የአሜሪካ ምርጫና የዕጩዎችዋ የዉጪ መርሕ | ዓለም | DW | 07.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአሜሪካ ምርጫና የዕጩዎችዋ የዉጪ መርሕ

የዓለም ትልቅ፤ ሐብታም፤ሐያሊቱ ሐገር ዕጩዎችዋን አወዳድራለች።ነገ ዜጎችዋን ታስመርጣላቸዉ።በእርግጥ ብዙዎችን ማራኪ፤ ተፈላጊዉ ሰዉ የለም።ግን አሜሪካዉያን ሰወስት ምርጫ አላቸዉ።ምርጫ አንድ ሰዉዬዉ፤ ምርጫ ሁለት ሴትዮዋ።ምርጫ ሰወስት አለመምረጥ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:27
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:27 ደቂቃ

የአሜሪካ ምርጫና የዕጩዎችዋ የዉጪ መርሕ

ሰዉዬዉ። በቅርብ የሚያዉቋቸዉ የተዋጣላቸዉ ነጋዴ፤ አሻሻጭ፤ አስተዋዋቂ፤ቁጡ፤መርሕየለሽ፤ ሴረኛ፤ ያልተገሩ፤ ግን ግርማ-ሞገስ ያላቸዉ ይሏቸዋል።ሥለዉጪ መርሐቸዉ እንዲሕ ማለታቸዉን እኛም እናዉቃለን።«ትልቅ ግንብ እገነባለሁ።ከኔ የተሻለ መገንባት የሚችል ሰዉ አይኖርም።እመኑኝ።»ሴትዮዋ።ጠንካራ ሠራተኛ፤በሌሎች የምትመራ፤ ግን የማትበገር፤ዘመናይ ደግሞ በተቃራኒዉ ወግ አጥባቂ፤ ተወዳጅ ግን ለፕሬዝደትነት የማይመቹ ይሏቸዋል።«ግንብ አንገነባም።ከዚሕ በተቃራኒዉ የሚፈልግ በሙሉ ሥራ የሚያገኝበት ምጣኔ ሐብት እንገነባለን።» ሰዉዬዉ ወይስ ሴትዮዋ። አሜሪካኖች ነገ ይበይናሉ። 

 

ቀዳማዊት እመቤት፤ ሴናተር፤ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርም ነበሩ።ሒላሪ ዲያነ ሮድሐም ክሊንተን።የሥልሳ ዘጠኝ ዓመት ወይዘሮ ናቸዉ።የአንዲት ልጅ እናት።«እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር፤ ሴናተርና ቀዳማዊት እመቤት አሜሪካንን በዉጪ የመወከል እና የዉጪ መርሕዋን ቅርፅ የማስያዝ ክብር አጋጥሞኝ ነበር።»ባለቤታቸዉ ከፊትም ከኋላም ነበሩ-አሉላቸዉም፤-የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን።ፕሬዝደንት ባራክ ኦባም እንደ ፖለቲካ መርሕ ተጋሪ፤ እንደተቀናቃኝ፤ እንደ አለቃም አስተማሪ፤መካሪ፤ ደጋፊያቸዉም ናቸዉ።ግን፤ የሕይወት ታሪክ ፀሐፊያቸዉ ካሬን ብሉሜንታል እንደሚሉት የባለቤታቸዉንም ሆነ የኦባማን አይነት ማራኪና ተወዳጅ ግርማ ሞገስ የላቸዉም።

                                

«የባለቤታቸዉን የቢል ክሊንተንንም ሆነ የባራክ ኦባማን አይነት አጓጊ ግርማ ሞገሳዊ አቀራረብ የላቸዉም።ጎረቤትሕ

እንዲሆኑ የምትፈልጋቸዉ አይነት ሴት ናቸዉ።እኛ አሜሪካዉያን ግን እንዲሕ አይነቱ ሰዉ ይሰለቸናል።እና አሰልቺ ዓይነት ሴትዮ ናቸዉ።»

ሰዉዬዉ።ነጋዴ፤የቴሌቪዥን ትርኢት አስተዋዋቂ፤ የኩባንዮች ባለቤት፤ የናጠጡ ቱጃር፤ ቢሊየነር  ናቸዉ።ዶናልድ ጆን ትራምፕ።ሰባ ዓመታቸዉ።የአምስት ልጆች አባት።ሥለ እሳቸዉ እና ሥለ ቤተሰባቸዉ ሁለት መፅሐፍት ያሳተሙት ግዌንዳ ብሌር «አሻሻጭ» ይሏቸዋል።«አሻሻጭ (አስተዋዋቂ) ናቸዉ።እራሳቸዉን በደንብ ያስተዋዉቃሉ።በራሳቸዉ በጣም ያምናሉ።እንዲያዉ አልፎ አልፎ የሆነ ሰዉ፤ የሰሩት ሥራ የተሳካ አይደለም ቢላቸዉ፤ የተጠቁ ይመስላቸዋል።ባስተያየቱ መረበሻቸዉ በግልፅ ይታይባቸዋል።እና ሐሳቡን ያጣጥሉታል።ከኔ በላይ የሚል መጥፎ በሽታ አለባቸዉ።»

ሌሎችን ለማጣጣል፤ ለማበሻቀጥ፤ አልፎ ተርፎ ለመዝርጠጥ ግን አያመነቱም።ያለፈዉ ሰባት ወር ዋና ኢላማቸዉ ያዉ-ሴትዮዋ ናቸዉ።«ሊቢያ ዉስጥ፤ አሜሪካ በመላዉ ዓለም ያላት ከብር ምልክት የሆነዉ ቆንስላዋ ጋይቷል።አሜሪካ ከበፊቱ ይበልጥ ለጥቃት ተጋልጣለች።ዓለም ከድሮዉ ይበልጥ ያልተረጋጋች ሆናለች።ኦባማ፤ ክሊንተንን የአሜሪካ የዉጪ መርeሕ  ሐላፊ በማድረጋቸዉ ምክንያት። ሕዳር ላይ እናሸንፋቸዉ።»

የኦባማን ይሁን ቀዳሚዎቹን የዴሞክራቲክ ፓርቲ መስተዳድሮችን ወይም ባለሥልጣናትን አጥብቀዉ ይተቻሉ፤ በተደጋጋሚ ይወቅሳሉ።ሥለራሳቸዉ መርሕ በተለይ ሥለዉጪ መርሐቸዉ በግልፅ ያሳወቁት ግን ዉስን ነዉ።ሙስሊሞች ነጋዴ ሆኑ ስደተኛ፤ ምሁር ሆኑ ማይም ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ማገድ፤ ስደተኛ ከሩቅ ይምጣ ከቅርብ፤ ሙስሊም ይሁን ክርስቲያን አሜሪካንን እንዳይረግጥ ግንብ ማሳጠር።አይሲስን መዉጋት።ጦራቸዉን ማጠናከር።

                 

«ደቡባዊ

ድንበራችን ላይ ትልቅ፤ በጣም ትልቅ ግንብ አስገነባለሁ።ወጪዉን ደግሞ ሜክሲኮን አስከፍላታለሁ።ቃሌን እንዳትረሱ።ISIS ላይ ከዶናልድ ትራምፕ የተሻለ ጠንካራ እርምጃ የሚወስድ የለም።ጦራችን ዉስጥ ጄኔራል ፓተንን ወይም መገርታን የመሰሉ፤ ጦራችን በትክክል እንዲሰራ የሚያደርጉ መኮንኖችን እፈልጋለሁ።ማንም ሐይል ሊነቀንቀን አይችልም።»

«ሰዉዬዉ እኮ እድሜያቸዉ እንጂ አዕምሯቸዉ ብዙ አላደገም ይላሉ ቲሞቲ ኤል ኦ ብሬይን።«ትራፕ ኔሽን» የሚል መፅሐፍ አሳትመዋል።የዶናልድ ትራምን የሕይወት ታሪክ የሚተርክ ነዉ።

                                  

«በመሠረቱ በጣም ያረጀ ግን የሰባት ዓመት ልጅ ነዉ።አንድ ለአንድ መነጋገር ይችሉ ይሆናል።ግን በጣም ሥርዓት የሌላቸዉ ሰዉ

ናቸዉ።በአስተሳሰብ፤በስሜት፤ በገንዘብ አያያዝ ይሁን በአደባባይ ቅጥ የለሽ ናቸዉ።ሲበዛ «ከኔ ሌላ» ባይ ናቸዉ።በየትኛዉም የሕይወት መስክ ቢሆን ለሳቸዉ፤ተፈላጊዉ እራሳቸዉ ብቻ ነዉ።»

እስከ ዛሬ የተሰባሰበዉ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያመለክተዉ ትራምፕ የክሊንተንን ያሕል ድጋፍ የላቸዉም። ግን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ደጋፊ አላቸዉ።የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ልምድ ያላቸዉን «ብልጥ እና ብልሕ» የሚባሉ የሪፐብሊካን ፖለቲከኞችን ተራ በተራ እየጣሉ ለነገዉ ምርጫ የደረሱትም በአድናቂ ደጋፊዎቻቸዉ ብዛት ነዉ።

ፕሬዝደንት ኦባማ ባንድ ወቅት «ትራምፕ ይመረጣሉ ብለዉ ያስባሉ?» ተብለዉ ሲጠየቁ «የምርጫ በፊት አስተያየት-ትክክል ቢሆን ኖሮ እኔ አልመረጥም ነበር» ብለዉ ነበር የመለሱት።አሜሪካ ሁሉም ነገር የሚሆንባት ሐገር ናት።ትራምፕም ያሸነፉ ይሆናል።ካሸነፉ የዉጪ መርሐቸዉ በዲፕሎማሲዉ መስክ እንዲሕ ይሆናል አሉ።

                       

«ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት አስቆማታለሁ።ሥለድርድር ምንም ነገር የማያዉቁትን መጥፎ እና አስቂኝ ስምምነት የሚያደርጉት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ኬሪን አይነት ሰዉ የዉጪ መርሐችን ሐላፊ አይሆንም።እነሱ የጦር መሳሪያ ሲሰሩ፤ በሰባ ሁለት ዓመቱ የብስክሌት ዉድድር ሲያደረግ ወድቆ እግሩን የሚሰበር ሰዉ በፍፁም (ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር) አላደርግም።በጭራሽ ብስክሌት አልወዳደርም።ይሕን እነግራችኋለሁ።»

ትራምፕ ኢራኖች የኑክሌር ቦምብ እንዳይኖራቸዉ በዉድም በግድም አግዳለሁ ባይ ናቸዉ።ተቀናቃኛቸዉ ሒላሪ ክሊንተን ግን ዶናልድ ትራምፕ ራሳቸዉ የአሜሪካን የኑክሌር ቦምብ ቁልፍ መያዝ የለባቸዉም ይላሉ።ለሐላፊነት ብቁ አይደሉም።«አሜሪካኖች ሕዳር ላይ የሚመርጡት ፕሬዝደንት ብቻ አይደለም።ከጦርነት እና ሰላም፤ ከሕይወትና ሞት አንዱን የሚወስን የጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥም ጭመር ነዉ የምንመርጠዉ።በሐገራችን እና በመላዉ ዓለም እንደሚገኙት እንደ አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉ ሪፐብሊካኖች ለፕሬዝደትነት ያጩዋቸዉ ሰዉ ሐላፊነቱን መወጣት አይችሉም ብዬ አምናለሁ።»

ክሊንተን  ሴናተር በነበሩበት ወቅት ፕሬዝደንት ቡሽ ኢራቅን የሚወር ጦር ማዝመታቸዉን ደግፈዉ ድምፅ ሰጥተዋል።ዩናይትድ ስቴትስን ከሜክሲኮ ጋር የሚያገናኘዉ ድንበር በግንብ መታጠሩን ይቃወማሉ።ግን ድንበሩ በሽቦ አጥር መታጠሩን ደግፈዋል።ታጥሯልም።

የዉጪ መርሐቸዉን ያዩ እንደሚሉት ከዶናልድ ትራምፕ ይበልጥ በግልፅ ተዘርዝሯል።ግን እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ካስፈፀሙት ብዙም የተለየ አይደለም።

                              

«እንደ ዕጩ ፕሬዝደንት ከሐገራችን ብሔራዊ ደሕንነት የበለጠ ትኩረት የምሰጠዉ ነገር የለም።ISISን እንዴት እንደምናሸንፈዉ ግልፅ ስትራቴጂ ነድፌያለሁ።ከወዳጆቻችን ጋር ያለንን ትብብር የሚያጠናክር፤ ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳታገኝ የሚያግድ ስልት ቀይሻለሁ።በዚሕ የምርጫ ዘመቻም የአሜሪካ ደሕንነት ዋናዉ ጉዳዬ ነዉ።»

ሴትዮዋ የሚያዉቋቸዉ

እንደሚሉት ለዘብተኛ ናቸዉ።ተግባቢ።ከሁለቱም በላይ የዴሞክራቲኩ ፓርቲ ዕጩ-ዴሞክራት ናቸዉ።የሕይወት ታሪክ ፀሐፊያቸዉ ጄምስ ዴ ቦይስ ግን ሴትዮዋ ብዙዎች ከሚያዉቋቸዉ በተቃራኒዉ ወግ አጥባቂ ናቸዉ።The Nation የተሰኘዉ መፅሔት ቋሚ ፀሐፊ ሪቻርድ ክሬይትነርም የቦይስን አስተያየት ይጋራሉ።ግን ክሊንተን ጠንካራ ሰራተኛም ናቸዉ ይላሉ።አሜሪካኖችን ታታሪ ሰዉ ይወዳሉ።ግን---«አሜሪካኖች ጠንካራ ሠራተኞችን እና አይበገሬዎችን ይወዳሉ።እና እሳቸዉንም ሊያደንቋቸዉ ይችላሉ።ፕሬዝደንታቸዉ እንድትሆን ግን ይፈልጋሉ ማለት አይደለም።»

የቢል ክሊንተንን እና የትልቁ ጆርጅ  ቡሽን፤ የጆርጅ ቡሽ ትንሹን እና የአል ጎርን፤ የኦባማንና የመኬይንን የምርጫ ዘመቻ፤ ፉክክር እና ክርክርን ያየ የክሊንተን፤ ትራምፕን ፉክክርን፤ ከአሜሪካዉያን ዕጩ ፕሬዝደንቶች ፉክክር መቁጠሩ አጠራጣሪ ነዉ።ግን እዉነት ነዉ።የዓለም ትልቅ፤ ሐብታም፤ሐያሊቱ ሐገር ዕጩዎችዋን አወዳድራለች።ነገ ዜጎችዋን ታስመርጣላቸዉ።በእርግጥ ብዙዎችን ማራኪ፤ ተፈላጊዉ ሰዉ የለም።ግን አሜሪካዉያን ሰወስት ምርጫ አላቸዉ።ምርጫ አንድ ሰዉዬዉ፤ ምርጫ ሁለት ሴትዮዋ። ምርጫ ሰወስት አለመምረጥ። ቸር ያሰማን!

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

                  

 

Audios and videos on the topic