የአሜሪካንና የጀርመን የስለላ ቅሌትና ተፅእኖው | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 15.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የአሜሪካንና የጀርመን የስለላ ቅሌትና ተፅእኖው

ዩናይትድ ስቴትስ ሁለት የጀርመን መንግሥት ሠራተኞችን ለስለላ መመልመሏ ከተደረሰበት በኋላ በበርሊን የአሜሪካን ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት CIA ተጠሪ ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ጀርመን መጠየቋ በሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ጥላ አጥልቷል። የጀርመን መንግሥት ፖለቲከኞች ጀርመንም ለአፀፋ ስለላ እድትዘጋጅ እየጠየቁ ነው።

አሜሪካውያን የነፃነት ቀን እዚህ ጀርመን የዛሬ 11 ቀን የተከበረው ቴምፕሎህፍ በተባለው ታሪካዊው የበርሊኑ አውሮፕላን ማረፊያ ነበር። አውሮፕላን ማረፊያው ከ66 ዓመት በፊት በምግብ እጦት ለተቸገሩ የበርሊን ነዋሪዎች ናዚዎችን ድል ያደረጉት የተባበሩት ኃይሎች ከአየር ምግብ በመጣል የታደጉበት ስፍራ ነው። በበርሊን የአሜሪካን ኤምባሲ በዓሉን በዚህ ስፍራ ሲያከብር አሜሪካን ጀርመን ላይ መጠነ ሰፊ ስለላ ማካሄዷ ከተደረሰበት በኋላ የተቃቃሩትን የአሜሪካንና የጀርመንን ወዳጅነት ከአንድ ዓመት በኋላም ቢሆን በሙዚቃ ድግስና በምግብ መጠጥ ግብዣ የማደስ ተስፋ አድርጎ ነበር። ይሁንና የዚያን እለት ጠዋት ማርኩስ አር የተባለ የጀርመን የውጭ ስለላ ድርጅት ባልደረባ ለአሜሪካኖች በመሰለል መያዙ ተዘገበ። ከጥቂት ሰዓታት በኋላም የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጀርመን የአሜሪካን አምባሳደር ጆን ኤመርሰን ስለ ጉዳዩ ማብራሪ እንዲሰጡ መጠራታቸውን አስታወቀ። 2,500 እንግዶችን ለጋበዙት ለአምባሳደሩ ይህ ያልተጠበቀ ክስተት ነበር። በዚህ ሳያበቃም ማርኩስ አር በተያዘ በሳምንቱ ሐምሌ 2 2006 ዓም ጀርመን ፌደራል አቃቤ ሕግ ቢሮ የሌላ ተጠርጣሪ መኖሪያ ቤትና ቢሮ መፈተሹን አስታወቀ። ይሄኛው ተጠርጣሪ ደግሞ የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር ሠራተኛ ነው። እርሱ ግን ግን አልታሰረም። በሰላይነት ያስጠረጠረውም ከአንድ አሜሪካዊ ገንዘብ ተቀብሏል መባሉ ነው። የአሜሪካን ባለሥልጣናት እንዳሉት ግለሰቡ ከአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛ ጋር እንጂ ከስለላ ድርጅት ባልደረቦች ጋር ግንኙነት የለውም። አሜሪካን አነዚህን ሁለት ተጠርጣሪ ሰላዮች ማሠራቷ ከተደረሰበት በኋላ ጀርመን ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ በበርሊን የአሜሪካን ኤምባሲ የCIA ተጠሪን ከሀገር እንዲወጡ ነግራለች።

በጉዳዩ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ከፍተኛ ጫና የተደረገባቸው መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ከሚኒስትሮቻቸው ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ተጠሪው ከሀገር እንዲወጡ እንዲነገራቸው መወሰናቸው ነው የተገለፀው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ጀርመን ይህን መሰል ውሳኔ በአሜሪካዊ ባለስልጣን ላይ ስታሳልፍ ይህ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። ሜርክል ወዳጅ በምትባለው በአሜሪካን የተፈመፀው ስለላ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን መተማመን እንደሚጎዳ ተናግረው ነበር። ባለፈው እሁድ በጀርመን ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ደግሞ የአሜሪካውያን ትኩረት ይህ ሊሆን አይገባም ነበር ብለዋል።

«ለኔ ይህ ስለ ስለላ አገልግሎት ያሉን ግንዛቤዎቻችን በመሠረቱ የተለያዩ መሆናቸውን የሚያሳይ ምልክት ነው። በኔ እምነት በ21 ኛው ክፍለ ዘመን የሚካሄዱ ስለላዎች በጣም አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማትኮር አለባቸው። ከአሜሪካኖች ጋር በቅርበት ነው የምንሰራው። ይህ ወደፊትም እንዲቀጥል እፈልጋለሁ። እርግጥ ነው ጀርመን በዚሁ ተግባር ከፀረ ሽብሩ ትግልና ከሌሎች ጉዳዮች ተጠቃሚ ናት። ሆኖም የምንገኘው አንዱ ሌላውን በማያምንበት በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ላይ አይደለም። የሚያሰጉን ጉዳዮችም የተለያዩ ናቸው። ጠቃሚ በሆነው ጉዳይ ላይ ነው ማተኮር ያለብን።»

አሜሪካን ከጀርመኑ ሰላይ እጅግ ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘቷን አንዳንድ የአሜሪካን ባለሥልጣናት በግል ተናግረዋል። ሆኖም የአሜሪካን መንግሥት ባለሥልጣናት ስለ ማርኩስ አር ስለላም ሆነ ስለ ሁለተኛው ተጠርጣሪ በመገናኛ ብዙሃን በይፋ አስተያየት ከመስጠት እንደተቆጠቡ ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም እስካሁን ስለዚህ ጉዳይ የሰጡት መግለጫ የለም። ቃል አቀባያቸው ጆሽ እርነስት ግን ቅሬታው በመገናኛ ብዙሃን በሚሰጥ መግለጫ መፍትሄ አያገኝም ብለዋል።

«ማናቸውንም ልዩነቶቻችንን በጣም በተሳካ ሁኔታ ልንፈታ የምንችለው ወትሮም በተመሰረተው ምሥጢራዊ መሥመር እንጂ በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት አይደለም። እነዚህ የተለመዱት መሥመሮችም በሁለቱ ሃገራት የስለላ የዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም የብሔራዊ ደህንነት ባለሥልጣናት ጋር የሚካሄዱ መደበኛ ንግግሮችን ያካትታሉ።»

የጀርመን ባለሥልጣናት አሜሪካን በስለላው መስክ ለጀርመን ጠቃሚ መሆኗን አይክዱም። ሆኖም እንደ አሁኑ ዓይነት የስለላ ቅሌት ሲፈጸም በዝምታ ሊታለፍ እንደማይገባና ስለ ጉዳዩ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ። የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቶማስ ደ ሚዜር መንግሥታቸው ከምንም በላይ ለዜጎች ደህንነት የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል።

«ለኛ አሜሪካን በማናቸውም የደህንነት መስኮች እጅግ አስፈላጊዋ አጋር ናት። ለነፃነታችንና ለዜጎቻችን ደህንነት በውጭ ለሚገኙትም የሠራዊታችን አባላት አስፈላጊውን እንክባካቤ እናደርጋለን። ነገ ግን አንዳንዴ የሚያጋጥም ሳንክ የመነጋገርን አስፈላጊነት የሚጠቁም ይሆናል።»

የአሜሪካን ባለሥልጣናት ችግሩ በተለመደው የንግግር መስመር መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል ቢሉም የጀርመን ባለሥልጣናት ግን መፍትሄው ይሄ ብቻ አይደለም እያሉ ነው። ቶማስ ደ ሚዜር በሰጡት መግለጫ ለጠንካራው የጀርመን ዲሞክራሲ አስተማማኝ ጥበቃ፣ ጀርመን ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ከጥቃት የሚከላከል ውጤታማ የአፀፋው ስለላ ይበልጥ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል ብለዋል። የ75 ዓመቱ ቤርንት ሽሚትባወር እጎአ ከ1991 እስከ 1998 በጀርመን ፌደራል የስለላ መሥሪያ ቤት በአስተባባሪነት ሠርተዋል። እርሳቸውም የአፀፋ ስለላን አስፈላጊነትን አበክረው ነው ያስገነዘቡት።

«የአፀፋ ስለላ፣ የአፀፋ ስለላ እንደገናም ተጨማሪ የአፀፋ ስለላ፤ ይህ ሲደረግ ብቻ ነው መጠናከር የሚቻለው። ይህ ከተደረገ ብቻ ነው ማንም እንደፈለገ በጓሯችን ሊፈነጭ የማይችለው። ይህ የወዳጆች ወይም የጠላቶች ጉዳይ አይደለም። የብሔራዊ ጥቅሞች ጉዳይ እንጂ። »

የቀድሞው የአሜሪካን ብሔራዊ የስለላ ድርጅት ባልደረባ ኤድዋርድ ስኖውደን በመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የእጅ ስልክና በጀርመን ዜጎች ላይ አሜሪካን ስለላ እንደሚታካሂድ ካጋለጠ በኋላ የጀርመን ፖለቲከኞችና አጠቃላዩ ኅብረተሰብ በድርጊቱ ተበሳጭቷል። ይህ ብስጭት ሳይበርድ የተደረሰበት የሰሞኑ ቅሌትም ንዴቱን አባብሶታል። የአፀፋ ስለላ ይካሄድ የሚሉት ወገኖች ለዚህ ሥራ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲመደብ ጠይቀዋል። በእነርሱ አስተያየት የጀርመን የስለላ መሥሪያ ቤት በጀት ከፍ ማለት አለበት።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አሜሪካን የጀርመን መድህን ሆና ነው የምትታየው። ከጦርነቱ በኋላ የኤኮኖሚ የባህል እና የሞራል ውድቀት የደረሰባትን ጀርመን 12 ቢሊዮን ዶላር በወጣበት በማርሻል እቅድ አሜሪካ ዳግም እንድታንሰራራ አድርጋለች። እጎአ በ1948 የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በተከፋፈለችው በበርሊን ምዕራባዊ ክፍል የቀድሞው የጀርመን ገንዘብ ራይሽስ ማርክ በጀርመን ማርክ ሲተካ ሶቭየት ኅብረት በምዕራብ በርሊን ላይ እገዳ በመጣሏ በከተማይቱ ለምግብ እጥረት ለተጋለጠው ሕዝብ የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታኒያ አውሮፕላኖች እገዳው እስኪነሳ ድረስ ከአየር ምግብ በመጣል የክፉ ቀን ደራሽ ነበሩ። ከዚህ በኋላም የቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ እጎአ በ1963 ጀርመንን በጎበኙበት ወቅት በጀርመንኛ «በርሊናዊ ነኝ »ሲሉ ለጀርመናውያን ድጋፋቸውን በይፋ መግለፃቸው አሜሪካውያን በጀርመናውያን ዘንድ ይበልጥ እንዲወደዱ አድርጓል። ይህንና በ1960 ዎቹ መጨረሻና በ1970 ዎቹ መጀመሪያ አሜሪካን ቬይትናምን ስትወጋ ይህ በጎ አመለካከት አልቀጠለም። ወጣት ጀርመናውያን የአሜሪካንን እርምጃ ተቃዉመዉ ነበር። ከዚያ በኋላም ሌሎች ተቃውሞዎች መቀጠላቸውን በሬግንስቡርግ ዩኒቨርስቲ የአሜሪካን ጉዳዮች ጥናት ክፍል ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር ኡዶ ሄብል ያስረዳሉ።

«ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት ጀርመናውያኑ ጥያቄ ያነሱባቸው ሊጤንባቸው የሚገባ 3 ወይም 4 መነሻ ነጥቦች አሉ። አንዱ የቬይትናም ጦርነት ነው። የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ እስከ ቬይትናም ጦርነት ዩናይትድ ስቴትስን በበጎ መንፈስና በጥሩ አርአያነት ነበር የምትመለከታት። ሁለተኛው ነጥብ እጎአ በ1980ዎቹ ዓመታት ከቀዝቃዛው ጦርነት ጋር በተያያዘ NATO በጀርመን የመካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይሎችን እንዲተክል የተደረሰበት ሁኔታ ነው። የቬይትናሙ ጦርነት ያስከተለው ውጤት የሚታይ ነበር። ሌላው ደግሞ የማይረሳው አሸባሪዎች በኒውዮርክ አደጋ ከጣሉ በኋላ በኢራቅ ላይ የተከፈተው ጦርነት ነው። እጎአ በመስከረም 11 2001 ዓመተ ምህረቱ የሽብር ጥቃት ሳቢያ አሜሪካን ከጀርመን አግኝታው የነበረው አብሮ የመቆም ስሜት ቀዘቀዘ።»

እጎአ በ2003 አሜሪካን ኢራቅን ስትወር እርዳታ የተጠየቁት የያኔው የጀርመን መራሄ መንግሥት ጌርሃርድ ሽሮደር ለጥያቄው አልተባበሩም ነበር። አሜሪካን በጀርመናውያን ላይ የምታካሂደው ስለላና በቅርቡ የተደረሰበት ከጀርመን ሰላዮች ጋር የምታደርገው ምስጢራዊ ግንኙነት ሄብል እንደሚሉት በጣም ከባድ ጉዳይ ነው። የጀርመን መንግሥት ባልተጠበቀ ሁኔታ የCIAን የበርሊን ተጠሪ ለማባረር እስከመወሰን መድረሱ ይህንኑ የሚያመለክት ነው። ያም ሆኖ እርሳቸው እንደሚሉት በቀደሙት ዓመታትም በሁለቱ ሃገራት መካከል ልዩነቶች ቢከሰቱም ወደ ባሰ ደረጃ ግን ተሸጋግረው አያውቁም። የአሁኑ የስለላ ቅሌትም እንደ ሄብል በሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ላይ ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ አይጠበቅም ። ከትናንት በስተያ ቪየና ኦስትርያ ውስጥ የተገናኙት የጀርመንና የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሰጡት መግለጫም የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት እንደማይቀዘቅዝ ነው የተናገሩት ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic