የአማራ ክልል የካቢኔ ሽግሽግና የቀረበበት ትችት | ኢትዮጵያ | DW | 24.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የአማራ ክልል የካቢኔ ሽግሽግና የቀረበበት ትችት

የአማራ ክልል መንግስት ትናንት ባካሄደው ሹም ሽር አስራ ሁለት የካቢኔ አባላትን ከቦታቸው በማንሳት በአዲስ ተሿሚዎች ተክቷል፡፡ የክልሉ መንግስት አዳዲሶቹ ተሿሚዎች “በህዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚችሉ ናቸው” ቢልም አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ግን “ጥገናዊ ለውጥ እንኳ ለመባል የማይመጥን” ሲሉ የክልሉን እርምጃ ተችተዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:50
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:50 ደቂቃ

ሹምሽሩ “ጥገናዊ ለውጥ እንኳ ለመባል የማይመጥን” ተብሏል

በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አቅራቢነት ሹመታቸው ትናንት የጸደቀላቸው የካቢኔ አባላት 12 ሲሆኑ አስሩ ባሉበት እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ በስልጣናቸው ከረጉት መካከል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ብናልፍ አንዷለም እና የክልሉ መንግስት ቃል አቃባይ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ይገኙበታል፡፡

ቀደም ሲል እንደተከናወኑት የፌደራል መንግስት እና የኦሮሚያ ክልል ሹመቶች ሁሉ በአማራ ክልል አዲስ ካቢኔም በትምህርት ደረጃ የዶክትሬት ማዕረግ ያላቸው አምስት ግለሰቦች ተካትተዋል፡፡ ለአዲሶቹ ተሿሚዎች ዋነኛ መመዘኛ የተደረገው “ህዝብን የማገልገል ፍላጎታቸው እና ሙያቸው ለተሾሙበት መስሪያ ቤት ያለው ቅርበት እንደሆነ” አቶ ገዱ ለአማራ ክልል ምክር ቤት ተናግረዋል፡፡

የአዲሱ ካቢኔ አባላት ሹመት በአንድ ድምጸ ተዐቅቦ ብቻ ቢጸደቅም በገዢ ፓርቲ ብአዴን ከተሞላው ምክር ቤት ግን ጥያቄያዎች ተነስተውበታል፡፡ የሴት ተሿሚዎች  ቁጥር አናሳ መሆን የተቹ እና የቢሮ ኃላፊ ለሆኑ የካቢኔ አባላት የምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ማዕረግ መደራረቡ እንደማይጠቅም እምነታቸውን የገለጹ ነበሩ፡፡ ከትምህርት እና ከምርምር ተቋማት የመጡ አዲስ ተሿሚዎች በቢሮክራሲው ውስጥ ፈተና እንደሚገጥማቸው የተነበዩም አሉ፡፡

በርካታ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ሹመቱን ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ በሚል ሲያወድሱት ቢደመጡም የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ቻላቸው ታደሰ ግን የክልሉ መንግስት የወሰደውን የካቢኔ ሽግሽግ ከመሰረታዊ የፖለቲካ እርምጃ የራቀ “ተራ ጉዳይ” ነው ሲሉ ያጣጥሉታል፡፡ የተደረገውን ሹም ሽርም “የነበረውን አካሄድ የማስቀጠል” እርምጃ እና “ምንም አይነት ለውጥ የማድረግ ፍላጎት ማጣት” ሲሉ ተችተውታል፡፡

“አራቱ ፓርቲዎች የሚመሯቸው አራቱ ዋና ዋና ክልሎች- ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አማረ እና ትግራይ- በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በቀጥታ የሚመሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም የፌደራል መንግስቱ በፌደራል ደረጃ ካደረገው ለውጥ በተቃራኒው ይሄዳሉ ተብሎ አይገመተም፡፡ የፌደራሉን ግልባጭ ያደርጋሉ ተብሎ ነው የሚታሰበውና ያደረጉትም ይህንኑ ነው፡፡ ይህን አይነት ለውጥ ማድረግ በገዢው ፓርቲ ቀደም ብሎ የተወሰነ መሆኑ የሚታወቀው የኦሮሚያ ክልል ተመሳሳይ እርምጃ ከፌደራሉ መንግስት ቀድሞ ማድረጉ ነው፡፡ አካሄዱ ያለውን ሁኔታ የማስቀጠል ነው፡፡ አሁን  የተደረገው ነገር ጥገናዊ ለውጥ ሊባል እንኳ የማይመጥን ነው” ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ መጠነ ሰፊ ቀውስ እየገባች ላለች እና አስቸኳይ ጊዜ ለታወጀባት ሀገር የካቢኔ ሹም ሽር ለውጥ አያመጣም ባይ ናቸው፡፡  ይልቅስ በሀገሪቱ እና በክልሉ ውስጥ በተደጋጋሚ እየተነሱ ላሉ ፓለቲካዊ ጥያቄዎች “ፖለቲካዊ እርምጃዎች” ያስፈልጋሉ ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ “የህዝብ ጥያቄ የካቢኔ ለውጥ አይደለም” ሲሉም ያስረግጣሉ፡፡ የክልሉ መንግስት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ግን “የአመራር መቀያየር ለውጥ አያመጣም” የሚለውን ትችት አይቀበሉም፡፡

“የሰው መቀየር ለውጥ አያመጣም የሚለው አስተሳሰብ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ሰው ለውጥ ያመጣል፡፡ ነገር ግን በክልላችን ባለፉት ወራት ግጭቶች መከሰታቸው በግጭቶቹም ጉዳት መድረሳቸው ይታወቃል፡፡ ዋነኛ በክልላችን ለደረሱት ግጭቶች ህዝቡን ቅር ያሰኙ ጉዳዮች ምንጮች በርካታ ናቸው፡፡ የክልሉ አመራር እና በየደረጃው ያለው አመራር ለህብረተሰቡ በቂ አገልግሎት አለመስጠት እና በመልካም አስተዳደርም እጥረት የሚገለጹ ችግሮች ናቸው ጎልተው የወጡት፡፡  እነዚህን ችግሮች የሚፈታው አመራር ነው፡፡ ስለዚህ አመራር መቀየር፣ አመራር ለውጥ ማምጣት፣ በአስተሳሰብም ጭምር ለውጥ ማምጣት ወሳኝ መሆኑ ማንም የሚክደው ጉዳይ አይደለም” ሲሉ አቶ ንጉሱ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡       

ባለፈው አንድ ዓመት በአማራ ክልል የተከሰቱ ችግሮችን ወደ ኋላ መለስ ብለው የሚያስታውሱት አቶ ቻላቸው አንዳቸውም ማጣራት ሳይደረግባቸው፣ ተጠያቂው ሳይታወቅ እና እርምጃ ሳይወሰድ የካቢኔ ለውጥ ማድረግ ብቻውን መፍትሄ አይሆንም ይላሉ፡፡ የወልቃየት የማንነት ጥያቄን በምሳሌነት አንስተው ከገዢው ፓርቲ ውስጣዊ አሰራር አንጻር እንዴት መፍትሄ አልባ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

“በገዢው ፓርቲ በማዕከሉ እና በክልሎች መካከል ተዋረዳዊ የሆነ ግንኙነት እንጂ የአግድሞሽ ውይይት በክልል ፓርቲዎች መካካል የለም፡፡ ስለዚህ አሁን በብአዴን እና በህወሓት መካከል ውይይት ኖሮ የወልቀይት ችግር ይፈታል ብዬ አላምንም፡፡ ትግራይ ክልልም የሚመራው ህወሓት ይህንን የወልቃይት ችግር ፈትቶ መፍትሄ ይሰጣል ወይም ከብአዴን ጋር የጋራ መድረክ ይቀመጣል የሚል እምነት የለም፡፡ እኔ በበኩሌ እንደዚያ አላምንም፡፡ ስለዚህ የወልቃይት ችግር እየተንከባለለ እንደሚቀጥል እና ትግራይ ክልልም ሙሉ ለሙሉ ቁጥጥሩን አጥብቆ ሊቀጥል እንደሚችል ነው” ይላሉ አቶ ቻላቸው፡፡

አቶ ንጉሱ የወልቃይትን ጥያቄ ለመፍታት በአማራ እና ትግራይ ክልል አመራሮች በኩል ችግር እንደነበር ይቀበላሉ፡፡ ሆኖም አሁን ስምምነት ላይ እንደተደረሰ እና ወደ ተግባር ሊገባ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

“ከአሁን ቀደም ችግሩን የተንከባለለበት ምክንያት በሁለቱ አጎራባች ክልሎች አመራሮች በኩል ችግሩን ለመፍታት የነበረ የመነሳሳት ወይም ደግሞ ፍላጎት የማጣት ነበር፡፡ ችግሩን ከህዝብ ወይም ከዜጎች አይን አኳያ በመፍታት እና በማየት ረገድ እጥረት ነበር፡፡ አሁን ግን ችግሩን ቁጭ ብሎ፣ ተመካክሮ፣ ህዝቡን አወያይቶ መፍታት ተገቢ እንደሆነ ስምምነት ተደርሷል፡፡ ይህንን ስናደርግ ደግሞ ግጭቶቹ ከተከሰቱባቸው ጊዜያትም ወዲህ በተመለከተ አመራር በማደራጀት፣ በየቦታው የተነሱ ችግሮችን  በመፍታት፣ ህዝቡን በማወያየት ላይ ነው ያለነው፡፡ አሁን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚገባበት ወቅት ነው” ብለዋል፡፡    

እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ትላንት በተጠናቀቀው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ጭምር በአማራ እና በትግራይ መካከል ስላለው የወሰን ጥያቄ እና የወልቃይት ጉዳይ ጠንከር ያሉ አስተያየቶች ሲነገሩ ተደምጠዋል፡፡ “የወሰን ጥያቄው 15 ዓመት ፈጅቷል፣ ቁርጥ ያለ ነገር ይወሰን” ያሉም ነበሩ፡፡   

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ

 

Audios and videos on the topic