የአማራ ክልል የክተት ጥሪ | ኢትዮጵያ | DW | 26.07.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአማራ ክልል የክተት ጥሪ

በአማራ ክልል ሚሊሺያዎች፣ የግል የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች እና ወጣቶች ከዛሬ ጀምሮ በወረዳ ማዕከሎች እንዲከቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ትናንት እሁድ ጥሪ አቅርበዋል። የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው የራያ፣ ጠለምት፣ የዋግ እና የወልቃይት አካባቢዎች ውጊያ እየተካሔደ መሆኑን ገልጸው ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:08

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የክተት ጥሪ አቅርበዋል

ሕወሓት በአማራ ክልል ላይ እያደረገ ያለውን ጥቃት ለመከላከልና አገርን ከብተና ለመከላከል በግልም ሆነ በመንግስት የታጠቁ የክልሉ ተወላጆችና ለግዳጅ እድሜው የደረሰ ወጣት ሁሉ ከዛሬ ጀምሮ ለክተትእንዲዘጋጅ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥሪ አቀረቡ፣ ህወሓት በ4 ግንባሮች ጥቃት መክፈቱንም ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር አመልክተዋል፡፡ 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በመግለጫቸው “ጠላት” ያሉትን ህወሓት ለመመከትና የተቃጣውን ወረራ ለመቀልበስ በግልም ሆነ በመንግስት የታጠቀ ማነኛውም የአማራ ተወላጅ ከዛሬ ጀምሮ ራሱን ለግዳጅ ዝግጁ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

“በፀጥታው ዘርፍ የነበሩና በተለያዩ ምክንያቶች ከውትድርና ሥራቸው የተሰናበቱ አባላትባለፈው በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት የህልውና ዘመቻውን በመቀላቀል ጠላትን እየተፋለሙ ነው” ብለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ህወሓት በራያ፣ ጠለምት፣ ዋግኽምራና ወልቃይት አካባቢዎች ጥቃት መክፈቱንም አቶ አገኘሁ ተናግረዋል፡፡ 

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ ዶ/ር ዓለማየሁ እርቅይሁን በበኩላቸው አማራና ትግራይ የጋራ ድንበር የሚጋሩ ክልሎች በመሆናቸው የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ አማራ ክልል በመሆኑ የወጣው ክተት ትክክለኛና ወቅታዊ ነው ብለዋል፣ ሆኖም ችግሩ በአማራ ክልል ተወስኖ የሚቀር ባለመሆኑ ሌሎች ክልሎችም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ 

ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ በማነኛውም አቅሙ በሚችለው መንገድ ሊያግዝ እንደሚገባ አመልክተው፣ በተለይ ካልተረጋገጠ ወሬ ራሱን ሊያርቅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ 
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሒር መሐመድ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት የክልሉ መንግስት ያወጣውን መግለጫ ድርጅታቸው በሙሉ ልብ ይደግፈዋል፡፡ 

7ሺህ 500 አባላት ያሉት የምስራቅ ጎጃም የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ማህበር ሰብሳቢ መቶ አለቃ ሙሉዓለም አበበ ጥሪውን መቀበላቸውንና አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡ 

ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሰ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች