የአሜሪካና የባህረ ሰላጤዉ አረብ ሃገራት ጉባኤ | ዓለም | DW | 13.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአሜሪካና የባህረ ሰላጤዉ አረብ ሃገራት ጉባኤ

የዩናይትድ ስቴትስና የስድስት የባህረ ሰላጤዉ አረብ ሃገራት ትብብር የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ማምሻዉን በዋሽንግተን ይካሄዳል። ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በሚያስተናግዱት ጉባኤ የስዑድ አረቢያ ንጉሥ እንደማይገኙ መገለፁን ተንታኞች አሜሪካ ከኢራን ጋ የጀመረችዉ ድርድር ያስከተለዉ ዉጤት ነዉ ይሉታል።

እንዲያም ሆኖ ኦባማ ከአልጋወራሹ ሞሐመድ ቢን ናያፍ እና ከምክትል አልጋወራሹ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋ ከጉባኤዉ አስቀድመዉ እንደሚወያዩ ተገልጿል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የኒኩሊየር መርሃግብሯን በተመለከተ በጀመሩት ድርድር ምክንያት ከኢራን ጋ የፈጠሩት መጠነኛ መግባባት ዛሬ ዋሽንግተን ላይ ለማካሄድ በጠሩት የባህረ ሰላጤዉ የአረብ ሃገራት ጉባኤ ላይ የራሱን ጥላ ማሳረፉ ነዉ የሚነገረዉ። ስድስቱ የዓለም ኃያላን ሃገራት ከቴህራን ጋ ከተወያዩ በኋላ የተጣለባትን ማዕቀብ ለማርገብ እንዲቻል ለመግባባት የሚያስችሏቸዉን ጉዳዮች ነድፈዉ ሲያበቁ ነዉ ኦባማ ይህን ጉባኤ የጠሩት። ለዛሬዉ ስብሰባም ስዑድ አረቢያን፣ ኩየት፣ ባህሬን፣ ቀጠርን፤ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችንና ኦማንን ነዉ ጋብዘዋል።

Kuwait Treffen Kooperationsrat der Arabischen Staaten des Golfes in Kuwait-Stadt

የአረብ ሃገራት ጉባኤ በኩየት

ፕሬዝደንት ኦባማ በመካከለኛዉ ምሥራቅ የሚገኙ ነባር የዩናይትድ ስቴትስ አጋሮችም ሆኑ የኢራን ጉዳይ በእኩል ሁኔታ መስተናገድ አለበት የሚለዉ አካሄዳቸዉ የአረብ ሃገራቱን ማስቆጣቱ ነዉ በዋሽንግተን ሆድሰን ተቋም የዉጭ ጉዳይ ተንታኝ ማይክል ዶርን የሚያመለክቱት። ይህን ጉባኤ የጠሩበት ዓላማም በምክር ቤት ዉስጥ ከሪፐብሊካን የሚቀርብባቸዉን ትችት ለማክሸፍና ከኢራን ጋ የታቀደዉ ዉል እንዳይደናቀፍ ለማድረግ ነዉም ባይ ናቸዉ።

«ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ለሚገኙ ተቺዎቻቸዉ እጆቻቸዉ አጋሮችንም እንደሚደርሱና ከእነሱም ጋ አብረዉ እንደሚሠሩ ለማሳየት ይፈልጋሉ። በዚህ ረገድ ዋና ግባቸዉ ምክር ቤቱ ነዉ። ምክር ቤቱ ከኢራን ጋ የታቀደዉን ዉል እንዳያግድ አስፈላጊዉን ድምፅም ማግኘታቸዉን ማረጋገጥም ይሻሉ።»

ሳዉዲና ሌሎች የባህረ ሰላጤዉ አካባቢ የአረብ ሃገራት ይህን ጉዳይ በከፍተኛ ጥርጣሬ ነዉ የሚመለከቱት። ኢራን የሺያት ሙስሊም የመሪነት ኃይሏን እያጠናከረች ነዉ፤ ስዑድ አረቢያ ደግሞ ራሷን የሱኒ ሙስሊሞች ጠባቂና ተከላካይ ብቸኛ ኃይል አድርጋ ታያለች። በአብዛኛዉ ኢራቅ፣ ሶርያ በቅርቡ ደግሞ የመን ዉስጥ ሁለቱ ኃይሎች በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያኪሂዱት ፍልሚያ የአካባቢዉን አለመረጋጋት አባብሷል። በዛሬዉ የአሜሪካና የባህረ ሰላጤዉ የአረብ ሃገራት ጉባኤም ራሱን እስላማዊ መንግሥት ከሚለዉ ፅንፈኛ እስላማዊ ቡድን ጋ የሚካሄደዉ ዉጊያ፤ የሶርያና የየመን ጦርነቶች መነጋገሪያ አጀንዳዎች ናቸዉ። ማይክል ዶራን፤

US-Präsident Obama trifft Iraks Premier Al-Abadi

ፕሬዝደንት ኦባማ እና የኢራን ጠ/ሚ አሊ አባዲ

«ኦባማ ዩናይትድ ስቴትስ የአካባቢዉ ጉዳይ ሸምጋይ እንድትሆን ይፈልጋሉ። ሶርያ፤ኢራቅም ሆነ የመን ችግር ሲኖር ሁሉንም በጋራ ይሰበስቡና፤ «ሁላችን አዋቂዎች ነን የሆነ የሚያግባባ ሃሳብ መፈለግ ይኖርብናል» ይላሉ። ኢራን በዚህ ጉዳይ ላይ ብትካተትም ይሻሉ፤ እናም ቴህራን በእንደዚህ ያሉ ጉዳዮች ሚና ቢኖራት ካለፉት ሶስት አስርት ዓመት በተሻለ የበለጠ ኃላፊነት ይሰማታል ብለዉም ያምናሉ።»

ኦባማ ሥለ ኢራን ያላቸዉ አቋም ግን የሳዉዲና የሌሎች የዋሽንግተን አጋር አረብ ሃገራትን አመኔታ የሸረሸረዉ ይመስላል። ለዚህም ይሆናል ሳዉዲ የአሜሪካን ይሁንታ ሳትጠብቅ የመን ዉስጥ የሚንቀሳቀሱት ሺያት ሁቲ አማፅያን ላይ የአየር ጥቃት የከፈተችዉ። ከዛሬዉ ጉባኤ አስቀድመዉም በዋሽንግተን የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች አምባሳደር የፀጥታና ደህንነት ዋስትና እንዲሰጣቸዉ መጠየቃቸዉ ተዘግቧል። ዋሽንግተን ፓስት አምባሳደር ዩሱፍ አል ኦታይባ፤ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋ በቃል የተደረሰዉ የደህንነት ዋስትና በፅሁፍ የሰፈረና በተቋም ደረጃ የተደነገገ እንዲሆን መጠየቃቸዉን ይፋ አድርጓል። ሆኖም ጉባኤ ከመካሄዱ አስቀድመዉ ከዋሽንግተን የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ፕሬዝደንት ኦባማ አሁንም የአሜሪካን አጋር የሆኑት የባህረ ሰላጤዉ አረብ ሃገራትን አመኔታ የሚያጠናክሩ አቋሞቻቸዉን እየገለፁ ነዉ። በዛሬዉ የአሜሪካ እና የስድስቱ የአረብ ሃገራት ጉባኤ የሳዉድ አረቢያዉ ንጉሥ እንደማይገኙ ቢገለፅም አልጋ ወራሹና ምክትል አልጋ ወራሻቸዉ ከስብሰባዉ አስቀድመዉ ከፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ጋ እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።

ጌሮ ሽሊስ/ ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic