የ«አሚሶም» ወታደሮች ደምወዝ | አፍሪቃ | DW | 28.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የ«አሚሶም» ወታደሮች ደምወዝ

በሶማልያ የአፍሪቃ ኅብረት ኃይል የ«አሚሶም» ወታደሮች ደምወዝ ከተከፈላቸዉ ስድስት ወራት ማለፉ ተገለጠ። በሶማልያ የሚንቀሳቀሰዉን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብን እንዲወጋ የአፍሪቃ ኅብረት ያዘመተዉ ጦር 22 ሺህ ወታደሮች እንዳሉት ይታወቃል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:48

አሚሶም


ከተለያዩ የአፍቃ ሃገራት የተዉጣጡት ወታደሮች የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩባቸዉም በአፍሪቃ ቀንድ ፀጥታን ለማስከበር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑ ይነገራል። የጦሩን ወጪ የሚችለዉ የአዉሮጳ ሕብረት ነዉ።


የአፍሪቃ ኅብረት የሶማልያ ተልዕኮ የ«አሚሶም» ወታደሮች ደምወዝ ሳይቀበሉ ስድስት ወር የቆየበት ምክንያት በአንዳንድ «የሂሳብ ነክ ጉዳዮች » አለመሟላት መሆኑን ቢቢሲ የ«አሚሶም»ን ተጠሪ በመጥቀስ ዘግቦአል። ደምወዙም ሆነ የገንዘብ መክፈያ ሰነዱ በመንገድ ላይ በመሆኑ በቅርቡ ወታደሮቹ ደምዛቸዉን እንደሚያገኙም ተዘግቦአል። የአዉሮጳ ኅብረት ለአሚሶም ከሚሰጠዉ ገንዘብ ይቀንሳል ከመባሉ ጋርና ሌሎች ችግሮች ተደምረዉ ያስከተለዉ ዉጤት ነዉ ያሉት ሲሉ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ስልታዊ ጥናት ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ አበበ አይነቴ ገልፀዋል።


የአዉሮጳ ኅብረት ሶማልያን ለሰፈረዉ ለያንዳዱ ወታደር በወር 1,028 ይሮ ገደማ ይከፍላል። ይሁንና ወታደር ያዘመቱ መንግሥታት ለሥራ ማስኬጂያ በሚል ከያንዳዱ ወታደር ክፍያ 200 ዶላር ይቀንሳሉ። ስለዚሕ አንድ ወታደር በወር የሚያገኘዉ 800 ዩሮ ገደማ ነዉ። ከ«አሚሶም» ሰላም ማስከበር ሂደት አንጻር ጎልቶ እየወጣ ያለዉ የጦር ኃይሉ ክፍተቶች ብቻ ነዉ ያሉት አቶ አበበ አይነቴ።


ባለፉት 12 ወራቶች ዉስጥ በሶማልያ የሚገኘዉ የብሩንዲ፤የዩጋንዳ፤ የኬንያና የኢትዮጵያና የጅቡቲ ጦር ሰፈር በአሸባብ ሚሊሺዎች ጥቃት ደርሶበታል። የሶማልያን ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበዉ በሶማልያ የአሸባብ ሚሊሽያዎች አሚሶም ላይ ባደረሱት አንድ ጥቃት ብቻ 180 የኬንያ ወታደሮች ተገድለዋል።

ኬንያ ግን በጥቃቱ የተገደሉባትን ወታደሮች ብዛት በይፋ አላስታወቀችም።በቅርቡም አሸባብ በአሚሶም የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት አድርሶ ስድሳ ወታደሮች ገድያለሁ ቢልም የኢትዮጵያ መንግሥት አንድም ወታደር አለመገደሉንና ለማጥቃት የመጣዉ የሚሊሽያ ቡድን በሙሉ መገደሉን ማስታወቁ ይታወሳል። የአፍሪቃ ኅብረት በአሚሶም ስር በሶማልያ ሰላም ለማስከበር ከተሰማሩት ወታደሮች መካከል እስካሁን ስንት ወታደሮች መገደላቸዉን በግልፅ ያወጣዉ መግለጫ አለመኖሩ ይታወቃል።


አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic