የአሜሪካ ኮንግረስ በኤች.አር. 128 ላይ ነገ ድምፅ ይሰጣል | ኢትዮጵያ | DW | 09.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአሜሪካ ኮንግረስ በኤች.አር. 128 ላይ ነገ ድምፅ ይሰጣል

የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኤች.አር 128 በተባለው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ላይ በነገው ዕለት ድምፅ ይሰጣሉ። የውሳኔ ሐሳቡ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ግድያዎች እንዲጣሩ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ እና አፋኝ የተባሉ ሕግጋት እንዲሻሩ ይጠይቃል። የውሳኔ ሐሳቡ አስገዳጅ ሕግ ባይሆንም እንኳ ጠንካራ መልዕክት ያስተላልፋል ተብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:40

ለመፅደቅ 2/3ኛ ድምፅ ማግኘት አለበት

የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ነገ ሚያዝያ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ኤች.አር. 128 በተባለው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ድምፅ ይሰጣሉ። 108 ተባባሪ አቅራቢዎች ያሉት የውሳኔ ሐሳቡ ከሚሰጠው ድምፅ 2/3ኛውን ካገኘ ይጸድቃል።

ክሪስቶፈር ሔንሪ ስሚዝ በተባሉ አሜሪካዊ ፖለቲከኛ ይፋ የተደረገው የውሳኔ ሐሳብ በኢትዮጵያ መንግሥት ተቺዎች ዘንድ ሰፊ ድጋፍ አግኝቷል። የኦሮሞ አራማጆች ጥምረት ለሰብዓዊ መብት እና ዴሞክራሲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሴና ጂምጂሞ በኮንግረስ ቀርበው ለውሳኔ ሐሳቡ ድጋፋቸውን ከገለጹ መካከል አንዷ ናቸው።

"የኢትዮጵያ መንግሥት በግድያ፣ በማፈናቀል እና በማሰቃየት ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ይጠይቃል። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች እንዲለቅ ይጠይቃል። በተለይ የኦሮሞ ሰዎች ለበርካታ አስርት አመታት ሲታሰሩ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሳ እና ዜጎች ሳይሸማቀቁ፤ ሳይታሰሩ በነፃነት መቃወም እና መናገር እንዲችሉም ሐሳብ አቅርቧል" ሲሉ ሴና የድጋፋቸው ምክንያት በኢትዮጵያ መመልከት የሚሹት በውሳኔ ሐሳቡ መካተቱ እንደሆነ ይናገራሉ።

ይኸው የውሳኔ ሐሳብ የሰላማዊ ተቃዋሚዎችን መገደል እና የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ከልክ ያለፈ የኃይል አጠቃቀም ይቃወማል። ሕገ-መንግሥታዊ የመሰብሰብ እና ሐሳብን በሰላማዊ ተቃውሞ የመግለፅ መብታቸውን በመጠቀማቸው ጋዜጠኞች፣ ተማሪዎች፣ አራማጆች እና ፖለቲከኞች መታሰራቸውንም ያወግዛል። ሲቪል ተቃውሞ እና የጋዜጠኞች መብትን ለማፈን የጸረ-ሽብር ሕጉ ግልጋሎት ላይ መዋሉንም ይኸው የውሳኔ ሐሳብ አጥብቆ ይተቻል። አቶ አምሳሉ ካሳው የውሳኔ ሐሳቡ ዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ጥብቅና በመቆሙ እንደሚደግፉት ይናገራሉ። የኢትዮ-አሜሪካ ሲቪክ ካውንስል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ አምሳሉ የአሜሪካ የሕግ ሥርዓት ውስብስብ ቢሆንም ይጸድቃል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።

በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ግድያዎች እና በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል በነበሩ ተቃውሞዎች የጸጥታ አስከባሪዎች የኃይል አጠቃቀም እንዲመረመር ጥሪ አቅርቧል። የመሰብሰብ እና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት እንዲከበር፤ ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀማቸው የታሰሩ ተቃዋሚዎች፣ አራማጆች፣ እና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፤ መንግሥት ስለሚከተለው የልማት ሥልት በግልፅ ከዜጎች ጋር እንዲማከርም አሳስቧል።

የሒውማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ አጥኚው ፌሊክስ ሆርን እነዚህ ሐሳቦች አዲስ አልሆኑባቸውም ። ሒውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተመሳሳይ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል። በኢትዮጵያ በተፈጸሙ ግድያዎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ የሆኑ ለሕግ ሳይቀርቡ መቆየታቸውን የሚያስታውሱት ፌሊክስ ሆርን የኢትዮጵያ መንግሥት አጋሮችም ዝምታን መርጠው ቆይተዋል ሲሉ ይተቻሉ።  

"የውሳኔ ሐሳብ 128 ለኢትዮጵያ መንግሥት ከአጋሮቹ መካከል አንዷ የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ ደስተኛ አለመሆኗን የሚጠቁም ጠንካራ መልዕክት የሚያስተላልፍ በመሆኑ እጅግ ጠቃሚ ነው። በውሳኔ ሐሳቡ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ምን ያክል ጠንካራ እንደሆኑ የሚገልጹ በርካታ ነገሮች ቢካተቱም በርካታ ትችቶች እና በማሻሻያዎች ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊወስዳቸው ይገባል የተባሉ የእርምጃ ጥያቄዎች ይገኙበታል"

የውሳኔ ሐሳቡ ድምፅ ይሰጥበታል የተባለው ባለፈው አመት ቢሆንም በግልፅ ባልታወቀ ምክንያት እንዲዛወር ተደርጓል። የውሳኔ ሐሳቡ ደጋፊዎች እንደሚሉት ረቂቁ ድምፅ ሳይሰጥበት የቀረው የኢትዮጵያ መንግሥት ባሳደረው ጫና ምክንያት ነው። ማይክ ኮፍማን የተባሉ አሜሪካዊ የሕግ-መወሰኛ ምክር ቤት አባል በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ድምፅ ከተሰጠ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያለውን የጸጥታ ሥምምነት አቋርጣለሁ ብሏል ሲሉ ተናግረው ነበር።  የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን ከመፍታት እና ዴሞክራሲያዊ አገር ከመመስረት ይልቅ በወር 150,000 ዶላር እየከፈለ የውሳኔ ሐሳቡ ድምፅ እንዳይሰጥበት የሚወተውት ድርጅት ቀጥሯል ሲሉ ማይክ ኮፍማን ወቅሰዋል።

አቶ አምሳሉ ካሳው እንደሚሉት የውሳኔ ሐሳቡ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ማሻሻያ ተደርጎበታል። ማሻሻያው "አዲሱ ጠቅላይ ምኒስትር በኢትዮጵያ ያለውን የሕዝብ ጩኸት እንዲሰሙ እና ያንንም ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ" እንደሆነ አቶ አምሳሉ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ይዞታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚሾመው ገለልተኛ ወገን እንዲመረመር ኤች.አር. 128 ጥሪ አቅርቧል። ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያቀረበውን ተመሳሳይ ጥያቄ ኢትዮጵያ ውድቅ ማድረጓ አይዘነጋም። ኤች አር 128 በኢትዮጵያ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚያቀርቡት አቤቱታ መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥም ይሻል። በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የደረሰው የእሳት ቃጠሎ እና የነበረው ተኩስ እንዲሁም በቢሾፍቱ ከተማ የኢሬቻ በዓልን በመታደም ላይ ሳሉ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች አሟሟት፣ በሶማሌ ክልል በፖሊስ የተፈጸሙ ግድያዎች እንዲጣሩ ሐሳብ አቅርቧል።

ዜጎችን ለማሸማቀቅ የሚያገለግሉ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚመረምሩ ተቋማትን በገንዘብ ከመደገፍ የሚከለክሉ፣ በሰላማዊ ፖለቲካዊ ተቃውሞ መሳተፍን፤ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች ጥያቄን የሚያግዱ ህግጋት እንዲሻሩ የኢትዮጵያ መንግሥትን ጠይቋል። 

ነገ ድምፅ የሚሰጥበት የውሳኔ ሐሳብ ለአሜሪካ መንግሥት ያቀረባቸው ሐሳቦችም አሉ። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለኢትዮጵያ የሚደረገውን የጸጥታ ድጋፍ እንዲመረምር ጠይቋል። የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ እና የአገሪቱ ግምጃ ቤት በዘፈቀደ ግድያዎች፤ ሥቅየት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ እውቅና በተሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች ላይ ለተፈጸሙ ጥሰቶች ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉ ጥሪ አቅርቧል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

 

 

Audios and videos on the topic