የአማራ ክልል መፈንቅለ-መንግሥትን ለመቆጣጠር የፌደራል ኃይሎች ባሕር ዳር ገቡ | ኢትዮጵያ | DW | 22.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአማራ ክልል መፈንቅለ-መንግሥትን ለመቆጣጠር የፌደራል ኃይሎች ባሕር ዳር ገቡ

የፌደራል የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ በተደረገባት የባሕር ዳር ከተማ ተሰማሩ። የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት መኮድ ተብሎ ከሚጠራው የጦር ሰፈር ወደ ከተማዋ የዘለቁ ወታደሮች የጸጥታ ቁጥጥር እያደረጉ ናቸው።  

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ዛሬ መደረጉን የጠቅላይ ምኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ምሽቱን ባወጣው መግለጫ በፌድራል መንግሥት የተሰማራው ኃይል "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር አውሎ በፈጸሙት አካላት ላይ ተገቢውን ርምጃ እንዲወስድ ትእዛዝ" መሰጠቱን አረጋግጧል። የጸጥታ ኃይሉ የተሰጠውን ትዕዛዝ "ተፈጻሚ በማድረግ" ላይ እንደሚገኝ ይኸው መግለጫ አትቷል።

በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ የተመራ ክልላዊ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ መደረጉን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) አስታወቋል። የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራው መክሸፉን የክልሉ ገዢ ፓርቲ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ገደማ በአማራ ቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

ከመንፈቅለ መንግሥት ሙከራው ጋር በተያያዘ የክልሉ መንግሥት መቀመጫ በሆነችው ባሕር ዳር ከምሽቱ 12 ከ30 ጀምሮ ቢያንስ ለግማሽ ሰዓት የዘለቀ የተኩስ ድምጽ ሲሰማ እንደነበር የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የከተማዋ ነሪዎች እንደሚሉት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የክልሉ ምክር ቤት እና የርዕሰ-መስተዳድሩ ፅህፈት ቤት በሚገኙባቸው አካባቢዎች የተኩስ ድምፅ ተሰምቷል።

አንድ የከተማዋ ነዋሪ "ተኩስ የጀመረው ፖሊስ ኮሚሽን አካባቢ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። ከፖሊስ ኮሚሽን ፅህፈት ቤት አቅራቢያ የነበሩት እኚሁ የዐይን እማኝ "የቀላል እና የከባድ መሳሪያ ተኩስ" መስማታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በክልሉ ልዩ ኃይል አዲስ እና ነባር አባላት መካከል ቀደም ሲል ግርግር እንደነበር መስማታቸውንም ገልጸዋል።

በባሕር ዳር ከተማ የነበረው ተኩስ ቢቆምም ነዋሪዎች በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ እንደሚገኙ አስረድተዋል። ከተማዋ በውጥረት ውስጥ ናት የሚሉት ነዋሪዎቹ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እንደተቸገሩ አብራርተዋል። የአማራ ክልላዊ መንግሥት የሚያስተዳድረው የአማራ ቴሌቭዥን ጣቢያ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ከተሰማ በኋላ ሁለት ጊዜ ሰበር ዜናውን አስተላልፎ መደበኛ ዝግጅቶቹን ማቅረብ አቋርጧል። የቴሌቭዥን ጣቢያው የሐይቅ እና የተራሮች ምስሎችን በመሳሪያ በተቀነባበሩ ሙዚቃዎች አጅቦ በማሳየት ላይ ይገኛል። በባሕር ዳር የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ስልክ ለመደወልም አስቸጋሪ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል። 

በመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራው የተገደሉ እና የቆሰሉ ሹማምንት መኖራቸው ቢሰማም እስካሁን በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም። የጠቅላይ ምኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ እንደተናገሩት በአማራ ክልል የመንግሥት መዋቅር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የተሞከረው በተደራጀ ሁኔታ ነው።። አቶ ንጉሡ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ያደረጉ ኃይሎችን ማንነት ባይገልጹም ድርጊቱን "የተደራጀ እንቅስቃሴ" ሲሉ ጠርተውታል።

በአማራ ክልል ተሞከረ የተባለውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የፌደራል ክልል፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና የአዲስ አበባ ክልል መስተዳድሮች በየፊናቸው አውግዘዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  ድርጊቱ "ሕገ መንግስታዊ ስርዓትን በሃይል ለመናድ የተደረገ ነው" ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። መግለጫው "ሕጋዊነት በሌለው አግባብ ስልጣን ለመቆናጠጥ ሙከራ ማድረግ የዜጎችን የራስ በራስ የማስተዳደር መብት የሚጥስና ስርዓት አልበኝነት እንዲነግስ መፈለግ ስለመሆኑ ግልጽ ማሳያ" ሲል አክሏል። የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት በበኩሉ ድርጊቱን ኢ- ሕገ-መንግስታዊ እና የዲሞክራሲ ስርዓትን የጣሰ ብሎታል።

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ