የአመአቱ ግብ | ዓለም | DW | 20.09.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአመአቱ ግብ

ዛሬም የአለምን ሕዝብ መፃኤ እድል ለመወሰን እንደገና ጉባኤ ላይ ናቸዉ።እንደገና ለእቅዱ ገቢራዊነት እንደገና ቃል-ይገቡ ይፈርሙ ይሆናል።ድሕነት፥ ረሐብ፥ በሽታ-ማይምነትም ቃል-እያስገባ ሕዝብ ይጨረሳል።ሌላ ዘመን ሌላ ቃል-ሌላ እልቂት

default

አናን

20 09 10


አለም በረሐብ-በሽታ፥ በድሕነት-ማይምነት፥ በፆታ ተባለጥ ላይ በጋራ ሊዘመት መሪዎቹ በጋራ ቃል ከገቡ እነሆ አስር አመት ደፈኑ።ዛሬም በአስር አመቱ ሌላ ቃል ሊገቡ ኒዮርክ ታድመዋል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአመአቱ ግብ፥ ቃሉ፥ ሒደትና ዉጤቱ።የዛሬ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ-ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ጋናዊዉ ዲፕሎማት ኮፊ አናን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠላም አስከባሪ ጉዳይ ምክትል ዋና ፀሐፊ በነበሩበት በ1990ዎቹ (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የሶማሊያዉን ግጭት-ድቀት፥ የሩዋንዳዉ፥ ጭፍጨፋ፥ የላይቤሪያዉን ፍጅት ቸል ብለዋል በሚል ሲተቹ ሲወቀሱ ነበር።የዋና ፀሐፊነቱን ሥልጣን ጠቅልለዉ ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ትችት ወቀሳዉን ለመፋቅ፥ ምናልባትም የያኔ ስሕተታቸዉን ለማረም-ወይም አፍሪቃን ለመካስ፥ ወይም ከሁሉም በላይ እንደ አፍሪቃዊ ለአፍሪቃዉያን በጎ ለማድረግ ያሰቡ ያሰላስሉት፥ የወጠኑ ያቀዱት ሕልም-ትልም የዚያን-ቀን የአለም ቃል ሆነ።መስከረም 8 2000.
«ሁላችሁምን እንኳን ደሕና መጣችሁ ሥል ታላቅ ክብር ይሰማኛል።ከዚሕ ቀደም ይሕን ያሕል ብዛት ያላቸዉ ሐገራት መሪዎች ባንድ ጉባኤ ላይ ተካፍለዉ አያዉቁም።ይሕ ልዩ ሁነት ነዉ።ልዩ አጋጣሚ ነዉ።በዚሕም ምክንያት ልዩ ሐላፊነት ነዉ።ክብራትና ክቡራን!እናንት የአለም ሕዝቦች መፃኤ እድልን የምትወስኑ መሪዎች ናችሁ።የአለም ሕዝቦች በዘመናችን ካሉ ትላልቅ አደጋዎች እንድት-ታደጓቸዉ ዘመኑ ካፈራዉ ፀጋ ተጠቃሚ እንድታደርጓቸዉ እናንተን ይጠብቃሉ።»

አናን የአለም አቀፉ ድርጅት የሠላም አስከባሪ ጉዳይ ምክትል ዋና ፀሀፊ በነበሩበት ዘመን ከቼችንያ እስከ ካሽሚር፥ ከቦስኒያ እስከ ጆርጂያ ፥ከኢራቅ እስከ ፍልስጤም-እስራኤል፥ ከሶማሊያ እስከ ሩዋንዳ አለምን የሚያብጠዉ ጦርነት፥ ግጭት፥ ጭፍጨፋ መባባሱ ከሶቬት ሕብረት መፈረካከስ በሕላ «የአዲሱ ዘመን አዲስ አለም» የሚባልለትን ዓለም የወደፊት ጉዞ አጠራጣሪ ምናልባትም አስጊ አድርጎት ነበር።

አዲሱን ዓለም ባሻት ለመዘወር የልዕለ ሐይልነቱን ሥልጣን ያለ ተቀናቃኝ የጠቀለለችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ጥርጣሬ ሥጋቱን የፈጠሩትን እልቂት ፍጅቶችን ለማስቆም ከልብ አለመጣሯ ወይም አለመቻሏ ወዳጆዋ ለምክር-ትችት፥ ጠላቶችዋን ለወቀሳ-ርግማን ባንድ አሳብሮ ነበር።ያ ቀን ግን የአለምን ብቸኛ የመሪነትን ሥልጣን ለጠቀለለችዉ ሐገር የወዳጆችዋን ምክር-ትችት ለመቀበሏ-ምልክት፥ የጠላቶችዋን ወቀሳ ርግማን ለማክሸፏ አብነት መስሎ ነበር።

UNO General Sekretär Ban Ki-Moon

ባን

ለፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ደግሞ እንደ ብቸኛዋ ልዕለ-ሐያል ሐገር መሪ በስምንት አመቱ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ላደረጉት በጎ- ማጠናከሪያ፥ላደረጉት መጥፎ ማካካሻ፥ ከሁሉም በላይ ፍልስጤም እስራኤሎችን ለማስታረቅ ያደረጉት ጥረት ከመጨረሻዉ ጠርዝ ላይ ሲደርስ በመክሸፉ ለገባቸዉ ሐዘን መፅናኛ ብጤ ነበር።እና እንደ መሪ ለሚሰናበቱት ዓለም-ቃል ገቡ።

«እዚሕ የተሰበሰቡት መሪዎች በአዲሱ አመአት ታሪክን ዳግም መፃፍ ይችላሉ።ካለፈዉ አስተምሕሩት ከተማርን ለልጆቻችን የተሻለ ዉርስ-ቅርስ ማኖር እንችላለን።ግን አንድ ቀላል እዉነታን መቀበል አለብን።የትም ቦታ፥ በየትኛዉም ሐገር፥ በየትኛዉም ደረጃ የሚገኙ ሰዎች አስፈላጊዎች ናቸዉ።እያንዳዱ የሚያደርገዉ አስተዋፅኦ አለ።እና ሥንረዳዳ የተሻለ ነገር እንሠራለን።አመሰግናለዉ፥ ፈጣሪ ይባርካችሁ።»

ምዕራብ አዉሮጶች በዩናይትድ ስቴትስ መሪነት ከአርባ አመት በላይ የታገሉት ኮሚንስታዊ ሥርዓት በተገረሠሠ ማግስት እንደ አዲስ ብቅ ያለችዉን ዓለም በጣሙን አዉሮጳን በቅጡ ማስተባበር፥ ማስተዳደር መምራት መቻል-አለመቻላቸዉን የዘመኑ እዉነት አጠያያቂ አድርጎት ነበር።

ከአጠያያቂነቱ ባለፍ የቀድሞዋ ይጎዝላቪያን የሚያደቀዉ ጦርነት፥ በጣሙን ቦስኒያ ሔርሶ ጎቪንያ ላይ የተፈፀመዉን ጭፍጨፋ ፈጥነዉ ባለማስቆማቸዉ የሚዥጎደጎድባቸዉን ተቃዉሞ፥ ወቀሳ-ትችትን በኮሶቮዉ ዘመቻ ለመቀልበስ ያደረጉት ሙከራም ከሰፊዉ የአለም ችግር ባንዲት ቁንፅል ግዛት ላይ ያነጣጠረ፥ ሐይልን-በሐይል ለመመከት ያለመ ሥለነበር ከገሚስ ግብ ባለፍ ለአለም ሠላም አሳማኝ ሠላማዊ እርምጃ አልነበረም።

የዚያን ቀን ኒዮርክ የቀረበዉ እቅድ አብዛኛዉን ዓለም የሚያረካ የሚያሳምን ሥለሆነላቸዉ በፀጋ ተቀበሉት፥ ለገቢራዊነቱም ቃል ገቡ።የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር-ድሕነት፥ ረሐብና በሽታን ለማጥፋት መሠረቱ ሠላም ነዉ አሉ።እና ለሰላም ቃል ገቡ።

«ሠላም የማስከበሩ አስፈላጊነት እንደዚሕ ዘመን ያክል ጨምሮ አያዉቅም።በአንዳድ ሁኔታዎች በርግጥ በሥርዓተ-አልበኝነትና በሆነ ደረጃ ባለ መረጋጋት መካካል ልዩነት መኖሩን ልናጤነዉ ይገባል።»

የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ጌርሐርት ሽሮደር ቀጠሉ።

«በጠና ድሕነት የሚኖረዉን ሕዝብ ቁጥር እስከ ሁለት ሺሕ አስራ አምት ባለዉ ጊዜ በግማሽ ለመቀነስ የወጣዉን እቅድ እንድንቀበል ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ለመንግሥታቱ ድርጅት አባላት ሁሉ ጥሪ አቅርበዉልናል።እኔ ይሕንን እቅድ በሙሉ በሙሉ እቀበለዋለሁ፥ በቁርጠኝነትም እደግፈዋለሁ። መንገስቴ ጀርመን ይሕን እቅድ በተጨባጭ ገቢር የምታደርግበትን ብልሐትና ሥልት ይቀይሳል።»
ሌሎቹም አሠለሱ።የዚያን ቀን በዚያ ጉባኤ የተካፈሉት የአንድ መቶ ሐምሳ ሐገራት መሪ-ተወካዮች ለዚያ ሰናይ እቅድ ገቢራዊነት እንደሚጥሩ ቃል ገቡ።በፊርማቸዉም አፀደቁ።የአመአቱ ግብ። ቃል ተገባ፥ ተፈረመ፥ ተጨበጨበ፥ተዘመረለትም።

ሥምንቱ ግቦች።በእቅድ ቃሉ መሠረት እስከ ሁለት ሺሕ አስራ-አምስት ገቢር መሆን አለባቸዉ።ግብ አንድ፥- የጠና ድሕነትን ማጥፋት።በእቅዱ መሠረት የቀን ገቢዉ ባሁኑ መመዘኛ ከአንድ ዶላር ከሃያ አምስት ሳንቲም በታች የሆነዉን የአለም ሕዝብ ከድሕነት ማላቀቅ።

ግብ ሁለት፥-እድሜያቸዉ ለትምሕርት የደረሱ ልጆች በሙሉ የትምሕር እድል እንዲያገኙ።

ግብ ሰወስት፥-ሴቶችን ለስልጣን ማብቃት ወይም የፆታ እኩልነትን ማረጋገጥ።ግብ አራት የሚሞቱ ሕፃናትን ቁጥር መቀነስ፥ ግብ አምስት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር መቀነስ።ግብ ስድስት የኤች አይቪ ኤድስ፥ ወባና የመሳሰሉ በሽታዎችን ስርጭት መቀነስ።ግብ ሰባት የአካቢ ጥበቃን ዘላቂነት ማረጋገጥ፥ ግብ ስምንት የልማት ትብብርን ማጠናከር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ጊ ሙን ከሁለት አመመት በፊት በተገቢዉ አቅጣጫ እየተጓዝን ነዉ ብለዉ ነበር።

«በተገቢዉ መንገድ እየተንቀሳቀስን ቢሆንም በሚፈለገዉ ፍጥነት እየተጓዝን ግን አይደለም።ከሰሐራ በስተደቡብ ባሉት ሐገራት በ1990 እና 2005 መካከል የድሐዉ ቁጥር እያሻቀበ ነዉ።ሕፃናትና ልጃገረዶች አሁንም በጤና፥ በትምሕርት፥ በሥራ እድል እና በሥልጣን አድሎዎ ይደርስባቸዋል።»

እቅዱ በፀደበቀበት ወቅት ከ1.1 ቢሊዮን በላይ የአለም ሕዝብ የቀን ገቢ ከአንድ ዶላር በታች ነበር።ከእቅዱ በሕዋላ የቻይና እና የሕንድን የመሳሰሉ ሐገራት የድሐ ሕዝብ ቁጥር በጅጉ ቀንሷል።በነዚሕ ሐገራት የደሐዉ ሕዝብ ቁጥር የቀነሰዉ ግን የአመአቱ ግብ ገቢር በመሆኑ ሳይሆን ሐገራቱ በየራሳቸዉ እቅድ ባሳዩት የምጣኔ ሐብት እድገት ነዉ።የተቀረዉ አለም በተለይ አፍሪቃ ባለፈዉ አስር አመት የአንድ በመቶ እድገት አሳይታለች።

MDG Indien Bildung 2

ትምሕርት ለሁሉም

በአለም ባንክ ጥናት መሠረት አፍሪቃ ዉስጥ በ1981 231 ሚሊዮን ሕዝብ ደሐ ነበር።አሁን ወደ አራት መቶ ሚሊዮን አሻቅቧል።የአለም የሕፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ እንደሚለዉ የእቅዱ አስረኛ አመት ዛሬ ሲዘከር በየቀኑ ሃያ-አራት ሺሕ ሕፃናት ወይም ልጆች በረሐብና በድሕነት-ይሞታሉ።

ትምሕርትን ለማዳረስ ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳድ ደሐ ሐገራት በመጠኑ እድገት አሳይተዋል።አንድ መቶ ሚሊዮን ሕፃናት ግን የመማር እድል አያገኙም።ስምንት መቶ ሚሊዮን ጎልማሶች ማይም ናቸዉ።ከነዚሕ ዉስጥ ሰወስት-አራተኛዉ አፍሪቃዊ ነዉ።ሩዋንዳ ብዙ ሴት የምክር ቤት አባላት አላት።ሌላዉ ግን በነበረበት ነዉ።የኤድስ፥ የወባ፥ የሳንባ ነቀርሳ ስርጭትን ለመቀነስ ብዙ ገንዘብ ፈሷል።ብዙም ተሞክሯል።ለዉጥም አለ።

በሁለት ሺሕ ስምንት ብቻ ግን እድሜያቸዉ ከአምስት አመት በታች የሆነ 8.8 ሚሊዮን ሕፃናት ሞተዋል።ከግማሽ የሚበልጡት አፍሪቃዉያን ናቸዉ።እንደ እቅዱ እነ ጊልዶፍ እንደዘመሩት ድሕነት-በሽታን ታሪክ ማድረግ ይቻል ነበር።ግን የድሕነት፥ በሽታ፥ ረሐብ የነገሰባት አፍሪቃ በሙስና በተዘፈቁ፥ አምባገኖነኖች፥ ሥልጣንን የሙጥኝ ባሉ ጨካኞች እየተገዛች አፍሪቃዊዉ ድሕነትን፥ ጦርነት እልቂትን የሚሰናበት መንገድ ብልሐት ተስፋ መኖሩ በርግጥ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።

ቃል-የእምነት እዳ ቢሆን ኖሩ የበለፀገዉ አለም ማድረግ የነበረበትን ማድረግ ባልገደደዉ ነበር።እቅዱን ገቢራዊ ለማድረግ የበለፀገዉ አለም ከገባዉ ቃል አንዱ እስከ 2015 አመት ባለዉ ጊዜ ከአጠቃላይ አመታዊ ገቢዉ 0.7 ከመቶዉን ለልማትተራድኦ መስጠት ነበር።ለእቅዱ የተያዘለት ጊዜ ሊጠናቀቅ አምስት አመት ቀረዉ።እስካሁን ቃላቸዉን ገቢር ያደረጉት ግን አራት ሐገራት ብቻ ናቸዉ።ዴንማርክ፥ላክስምበርግ፥ ኔዘላንድስ እና ሲዊድን በቃ።

የቀድሞዋ የኔዘርላንድ የልማት ተራድኦ ሚንስትርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአመአቱ ዘመቻ መስራች ወይዘሮ ኤቬሊን ሔርፍኬኒስ የበፀገዉ አለምን ቃል-ገብቶ እንደገና ቃል የመግባት አባዜ አሳዛኝ ከማለት ሌላ ሌላ ቃል አላገኙለትም።
------------------------------------------------------------

እንደ እስከዛሬዉ ሒደት እቅዱ ከቅድ ማለፉ አጠራጣሪ ነዉ።ኮፊ አናን የዛሬ አስር አመት የአለምን ሕዝብ መፃ እድል የምትወስኑ በሚል ትክክለኛ ሐረግ የገለፁዋቸዉ መሪዎች ዛሬም የአለምን ሕዝብ መፃኤ እድል ለመወሰን እንደገና ጉባኤ ላይ ናቸዉ።እንደገና ለእቅዱ ገቢራዊነት እንደገና ቃል-ይገቡ ይፈርሙ ይሆናል።ድሕነት፥ ረሐብ፥ በሽታ-ማይምነትም ቃል-እያስገባ ሕዝብ ይጨረሳል።ሌላ ዘመን ሌላ ቃል-ሌላ እልቂት።ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ


Audios and videos on the topic