የአሜሪካ መሪዎችና አፍሪቃ፧ | አፍሪቃ | DW | 18.02.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአሜሪካ መሪዎችና አፍሪቃ፧

የዩናይትድ እስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደ. ቡሽ፧ በ 5 የአፍሪቃ አገሮች የሚያደርጉትን ጉብኝት ከትናንት በስቲያ በቤኒን ከጀመሩ በኋላ፧ ወደ ታንዛንያ ጎራ በማለት አሩሻ ውስጥ ከአስታናጋጂአቸው ጃካያ ኪክዌቴ ጋራ በጋራና ዐበይት አፍሪቃ አቀፍ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ ተለዋውጠዋል።

ቡሽና ኪክዌቴ፧ በዳሬሰላም ቤተ-መንግሥት፧

ቡሽና ኪክዌቴ፧ በዳሬሰላም ቤተ-መንግሥት፧


ቡሽ፧ ውዝግብ የሚንጣቸውን አገሮች ሳይሆን፧ በኤኮኖሚ እያገገሙ፧ በዴሞክራሲ ግንባታም ማለፊያ ስም እያተረፉ በመገኘት ላይ ያሉትን የአፍሪቃ አገሮች ነው ለመመልከት የመረጡት። እነርሱም ቤኒን፧ ታንዛንያ፧ ሩዋንዳ፧ ጋናና ላይቤሪያ ናቸው። ተጭበርብሯል በተባለ ምርጫ፧ ከታህሳስ 17 ቀን 2000 ዓ ም አንስቶ በውዝግብ ላይ ለቆየችው ሀገር፧ ለኬንያ፧ መፍትኄ በማፈላለግ ረገድ፧ ሸምጋዩን የቀድሞውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ ኮፊ አናንን ያግዙ ዘንድ፧ ቡሽ ውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸውን ኮንዶሊሣ ራይስን ወደ ናይሮቢ ልከዋቸዋል«ኬንያ አሳሳቢ ርእሰ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ራይስ የኮፊ አናንን የሽምግልና ጥረት ታግዝ ዘንድ የምልካት። የሽምግልናው አጠቃላይ ግልጽ መልእክት ሁከት እንዲወገድና የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት እንዲደረግ ነው። ይህ በጣም ሰፊና ብዙ ብሔረሰቦች ያሉበት ሀገር ነው። ሁሉም ነገር ፍጹም የተሟላ አለመሆኑ ደግሞ አጠያያቂ አይደለም።«
ቡሽ ወደ አፍሪቃ ያመሩት የሥልጣን ዘመናቸው ሊያከትም አንድ ዓመት ገደማ እንደቀረው ሲሆን የጉብኝታቸው ዓላማም፧ አሜሪካ ከአፍሪቃ ጋር የሚያስተሣሥር ወዳጅነት ያላት መሆኑን ለማሳየት ነው። የአሜሪካ መርኅ በአፍሪቃ የሠመረበትን ሁኔታ የሚያሳየው አንዱ፧ የዶቸ ቨለ ባልደረባ Frank Räther እንዳለው ታንዛንያ፧ የሦስት ሺኛውን ዓምአት የተባበሩት መንግሥታት የልማት ግብ እውን ለማድረግ፧ ከአሜሪካ 700 ሚልዮን ዶላር እርዳታ የምታገኝበት ውል መፈረሙ ነው። ገንዘቡ ድኅነትን ለመታገል ይውላል ነው የተባለው። እርዳታውን አስታከው፧ የታንዛንያው ፕሬዚዳንት ጃካያ ኪክዌቴ፧ ስለቡሽና አስተዳደራቸው እንዲህ ነበረ ያሉት።
«የተለያዩ ሰዎች፧ ስለእርስዎ፧ ስለአስተዳደርዎና ስለሚተውት ቅርስ፧ የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል። እርስዎ፧ የተከበሩ ፕሬዚዳንትና አስተዳደርዎ የአገራችን፧ በአጠቃላይም የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ጥሩ ወዳጆች ሆናችሁ ዘልቃችኋል።«
አንድ አሜሪካዊ የፖለቲካ ምሁር እንዳተቱት፧ አሜሪካ አፍሪቃ ውስጥ በአውሮፓው ኅብረትና በቻይና በመቀደሟ፧ አሁን ገሸሽ እንዳላለች ማሥመሥከር ትሻለች። ከአፍሪቃ ነዳጅ ዘይት ማግኘት አንዱ የአሜሪካ ዐቢይ ትኩረት ሲሆን፧ አሁን ካለው የነዳጅ ዘይት አቅርቦት፧ እ ጎ አ እስከ 2015 ዓ ም፧ ከ 18 ከመቶ፧ ወደ 25 ከመቶ ከፍ የማድረግ እቅድ ነው ያላት። አሜሪካ፧ አፍሪቃ ውስጥ 80% ገንዘብ ሥራ ላይ የምታውለው፧ ከነዳጅ ዘይት ጋር በተያያዘ ሁኔታ ነው። በዚህ ረገድ ከቻይና ጋር ብርቱ ፉክክር መደረጉ የማይቀር ነው። ቻይና፧ በአሁኑ ጊዜ የነዳጅ ዘይት ጥማቷን የምታረካው አፍሪቃ ውስጥ ነው። ቻይና፧ በከፍተኛ ደረጃ መሪዎቿ በያመቱ ወደ አፍሪቃ ብቅ ይላሉ። አፍሪቃውያን መሪዎችንም ትጋብዛለች፧ በመሆኑም ብዙዎቹ የአፍሪቃ አገሮች ከቻይና ጋር የጠበቀ ጥብብር በማድረግ ላይ ናቸው። የአሜሪካ መሪ ግን በ 5 ዓመት ገደማ አንድ ጊዜ ነው ወደ አፍሪቃ ብቅ የሚለው። ከቻይና፧ የልማት እርዳታ በገፍ ሲቀርብ፧ ከአሜሪካ፧ በጥቂቱ ነው የሚንጠባጠበው። በጥቂት መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ! እርሱም በአመዛኙ ለ HIV/AIDS መከላከያ እየተባለ ነው የሚሰጠው። ስለሆነም የአሜሪካ ተሳትፎ ያን ያህል ያላረካቸው ብዙዎች የአፍሪቃ አገሮች፧ አሁን ዋና ማዕከሉን እሽቱትጋርት ጀርመን ላይ ያደረገው፧ Africom የተባለው የአሜሪካ ተወርዋሪ ጦር ኃይል፧ በግዛታቸው እንዲሠፍር አይፈልጉም። አሜሪካ፧ የነዳጅ ዘይት አቅርቦትን ለማረጋገጥ፧ እንዲሁም በሳሔል ቀበሌና በምሥራቅ አፍሪቃ እሥላማዊ አሸባሪነት የምትለውን ለመታገል ነው፧ አፍሪቃ ውስጥ ተሥፈንጣሪ ጦር ለማሥፈር የምትፈልገው።
በፖለቲካው ረገድ፧ አሜሪካ መልሕቅ የሚጠልባቸው ወይም ጎላ ብለው የሚታዩ አገሮች ለምትላቸው ነው፧ ላቅ ያለ ትኩረት የምትሰጠው። እነርሱም፧ በደቡብ፧ ደቡብ አፍሪቃ፧ በምሥራቅ አፍሪቃ ኢትዮጵያና ኬንያ፧ በምዕራብ ፧ ናይጀሪያና ጋና ናቸው። ፈረንሳይና ፖርቱጋልኛ ተናጋሪ ለሆኑት ስልታዊ አቀማመጥ ላቸው ሌሎቹ አገሮች ማለትም፧ ሴኔጋል፧ ሞሮኮ፧ ኮንጎና አንጎላ ደንታ ያላት አልመሰለችም። በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ካርታ ውስጥ እንዳሉ ያልተቆጠሩት አገሮች ደግሞ፧ ጥቂቶች አይደሉም። ምንም እንኳ፧ ከሰሞኑ፧ ፕሬዚዳንት ቡሽ 5 የአፍሪቃ አገሮችን ለመጎብኘት ቢሠማሩም፧ አገራቸው፧ በውል የተያዘ አፍሪቃ አቀፍ የፖለቲካ መርኀ አላት ለማለት የሚያስደፍር አይደለም።