከኞች ድጋፍ በማግኘታቸው ለመጪው ጥቅምት ምርጫ ከጉባዔው ይበልጥ ተጠናክረው እንደወጡ የብዙዎች ዕምነት ነው። የ 47 ዓመቱ ጎልማሣ ሤናተር ከሬፑብሊካን ተቀናቃኞቻቸው ጉራ በቂ የፖለቲካ ልምድ የላቸውም ሲል ሲሰነዘርባቸው የቆየው የማጣጣል ዘመቻ በብዙዎች ዘንድ ያሳደረውን ጥርጣሬ በሰከነ፣ የሕዝብን የልብ ትርታ ባደመጠና ትግል በተዋሃደው መንፈስ ረገብ እንዲል አድርገውታል። ኦባማ በፖለቲካው መድረክ ላይ ከአራት ዓመት በላይ ባይቆዩም ብቃታቸውንና አገር ወዳድነታቸውን አጠያያቂ ላደረጉት ሬፑብሊካኖች ትናንት የሰጡት ምላሽ የሚደነቅ ነው።

ከዚህ አንጻር የሬፑብሊካኑ ዕጩ ጆን ማክኬይን በመጪው ሣምንት በሚካሄደው የፓርቲያቸው ጉባዔ ላይ የኦባማን ታላቅ ንግግር ለማስናቅ መብቃታቸው ሲበዛ ያጠራጥራል። ቢቀር ቀላል ነገር አይሆንላቸውም። እርግጥ የዴሞክራቱን ፓርቲ ጉባዔ በሚገባ ተከታትለዋል። ቢሆንም ስለ ትናንቱ ምሽት ታሪካዊ ንግግር ግን ብዙ ማውራቱን አልመረጡም።

“ፉክክሩን ነገ እንደገና እንቀጥልበታለን። ለዛሬው ግን የምለው አንድ ነገር ብቻ ነው። ግሩም ነበር ሤናተር!”
ማክኬይን ከልብም ይሁን አይሁን ቢቀር በአንድ የምርጫ ቅስቃሣ ማስታወቂያቸው ኦባማን እንኳን ደስ ያለዎት ብለዋቸዋል። ለማንኛውም ሁለቱ ዕጩዎች በሚቀጥሉት ሣምንታት የሚያካሂዱት ፉክክር የቃላት ፍልሚያ የሰመረበት እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም።