የአማራጭ ኃይልምንጮች ዓለምአቀፍ ጉባኤ ፍፃሜ | ኤኮኖሚ | DW | 04.06.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአማራጭ ኃይልምንጮች ዓለምአቀፍ ጉባኤ ፍፃሜ

መራሔመንግሥት ሽረደር በጉባኤው ወቅት ከጀርመን የልማት ትብብርና የተፈጥሮ ጥበቃ ሚኒስትሮች ጋር

መራሔመንግሥት ሽረደር በጉባኤው ወቅት ከጀርመን የልማት ትብብርና የተፈጥሮ ጥበቃ ሚኒስትሮች ጋር

ባለፉት አራት ቀናት ውስጥ ወደ ፫ሺ የሚጠጉ የመንግሥታት ልኡካንን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ የዓለምአቀፍ ተቋማትን፣ የሙያ ማህበራትን፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ቡድናትን፣ የምርምርና የቴክኒክ ምርት ኩባንያዎችን፣ ሻጮችንና ፍጆተኞችንም ሲያወያይ የሰነበተው፣ አማራጭ የኃይል ምንጮጭን ልማት የሚመለከተው ዓለምአፍ ጉባኤ ዛሬ ተፈጽሟል። ከበካዮቹና ከውዶቹ ወደ ንፁሆቹና ርካሾቹ የኃይል ምንጮች አቅርቦት ለመሸጋገር አሁንና ወደፊት ምን መደረግ እንዳለበት ጉባኤው አንድ ዓለምአቀፍ መመሪያ-ንድፍ አቅርቧል።

ፀሀይን፣ ውሃን፣ ነፋስንና የምድር ሙቀትን የመሳሰሉት አማራጭ፣ ታዳሽ፣ንጹሕ እና በንጽጽርም ርካሽ የሆኑት የኃይል ምንጮች እርከን በእርከን ከሰልን፣ የምድርዘይትንና የምድር ጋዝን በመሳሰሉት በበካዮቹ የተፈጥሮ ቅሪቶች ቦታ የሚተኩበትን መንገድ ያሳየው ዓለምአቀፍ ጉባኤ ዛሬ ፍፃሜ ላይ በደረሰበት ወቅት በተለይ ለ፫ኛው ዓለም ሀገሮች ከፍተኛውን ተሥፋ ነበር የፈነጠቀው። መደምደሚያ ንግግር ካሰሙት ልኡካን መካከል አንዱ የሆኑት የፊሊፒን ወኪል፣ የሀገራቸው መንደሮች በሙሉ እጎአ እስከ ፪ሺ፮ ድረስ ከፀሐይ ብርሃን፣ ከነፋስ እና ከኮኮ በሚመረተው ኃይል አማካይነት የኮሬንቲው መረብ እንደሚዘረጋላቸው በማረጋገጥ በጉባኤው አዳራሽ ውስጥ ያስተጋቡት ቃል “እኔ ሰላማዊ ሰው ነኝ፥ ግን በድህነት አንፃር ጦርነትን ለማወጅ ዝግጁ ነኝ--ይህንኑ ጦርነት ለማሸነፍ ጠንክረን እንታገል” የሚል ነበር። ከኮኮ እፀዋት በሚመረት ነዳጅ መኪና ለማሽከርከር ፕሮዤ መዘርጋቱም ነበር በፊሊፒኑ ወኪል የተገለፀው። የዚህ ዓይነቱ ንግግር ነው ተሥፋን የፈነጠቀው። ለዚሁ ተሥፋ አንድ ተጨማሪ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፥ ለጉባኤው መደምደሚያ ተባባሪ ሊቀመንበርነቱን ይዘው የነበሩት የደቡብ አፍሪቃም ልኡካን መሪ ሀገሪቱ ውስጥ በሚቀጥሉት ስምንት ዓመታት በአማራጭ የኃይል ምንጮች አማካይነት የኮሬንቲውን ብርሃን ለመላው ሕዝብ ለማዳረስ መታቀዱን ባረጋገጡ ጊዜ የጋለ ጭብጨባ ነበር የተደረገላቸው።

ከዚሁ ጉባኤ ዓበይት ውጤቶች አንዱ፣ ዓለምአቀፉ የተጨባጭ ርምጃ መርሐግብር ነው። ይኸው መርሐግብር መንግሥታትና ሌሎችም የተግባር ተሳታፊዎች ታዳሽ የኃይል ምንጮች በሰፊውና በቅልጥፍና ጥቅም ላይ በሚውሉበት ግብ ረገድ ተጨባጭ ርምጃዎችን እንዲወስዱ፣ በዚሁ አግጣጫ ሙሉ ኃላፊነትን እንዲተገብሩ መመሪያ የሚሰጥ ነው። በጉባኤው ላይ የተገኙት መንግሥታት፣ የተባ መ ድርጅት፣ ሌሎች ዓለምአቀፍ ድርጅቶችና የፊናንስ ተቋማት፣ የኅብረተሰብ ቡድናት፣ የግሉ ዘርፍና ሌሎችም የፕሮዤ ተንቀሳቃሾች--ሁሉም ናቸው ለዚሁ የጋራ መርሐግብር አስተዋጽኦ ያደረጉት።

መርሐግብሩ እንደሚዘረዝረው፣ የታዳሽ ኃይልምንጮች ልማትና ስርጭት፣ እንዲሁም ይህንኑ ዘርፍ የሚመለከተው የቴክኖሎጂው/ማለት የሥነቴክኒኩ እመርታ በዚህ ፳፩ኛ ምእተ-ዓመት መጀመሪያ ላይ የኤኮኖሚ፣ የተፈጥሮ ደኅንነት እና የማኅበራዊ ኑሮ ድብረት ግብን ለመተግበር የሚረዳ ይሆናል። አማራጭ/ማለት ታዳሽ የኃይል ምንጮች ለዘላቂው ልማት ዓይነተኛ መከታ ሆነው ይታያሉ።

በሚቀጥሉት ፴ ዓመታት ውስጥ በመላው ዓለም ውስጥ ለኃይል ምንጭ አቅርቦት እንደሚመደብ ከሚታሰበው ፲፮ ትሪሊዮን ዶላር ትልቁ ከፊል ለታዳሽ ኃይልምንጮች ልማትና ስርጭት እንዲውል ሲደረግ ብቻ ነው የዘላቂውን ልማት ግብ ለመተግበር እና ያየርን ቀውስ ለመግታት የሚቻለው ይላል የጉባኤው አዋጅ። የታዳሽ ኃይልምንጮችን ጠቀሜታ ለማስፋፋት በተለይ ሦሥት ዘርፎች እንዲጠናከሩ ማስፈለጉ ተዘርዝሮአል፥ ይኸውም፣ ቴክኖሎጂን/ማለት ሥነቴክኒክን ለማፍለቅ፣ ለማምረት፣ ለመትከል፣ ለማካሄድና ለመንከባከብ፣ እንዲሁም አሠራርንና ሥርዓትን ለማቃናት የሚያስችል አንድ ሥልጡን የሙያ ኃይል ዝግጁ እንዲሆን፣ የተቃና ተቋማዊ አውታር እንዲኖርና ቴክኖሎጂው በቦታው ያለ፣ ለቦታው ምቹ የሆነ እና ከቦታው የፊናንስ ኣቅም ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን ግዴታ ነው። ሦሥቱም እይታ የአቅምን ግንባታ እንደሚመለከት መርሐግብሩ ይጠቅሰዋል።

ሠነዱ አበክሮ እንደሚያስገነዝበው፣ ግቡን የሚያራምዱ የተጽእኖ ቡድኖች አስፈላጊ ይሆናሉ፥ በዚህ ረገድ በተለይ የተጠቀሱት፥ መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች ናቸው። መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች በሚደረጁት ሀገሮች ውስጥ ታዳሽ የኃይል ምንጮች በሰፊ ጥቅም ላይ በሚውሉበት ተግባር ረገድ ቁልፉን ሚና የሚይዙ ሆነው ነው የሚታዩት። ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎችም የምርምር ተቋማት በታዳሽ የኃይል ምንጮች አዋዋል ረገድ የሚያከናውኑት የምርምር ሥራ ከፍተኛ ክብደት ነው የሚሰጠው።

የዓለም ባንክ እጎአ እስከ 2010 --ማለት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ -- ለአማራጭ ኃይልምንጮች ልማትና ቀልጣፋ አመራረት የሚሰጠውን የብድር ርዳታ በያመቱ በሃያ በመቶ እንደሚያሳድገው ለጉባኤው የሰጠው ማረጋገጫ ስለ ድህነት ቅነሳ ለተተለመው ለተባ መ የአሠርቱ ምእት ግብ ተሥፋ ፈንጥቆለታል ለማለት ያስደፍራል።

ተዛማጅ ዘገባዎች