የአሜሪካን ተምች በአፍሪቃ | ጤና እና አካባቢ | DW | 02.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የአሜሪካን ተምች በአፍሪቃ

በእንግሊዝኛዉ ስያሜዉ አርሚዎርም የሚል መጠሪያ ያለዉ የተምች ዘር ስያሜዉን ያገኘዉ በተናጠል ሳይሆን በኅብረት ሆኖ ሲንቀሳቀስ በመንገዱ ያገኘዉን ማንኛዉንም የተክል ዘር እያወደመ ስለሚጓዝ መሆኑን አንዳንድ የትርጉም ማብራሪያዎች ይጠቁማሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:41

የበቆሎ ጠር የሆነዉ የተምች መንጋ

የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ይፋ ባደረገዉ መረጃ መሠረት ይህ ተክል አዉዳሚ በተለያዩ የደቡብ፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ የአፍሪቃ ሃገራት እየተዛመተ እንደሚገኝ ማሳሰቡን ቀጥሏል። በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የእጸዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዴዎስ ሰላቶ፤ ከሀገር ሀገር እየተዛመተ ስለሚገኘዉ ፀረ ሰብል ትል ምንነት ይናገራሉ።

ለጊዜዉ ሀገራዊ መጠሪያ ያልተሰጠበትም ምክንያት አላቸዉ፤ ቀደም ሲል የሚታወቅ መደበኛ ተምች በመኖሩ ከዚህ ከአዲስ መጤዉ ጋር ልዩነትም ሆነ አንድነት ስላላቸዉ አርሶ አደሩም ሆነ ሌሎች አካላት ግር እንዳይሰኙ፤ ተገቢዉ መረጃ እና ስልጠና እስኪሰጥ በሚል መቆየቱን አብራርተዋል። ሁለቱም ሰብል አዉዳሚ የተምች ዘሮች በበልግ ዝናብ ወቅት እንደሚከሰቱ ነዉ ባለሙያዉ ያብራሩልን። ይህ አዲስ መጤዉ የአሜሪካን ተምች በእድገት ሂደቱ ወደ በራሪ የእሳት እራትነት ይሻገራል።

 የአንጎላ መንግሥት በሀገሪቱ ከፍተኛ በቆሎ አምራች በሆኑ አራት አካባቢዎች ይህ ፀረ ሰብል የሆነዉ ትል መዛመቱን፤ በአምስተኛዉ ግዛቱ ደግሞ የበቆሎ ግንድ በመቦርቦር የሚታወቅ ሌላ ፀረ ሰብል ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝም አስታዉቋል። አንጎላ ዉስጥ ብቻም ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ የበቆሎ፣ የአጃ እና የማሽላ ሰብል የወደመ ሲሆን፤ የደረሰዉ ጉዳት በገንዘብ ሲተመን ወደ 1,8 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ተገምቷል። በዚህ ፀረ ሰብል የትል መንጋ ምክንያትም በአብዛኛዉ በአነስተኛ እና መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ገበሬዎች መጎዳታቸዉ ነዉ የተነገረዉ። አቶ ዘብዴዎስ ፤ ጉዳት እንዳይደርስ እየተደረገ ነዉ ያሉትን እንዲህ ገልጸዋል።

መነሻዉ በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ ዉስጥ እንደሆነዉ የሚነገረዉ ይህ የትል መንጋ ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2016 ነዉ ለመጀመሪያ ጊዜ ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ የታየዉ። ቀስ በቀስ ከሰሃራ በስተደቡብ ወደሚገኙ ሃገራት በቆሎ እና ሌሎች የሰብል ምርቶችን እያወደመ መስፋፋቱ ተመልክቷል። በተለይ ደግሞ በኤሊንኞ ክስተት ምክንያት በድርቅ የተጠቃዉ ደቡባዊ አፍሪቃ ሚሊዮኖች የምግብ ርዳታ ፈላጊዎች ሆነዉ ሳለ፤ የዚህ ሰብል አዉዳሚ ትል መዛመት ችግሩን በማባባስ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል አስግቷል።

ምንም እንኳን በዚህ ዓመት የዝናቡ ሁኔታ የተሻለ በመሆኑ ጥሩ ምርት እንደሚታፈስ ተስፋ ቢደረግም ሰብልን በቁሙ የሚያወድመዉ ትል መስፋፋት እንዳሰጋት እና ወረርሽኙም እንደተከሰተባት አንጎላ አሳዉቃለች። የዚህ የመጤ ተምች ወረርሽኝ እንደተከሰተባቸዉ የገለጹ ሃገራት የእርሻ ምርታቸዉን ለዉጭ ንግድ ማቅረብ እንዳልቻሉም ተነግሯል።

አሁን ባለዉ የቅርብ ጊዜ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ዉስጥ ይህ አዲስ መጤ የተምች ዘር የተከሰተበት አካባቢ በቆሎ ከተዘራዉ ወደ 1 መቶ ሰባሺ ህ ሄክታር መሩት 10 በመቶዉን እንኳ እንዳላዳረሰ ነዉ አቶ ዘብዴዎስ ሰላቶ የገለጹልን። በዚህም ምክንያት እንደነአንጎላ የተምች ወረርሽኝ ተከስቷል ማለት እንደማይቻልም አመልክተዋል። ተምቹ በሌሎች ሃገራት ላይ ያደረሰዉ ችግርም ለኢትዮጵያ መነሻ በመሆኑ ፈጣን ጥንቃቄ ለመዉሰድ ረድቶናልም ባይናቸዉ። ይህ የተምች ዘር ርጥበትና ሞቃታማነት ባላቸዉ አካባቢዎች እንደሚራባ እና ያንን የአየር ጠባይ እንደሚፈልግም አመልክተዋል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

 

 

 

 

Audios and videos on the topic