የአሜሪካ የባንኮች ክስረትና የፊናንስ ቀውሱ አደጋ | ኤኮኖሚ | DW | 17.09.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአሜሪካ የባንኮች ክስረትና የፊናንስ ቀውሱ አደጋ

ከታላላቁ የአሜሪካ የመዋዕለ-ነዋይ፤ ኢንቨስትመንት ባንቦች አንዱ ሌህማን ብራዘርስ ባለፈው ሰኞ ክስረት ላይ መውደቁን ማስታወቁ በዓለም የፊናንስ ገበዮች ላይ ብርቱ ነውጽ ነው የቀሰቀሰው።

የኒውዮርክ የፊናንስ ገበያ

የኒውዮርክ የፊናንስ ገበያ

ከኒውዮርክ እስከ ለንደን፤ ከፍራንክፈርት እስከ ቶኪዮ የቀውሱ ትርታ ብዙ የምንዛሪ ገበዮችን አዳርሷል። ይሄው ገና ማለቂያው ያልታወቀ ውዥቀት የሰላሣኛዎቹን ዓመታት መሰል ዓለምአቀፍ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ እየደቀነ ይሆን? በወቅቱ አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ሂደቱ የሚገታ ነው ይላሉ፤ ሎሎች ደግሞ የዓለም ኤኮኖሚ ከቀውስ ብዙም ሩቅ እንደማይሆን ነው የሚናገሩት። የችግሩ አሳሳቢነት ግን ሁሉም የሚጋሩት ሆኗል።

ያለፈው ሰንበት በአሜሪካ የምንዛሪ ገበያ ላይ ባለፉት አሠርተ-ዓመታት ተመሳሳይ ያልታየለት ውዥቀት የታየበት ነበር። በ 2006 ዓ.ም. በቤት ባለንብረቶች ዕዳ ሳቢያ የጀመረው የአሜሪካ የባንኮች ቀውስ በወቅቱ ያልተጠበቀ አስደንጋጭ አቅጣጫ መያዙና ችግሩ እየተባባሰ መሄዱ የተሰወረ ነገር አይደለም። አራተኛው ታላቅ የአሜሪካ የመዋዕለ-ነዋይ ባንክ ሌህማን ብራዘርስ ተንኮታኩቶ ሲወድቅ ሶሥተኛው ሜሪል ሊንች ደግሞ እስትንፋስ በሚያሳጣ ፍጥነት መሸጡ ግድ ሆኖበታል።
ገዢው የአሜሪካ ባን’ክ ነው። ነገሩ በዚህ ብቻ አላበቃም። የአሜሪካው ዓለምአቀፍ የኢንሹራንስ ቡድን AIG-ም በአንድ ቀን ሁለት-ሶሥተኛ የገበያ ዋጋውን አጥቷል። ነፍስ ለመዝራት የድጎማ ያለህ እያለ ነው። የሚያስፈልገው መንሰራሪያ ገንዘብ በአርባ ሚሊያርድ ዶላር ይገመታል። ይሄው ተቁዋም ከመደበኛው ኢንሹራንስ ባሻገር ሃብትን በማስተዳደሩ ተግባርም ግዙፍ ተሳትፎ ያለው ሲሆን ክስረቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚኖረው ተጽዕኖ ቀላል አይሆንም። ጉዳዩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ መንፈቅ ባልሞላ ጊዜ ከአሜሪካ አምሥት ቀደምት የመዋዕለ-ነዋይ ባንኮች መካከል ሁለተኛው ሌህማን ብራዘርስ መክሰሩ ነው።
ባንኩ ድጋፍ ማግኘቱ ቀላል ነገር አልሆነም። ለዚህም ምክንያቱ ለውድቀት የተጋለጡትን የባንኩን የገንዘብ ሰነዶች ለብቻው ወይም ያለ አሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ለመግዛት የሚደፍር አለመኖሩ ነው። የገንዘብ ሚኒስትሩ ሄንሪይ ፓውልሰን መንግሥት ከዚህ ቀደም ለሌሎች እንዳደረገው አንዳች የፊናንስ ዕርዳታ እንደማይሰጥ ቁልጭ ባለ መንገድ ነው ያስገነዘቡት። በዚሀ በጀርመን የፍራንክፈርት ዩኒቨርሲት የፊናንስ ፖሊሲ ፕሮፌሰር ፎልከር ቪላንድ ውሣኔው ተገቢ ነው ባይ ናቸው።

“መንግሥት በያንዳንዱ ሁኔታ ጣልቃ መግባቱ ተገቢ እንዳልሆነ መመልከቱ ጊዜው አሁን ነው ብዬ አስባለሁ። መለስ ብለን የቢር-ስተርንስን ጉዳይ ከተመለከትን መንግሥት ምርጫ አልነበረውም። ሁኔታው ያልተጠበቀ ነበርና ዕርምጃ መውሰድ፤ መርዳት ነበረበት። አሁን ባለፈው ሣምንትም የገንዘብ ሚኒስቴሩ ፋኒ-ሜይና ፍሬዲ-ማክን ለማዳን ዕርምጃ ወስዷል። ይህ ሂደት ባለበት ሊቀጥል አይችልም። ለዚህ ነው መንግሥት ሁልጊዜ አናግዝም ያለው”

የቀውሱ መነሻ አሜሪካ ብትሆንም ችግሩ በዚህ በአውሮፓም ብርቱ ስጋትን ነው ያስከተለው። በጀርመን የማይንስ ከተማ የፊናንስ ምርምር ኢንስቲቲዩት ሃላፊ ሮልፍ ፔፍክሆፈን እንደሚሉት ችግሩ ቢቀር በዚህ ዓመት ቀጣይነት ሊኖረው የሚችል ነው።
“በዓመቱ ሂደት አንዳንድ ተመሳሳይ ኪሣራዎች መከሰታቸው አይቀርም ብዬ ነው የምገምተው። እና ቀውሱና ከዚሁ ተያይዞ የሚከተለው ሁኔታ የምናተኩርበት ጉዳይ ይሆናል። ግን አይደርስም አይባልም፤ የኤኮኖሚ ቀውስ ከተከተለ በዓለምአቀፍ ደረጃና በዚህ በጀርመንም ተጽዕኖ እንደሚኖረው መጠበቅ ይኖርናል”

በአሜሪካ የታላላቆቹ የመዋዕለ-ነዋይ ባንኮቸ መንኮታኮት እርግጥ እስካሁን ገና ዓለምን ከሰላሣኛዎቹ ዓመታት መሰል የፊናንስ ቀውስ ላይ አልጣለም። ሆኖም የወቅቱ ችግር በዓለምአቀፉ የፊናንስ ስርዓት ላይ ከባድ የፖሊሲ ስህተቶች መፈጸማቸውንና ቢቀር መንታ መንገድ ላይ መደረሱን የሚያመለክት ነው። ቀደምቱ የመዋዕለ-ነዋይ ባንኮች ለዓመታት ከፍተኛ ትርፍ ለማስገባት ባደረባቸው የመስገብገብ ባሕርይ በየጊዜው ያልፈጠሩት መላ፤ ያልሞከሩት ነገር አልነበረም። በብድር አሰጣጡ ረገድ ድርጊቶቻቸው ብዙም ከቁማር የተለዩ ነበሩ ለማለት አይቻልም። የባለሥልጣናቱ ክፍያም ራሱ አዕምሮ ሊቀበለው ያዳግታል። አሁን እንግዲህ ለብዙዎች ዱብ-ዕዳ የሆነው የዚህ አሠራር ዘይቤ ውጤት ጭምር ነው።

ባለፈው ዓመት የሜሪል ሊንች አስተዳዳሪ የሆኑት ጆን ቴይን በቅርብ እስከተሰናበቱበት ጊዜ ድረስ የዓመት ደሞዛቸው ከ 80 ሚሊዮን ዶላር የሚበልጥ ነበር። ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ነገር ነው። በአንጻሩ አሁን በደረሰው ክስረት ንብረታቸውንና ሥራቸውን የሚያጡት፤ ባዶ ዕጃችቸውን የሚቀሩት ብዙዎች ናቸው። ከቀድሞው የባንኩ ሠራተኞች አንዱ እንደሚሉት አመራሩ የችግሩን ክብደት በሚገባ አላጤነም።

“ሃላፊነት ያለባቸው ሰዎች አደጋውን አቃለው ነው የተመለከቱት። በመሆኑን አሁን ሸክሙ ሌሎች ነው የወደቀው”

ለመሆኑ የአሜሪካ የመዋዕለ-ነዋይ ባንኮችን ከአውሮፓ ለየት የሚያደርጋቸው ምንድነው? ለምሳሌ በዚህ በጀርመን ባንኮች በሁሉም የፊናንስ ዘርፍ መነገድ ይችላሉ። በአሜሪካ ሁኔታው እስከ ዘጠኝ ዓመታት ገደማ በፊት ድረስ የተለየ ነበር። ማለት ባንኮቹ በተወሰነ ዘርፍ ላይ አተኩረው ነው የቆዩት። እርግጥ ከዚያን ወዲህ ሁሉም የአሜሪካ ባንኮች በመሠረቱ በሁሉም ዘርፍ መሰማራት የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱ አልቀረም። ይሁንና ዛሬም በተወሰነ ነገር ላይ አተኩረው ነው የቀጠሉት።
ከነዚሁ አንዱም ኢንቨስትመንት-ባንኪንግ፤ የመዋዕለ ነዋዩ ዘርፍ ነው። አምሥቱ የአሜሪካ ታላላቅ ባንኮች ጎልድማን-ሣክስ፣ ሌህማን-ብራዘርስ፣ ሜሪል-ሊንች፣ ሞርጋን ስታንሊይም ሆነ ቢር-ስተርንስ ግለሰቦች የገንዘብ ማስተላለፊያና የቁጠባ ሂሣብ ከፍተው የሚገለገሉባቸው ወይም ብድር የሚያመለክቱባቸው ቅርንጫፎች የሏቸውም። የግል ደምበኞች አያስተናግዱም ነበር ማለት ነው። በአንጻሩ እንደ መዋዕለ-ነዋይ ባንክ በከፍተኛ ደረጃ መነገዱን ነው የሚመርጡት። ካፒታል ለማከማቸት ራሳቸው የመደቡትን ገንዘብ ያበድራሉ፤ ወይም ይህን ተግባር ካፒታል ለሚሹ ኩባንያዎች ያካሂዳሉ።

ከዚሁ በተጨማሪ ኩባንያዎች ከምንዛሪው ገበያ ለመግባት የሚያደርጉትን ሂደት ያጅባሉ፤ የታላቅ ደምበኞቻቸውን ንብረት ያስተዳድራሉ። ኩባንያዎችን በመግዛትና በኩባንያዎች ውስጥ ተሳትፎ በማድረጉ ረገድ ማማከሩም አንዱ ሥራቸው ሆኖ ቆይቷል። ለራሳቸውና ለደምበኞቻቸው በገንዘብ ሰነዶች መነገድ፤ በአጠቃላይ የፊናንሱን ገበያ የሚደግፍ ማንኛውንም ተግባር ማከናወን ወዘተ,። ይህ አንድ-ወጥ ጉዞ ነው አሁን የችግሩን መጠን ያባባሰው።

የአሜሪካ ባንኮች ኪሣራ መፈራረቅና የምንዛሪው ገበያ ውዥንብር በዚህ በአውሮፓም ስጋት ማሳደሩ አልቀረም። በመሆኑም ለምሳሌ በዚህ በጀርመን ፖለቲከኞች፣ ባንኮችና የኤኮኖሚ ጠበብት ሁኔታው ሊያስከትል የሚችለውን ውዥምብር ከወዲሁ ለመግታት አረጋጊ ቃል እየሰነዘሩ ነው። ብዙዎቹ በአሜሪካ የተነሣው የፊናንስ ቀውስ ለኤኮኖሚያችን አደገኛ አይደለም፤ ልንገታው የምንችለው ነገር ነው ይላሉ። ከነዚሁ አንዱ የፊናንስ ሚኒስትሩ ፔር ሽታይንብሩክ ሲሆኑ ሰሞኑን በፌደራሉ ፓርላማ የበጀት ክርክር ላይ ባሰሙት ንግግር የጋዜጠኞችን የአዘጋገብ ዘይቤ የተጋነነ በማለት አስተባብለዋል።

“እርግጥ ይህ የፊናንስ ገበያ ቀውስ ሰፊ ተጽዕኖ የሚኖረውና በጣም የሚያሳስብም ነው። በጀርመን ላይም ግፊት ማሳደሩ አያጠራጥርም። ሆኖም የጀርመንን የፊናንስ ስርዓት እርጋታ አጠያያቂ ለማድረግ ምክንያት የለም። የጀርመን ባንኮች ጥንካሬ ዛሬ ከበፊቱ የተሻለ ነው። ከአሜሪካ የባንክ ስርዓት ይልቅ ጠንካራና የማይበገር መሆኑን አስመስክሯል”

በሌላ በኩል የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ፣ የእንግሊዝ ባንክና የስዊስ ብሄራዊ ባንክ የገንዘብ ፍሰት ጥበትን ለመግታት በፊናንሱ ገበዮች ላይ ብዙ ሚሊያርድ አፍሰዋል። ሌሎች ባንኮችም ተመሳሳይ ዕርምጃ በመውሰድ ላይ ናቸው። ይህም ሆኖ በዚህ በጀርመን የፊናንሱ ቀውስ በአገሪቱ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ወሣኝ ተጽዕኖ ይኑር-አይኑረው የተለያየ አመለካከት መከሰቱ አልቀረም። የሃምቡርግ የዓለም ኤኮኖሚ ጥናት ኢንስቲቲቱት ባልደረባ ሚሻኤል ብሮይኒገር እንደሚሉት ከሆነ ብዙም የሚያስብ ነገር የለም።

“የፊናንሱ ዘርፍ በከባድ ቀውስ ተመቷል። እንደ ዕድል ሆኖ ግን የኤኮኖሚው መስክ በሰፊው አልተነካም። እርግጥ የባንኩ ቀውስ ጎጂ ተጽዕኖ እንዳለው አያጠያይቅም። ይሁንና በዓለም ኤኮኖሚ ላይ በወቅቱ የቀውስ ሁኔታ አይታየንም። እንበል የፊናንሱ ቀውስ መሃሪ ሆኖ ነው አልፎን የሄደው”

የሆነው ሆኖ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ፕሬዚደንት ዣን-ክላውድ-ትሪሼ በፊናንስ ገበያው ላይ ከተከሰተው አሳሳቢ ነውጽ አንጻር ልዩ ንቃት እንደሚያስፈልግ ነው የሚያስገነዝቡት። በርሳቸው አባባል የዋጋ ውጣ-ውረድ መገታት ለፊናንስ መረጋጋት አንዱ ቅድመ-ግዴታ ነው። ትሪሼ ከዚህ ሻገር በማለትም በወቅቱ ለጽኑ ትኩረት እንጂ ለራስ እርካታ ጊዜ እንደሌለም ተናግረዋል። በዕውነትም ጊዜው ንቃትን የሚጠይቅ ነው። የኤኮኖሚ ቀውስ አደጋ ለጊዜው የለም ቢባልም ችግሩ ገና ጨርሶ አክትሞለታል ለማለት የሚቻል አይደለም። ይህ የአውሮፓ የኤኮኖሚ ምርምር ማዕከል ባልደረባ የሚሻኤል ሽሮደርም አስተያየት ነው።

“ከዚህ ቀውስ የተከሰተው በፊናንሱ ገበዮች ላይ የተፈጠረው ችግር ያስከተለው ጉዳት ወደፊት እስካሁን ከታሰበው በላይ ሊሆን እንደሚችል ነው። ገና ብዙ ሳይርቅ በሚቀጥሉት ወራት በተለይ በአሜሪካ የባንክ ዘርፍ ውስጥ ክስረት መታየቱን መገመት ይቻላል። ከሣምንታት በፊት የከፋው ችግር አልፏል ሲሉ አንዳንዶች ያሳዩት ተሥፋ፤ ይህ ተሥፋ አሁን ስህተትነቱን አስመስክሯል”

በአጠቃላይ የዓለም ኤኮኖሚ ከለየለት ቀውስ ላይ አይውደቅ እንጂ ቀውስ የማይደርስበት ነው ለማለት በጣሙን የሚያዳግት ነው። የአሜሪካ ባንኮች ቀውስ በቅርቡ መረጋጋት መያዙ ነበር የተነገረው። ግን ሰንበቱን የምንዛሪ ገበዮችን ያናጋው ክስረት የዕርጋታን ተሥፋ የሚያጠናክር አይደለም። ጥያቄው ነገ ከነገ ወዲያ ተከታዩ ባንክ ደግሞ የቱ ይሆን? የሚል ነው።