የአሜሪካን ኤምባሲ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተቃወመ | ኢትዮጵያ | DW | 17.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአሜሪካን ኤምባሲ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተቃወመ

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ የሚንስትሮች ምክር ቤት የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተቃወመ። የኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ ማሽቆልቆል ያሳሰባቸው የካናዳ፣ የስዊድን፣ የሩሲያ እና የአየርላንድ ኤምባሲዎችም ለዜጎቻቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ የኢትዮጵያ የሚንስትሮች ምክር ቤት የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተቃወመ። አዲስ አበባ የሚገኘው ኤምባሲ በድረ-ገፁ ባወጣው ሐተታ "የኢትዮጵያ መንግሥት የመሰብሰብ እና ሐሳብ መግለጽን ጨምሮ መሰረታዊ መብቶች የሚገድብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ የደረሰበትን ውሳኔ በብርቱ አንስማማበትም" ብሏል።

የኢትዮጵያ የምኒስትሮች ምክር ቤት የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስፈፅመው ኮማንድ ፖስት ርምጃ ይወስድባቸዋል ተብለው ከተዘረዘሩ ድርጊቶች መካከል "የአደባባይ ሰልፍና ሰልፍ ማድረግ፣ መደራጀት እንዲሁም በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስ" ይገኙበታል። የኢትዮጵያ የመከላከያ ምኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ሕገ-መንግሥቱን እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለአደጋ የሚያጋልጡ የኹከት የብጥብጥ ተግባራት" መከሰታቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለመደንገግ እንዳስገደዱ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት የተጠቀሰው የኹከት ክስተቶች እና የዜጎች ሞት ሥጋትን እንገነዘባለን፤ እንጋራዋለንም ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ "መፍትሔው ከፍ ያለ ነፃነት እንጂ ከዛ ያነሰ ላለመሆኑ በጽኑ እናምናለን" ሲል አትቷል።

ኢትዮጵያ የገጠሟት ዴሞክራሲያዊ ማሻሻያ የማድረግ፣ የኤኮኖሚያዊ እድገት እና ዘላቂ መረጋጋት የመፍጠር ፈተናዎች ገደብ ከመጣል ይልቅ በአካታች ውይይት እና ፖለቲካዊ ሒደት መፍትሔ ቢፈለግላቸው እንደሚሻል ኤምባሲው ጠቁሟል።  

Äthiopien Siraj Fegesa

የኢትዮጵያ መከላከያ ምኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገግ አካታች ፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን መፍታትን ጨምሮ በቅርቡ የታዩ አወንታዊ ለውጦችን እንደሚያንኳስስ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል።

"ኢትዮጵያውያን ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ መብታቸው ላይ የሚደረግ ገደብ ሰሚ ማጣታቸውን የሚጠቁም መልዕክት ያስተላልፋል" ሲል ኤምባሲው ሥጋቱን ገልጿል። መንግሥት ውሳኔውን መለስ ብሎ እንዲመለከት በጥብቅ ያሳሰበው መግለጫው የዜጎችን ሕይወት እና ንብረት ለመጠበቅ ትርጉም ላለው ውይይት የሚያስፈልገውን ምኅዳር እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚያሰፋ እና የሚያረጋግጥ ለዘላቂ ዴሞክራሲ መንገድ የሚጠርግ ሌላ ሥልት እንዲያፈላልግ መክሯል።

የኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ ማሽቆልቆል ያሳሰባቸው የካናዳ፣ የስዊድን፣ የሩሲያ እና የአየርላንድ ኤምባሲዎች ለዜጎቻቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ የአገሪቱ ዜጎች ኢትዮጵያን ከመጎብኘት እንዲታቀቡ መክሯል። ኢትዮጵያ በገጠማት ፖለቲካዊ ምሥቅልቅል ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጓን ያስታወሰው የኤምባሲው ማስጠንቀቂያ ከአዲስ አበባ ውጪ መጓዝ አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ገልጿል።

የስዊድን ዜጎች ሰዎች ከሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች እንዲርቁ፣ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና በየአካባቢው ከሚገኙ መገናኛ ብዙኃን መረጃ እንዲያሰባስቡ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው ኤምባሲ መክሯል። የካናዳ ኤምባሲ በበኩሉ በኢትዮጵያ በሚታየው "ተለዋዋጭ የጸጥታ ሁኔታ" ምክንያት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ አትቷል። የአየርላንድ ኤምባሲ የኢትዮጵያን የጸጥታ ሁኔታ "ከፍተኛ ጥንቃቄ" ከሚሹት ጎራ መድቦታል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ