የአልጀሪያውያን ተቃውሞና ፈረንሳይ ያሉ አልጀሪያውያን | አፍሪቃ | DW | 09.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአልጀሪያውያን ተቃውሞና ፈረንሳይ ያሉ አልጀሪያውያን

ዩናይትድ ስቴትስ በአልጀሪያ ለአምስተኛ ጊዜ ምርጫ እወዳደራለሁ ባሉት የ82 ዓመቱ ፕሬዚደንት ላይ የተጠናከረውን ተቃውሞ ከጀርባ ትደግፋለች። ከአልጀሪያ ጋር ለዘመናት ስሟ የተቆራኘ አንዲት ሀገር ግን ተቃውሞውን ዐይቶ እንዳላየ፤ ሰምቶ እንዳልሰማ «ጆሮ ዳባ ልበስ» ብላለች። ያቺ ሀገር ባንድ ወቅት አልጀሪያን ቅኝ የገዛችው አውሮጳዊቷ ፈረንሳይ ናት።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:36

«ፕሬዚደንቱ ዝምታውን መስበር አለባቸው»

ዩናይትድ ስቴትስ በአልጀሪያ ለአምስተኛ ጊዜ ምርጫ እወዳደራለሁ ባሉት የ82 ዓመቱ ፕሬዚደንት ላይ የተጠናከረውን የመንግሥት ተቃውሞ ከጀርባ ትደግፋለች። ከአልጀሪያ ጋር ለዘመናት ስሟ የተቆራኘ አንዲት ሀገር ግን ተቃውሞውን ዐይታ እንዳላየች፤ ሰምታ እንዳልሰማች፦ «ጆሮ ዳባ ልበስ» ብላለች።  ያቺ ሀገር ባንድ ወቅት አልጀሪያን ቅኝ የገዛችው አውሮጳዊቷ ፈረንሳይ ናት። ለበርካታ አልጀሪያውያን ኹለተኛ ሀገር የኾነችው ፈረንሳይ መዲናይቱ አልጀርስ ከከተሙ ባለሥልጣናት ጋር እሰጥ-አገባ ላለመግባት የቆረጠች ትመስላለች።

ኑሯቸውን ፈረንሳይ ውስጥ የመሰረቱ አልጀሪያውያን ባለፈው ሳምንት አደባባይ ተመው ነበር። ለተቃውሞ ሰልፍ የመውጣታቸው ሰበቡ ደግሞ የሀገራቸው ሰዎችን የተቃውሞ ድምፅ ከሜዲትራንያን ባሕር ባሻገርም ለማስተጋባት ነው። የፈረንሳይ መንግሥት መቀመጫ የኾነው የኤሊዜ ቤተ-መንግሥት ተቃውሞ ሰልፈኞቹ ከወጡበት አደባባይ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ቢርቅ ነው። የአልጀሪያውያኑ የተቃውሞ ድምጽ ግን በቅጡም የተሰማም አይመስል።

Algerien - Präsident Macron in Algiers

የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ በአልጀሪያ ጉብኝታቸው ወቅት፤ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2017 ዓ.ም

ፕሬዚደንት ኤማኔኤል ማክሮ ወትሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ድምፃቸው ጎላ ብሎ ሲሰማ ነው የሚስተዋለው። ላቲን አሜሪካ የምትገኘው ቬኔዙዌላ ተቃዋሚን ከመደገፍ እስከ አውሮጳ ኅብረት መጠናከር  ሲናገሩ አይታክታቸውም። ኾኖም የአልጀሪያው አዛውንት ፕሬዚደንት አብዱልአዚዝ ቡተፍሊካ ለተጨማሪ የፕሬዚደንትነት የሥልጣን ዘመን እወዳደራለሁ ሲሉ ባለፈው እሁድ ይፋ ሲያደርጉ ፈረንሳይ አጭር መግለጫ ከመስጠት አልዘለለችም። «የራሳቸውን መንግሥት በነፃነት መምረጥ እና የወደፊት እጣ መወሰን መብት አላቸው» ይላል አልጀሪያውያኑ ተቃዋሚዎችን የሚመለከተው ቁጥብ መግለጫ።

የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ዦን ይቬ ሎ ዶሬይ መንግሥታቸው ስለ አልጀሪያውያን በበቂ ኹናቴ አልተናገሩም ሲሉ ባለፈው ረቡዕ ምክር ቤት ውስጥ ቅሬታ አሰምተዋል። ሀገራቸው ፈረንሳይ ፦ «አልጀሪያ ሉዓላዊ ሀገር ናት» ከማለት አለመዝለሉ የከነከናቸው ይመስላል። በበኩላቸው የአልጀሪያ ምርጫ ነጻ እና ግልጽ መኾን ይገባዋል ሲሉ በምክር ቤቱ አስጠንቅቀዋል።

የሰሜን አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኟ ከድጃ ሙኅሴን ፊናን የኤማኑዌል ማክሮ መንግሥት አካባቢውን በብልጣብልጥነቱ መተንተኑን ይዘልቅበታል ባይ ናቸው።

«መንግሥቱ በእርግጥም ከተንኮታኮተ እጅግ የሚደንቅ ነው የሚኾነው። በዚህ አጋጣሚ ከሕዝቡ ጋር መወገን የግድ ነው። አለያስ መንግሥቱ ከወደቀበት ትብያም ይነሳ ይኾን

Frankreich - Algerias Präsident Abdelaziz Bouteflika in Krankenhaus in Frankreich

የአልጀሪያው ፕሬዚደንት አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 ዓ.ም በፈረንሳይ ሐኪም ቤት

ፈረንሳይ በዚህ ቀውጢ ወቅት እጇን ከአልጀሪያ የመሰብሰቧን ምክንያት ለመተንተን በኹለቱ ሃገራት መካከል የነበረውን ታሪካዊ ግንኙነት መቃኘት በከፊል ይረዳል።  እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1962 ያከተመውን የአልጀሪያ ቅኝ አገዛዝ በይፋ ይቅርታ ላለመጠየቅ በተከታታይ የመጡ የፈረንሳይ መሪዎች ዳር ዳር ሲሉ 130 ዓመታትን አስቆጥረዋል። በብዙ ደም ክፍያ ከተገኘው የአልጀሪያ ነጻነት በኋላ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1990ዎቹ አልጀሪያ በመንግሥት ወታደሮች እና እስላማዊ አማጺያን የእርስ በእርስ ጦርነት ስትዘፈቅ ፓሪስ ድምጿን ዝቅ አድርጋ ቆይታለች። እንዲያም ኾኖ ግን በእንግሊዝኛ ምኅጻሩ (GIA) የሚሰኘው እስልምና አክራሪው ታጣቂ ቡድን ፈረንሳይ ለአልጀሪያ መንግሥት ወግናለች በሚል ፓሪስ ላይ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን ሰንዝሯል። 

«በአልጀሪያ ወቅታዊ ኹኔታ የፈረንሳይ ዝምታን በግሌ እረዳለሁ። ያለፈው የቅኝ ግዛት ግንኙነት በፈረንሳይ እና አልጀሪያ መንግሥታት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ስሱ እንዲኾን አድርጎታል።»

ብራሂም ዖማንሱር ፓሪስ ውስጥ የሚገኘው የፈረንሳይ ስልት ቀያሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም የሰሜን አፍሪቃ ጉዳዮች ተንታኝ ናቸው።

«አኹን ካለው መንግሥት አለያም ከፕሬዚደንት ማክሮ የሚደረግ ማናቸውም ንግግር በአልጀሪያ መንግስትም ኾነ በሕዝቡ ዘንድ እንደ ጣልቃ-ገብነት ሊተረጎም ይችላል።»

ኢማኑዌል ማክሮ በገዛ ቤታቸው ያለው ጉዳይም ያሳስባቸዋል። የዛሬ ሁለት ዓመት ለፕሬዚደንትነት ሲወዳደሩ የፈረንሳይ የቅኝ ግዛት ዘመንን በተመለከተ ባሰሙት ንግግር፦ የአልጀሪያ ወረራ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው ማለታቸው ብርቱ ወቀሳ እና ትችት አስከትሎባቸዋል።

Algerien Algier - Polizei nimmt Demonstranten fest während Proteste gegen Abdelaziz Bouteflika

አልጀሪያ መዲና አልጀርስ፦ ፖሊሶች የፕሬዚደንት አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ ተቃዋሚ ሰልፈኛን ይዘው ሲሄዱ

 

ንግግሩን ባሰሙ በዓመቱ አልጀሪያ ተጉዘው ባሰሙት ሌላኛው ንግግራቸው፦ ከአልጀሪያ ጋር አዲስ ምእራፍ መከፈቱን በማብሰር አልጀሪያውያን ወጣቶች የወደፊቱን ተስፋቸውን እንዲመለከቱ አሳስበዋል።  ዛሬ አልጀሪያ ስልታዊ ጥቅም ያላት ሀገር ኾናለች። ያም ለፈረንሳይ እና ለአውሮጳ በምትልከው ጋዟ ብቻ ሳይኾን፤ በሳኅል ቃጣና ባላት ወታደራዊ ትብብር ጭምር ነው።

«በአካባቢው በተለይም በሣኅል ቃጣና ሽብርተኝነትን በመዋጋት፤ ብሎም በዋናነት ከሣህራ በታች ካሉ ሃገራት በሚፈልሱ ስደተኞች የሚፈጠረውን የፍልሰት ቀውስ በመቆጣጠር ረገድ ቊልፍ አጋር ናት።»

ፈረንሳይ ከነፃነት ዘመን አንስቶ አልጀሪያ ውስጥ የሥልጣን መዋቅሩ ላይ መረጋጋት እንዲኖር በብርቱ መንቀሳቀሷን ቀጥላበታለች። ኾኖም ያ በራሱ ብቻ ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ብሎም አደባባይ ከወጡ አልጀሪያውያን ጎን እንዲቆሙ በሃያሲያን ዘንድ ከመወትወት አልታደጋቸውም።   በድጋሚ የፖለቲካ ተንታኟ ሞኅሲን ፊናን የሚሉት አላቸው።

«የውጭ ሀገር ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ላለመግባት በሚል መሸሸግ አይቻልም። ፕሬዚደንቱ ዝምታቸውን ሰብረው ነገሮችን በግልጽ መናገር ያሻቸዋል።»

ፕሬዚደንቱ ዝምታን ቢመርጡም ፈረንሳይ ውስጥ ግን ጎላ ብሎ የሚሰማ ድምፅ አለ፤የአልጀሪያ ዲያስፖራዎች ድምፅ። እንደ ባለሞያዎች ገለጣ ከኾነ ጥምር ዜግነት የያዘውም ሕገወጡ ስደተኛም ተደምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አልጀሪያውያን ፈረንሳይ ውስጥ ይኖራሉ። ጀማል ማይዲኔ ያለፈው ሳምንት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተሳትፎ ነበር። እትብቱ የተቀበረው አልጀሪያ ውስጥ ነው ፈረንሳይ መኖር ከጀመረ ግን ዐሥርተ-ዓመታትን አስቆጥሯል።

Algerien Algier - Proteste gegen Abdelaziz Bouteflika gegen weitere Amtszeit

የፕሬዚደንት አብደአዚዝ ቡተፍሊካ ተቃዋሚዎች በመዲናይቱ አልጀርስ እምብርት የሚገኘው ሐርቻ አዳራሽ ፊት ለፊት

«ፈረንሳይ የአልጄሪያ ሕዝብ ከእነዚህ ማፊያዎች እንዲላቀቅ ርዳታ ልታደርግ ያስፈልጋታል። የፈረንሳይ መንግሥት ስለኛ ሊረዳ ይገባዋል። ሺህዎች ሳንኾን ሚሊዮኖች ነን።»

ያስሚን ቦዋቺ ፈረንሳይ ከአልጀሪያ መንግሥት ጋር ያላትን ግንኙነት መበጠስ የሚያሻት ጊዜ አኹን እንደኾነ ይስማማሉ።

«የፈረንሳይ መንግሥት አኹን ያለውን የኃይል አገዛዝ ይደግፋል። ይኼ እውነታ ነው። ማንም ስለዚኢ ምንም ያለው ነገር የለም ግን ሁላችንም የምናስበው ያንን ነው።»

ያስሚን ቦዋቺ፦ ሊመጣ የሚችለውን በመፍራት ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ እና የፈረንሳይ መንግሥት ወገንተኛ መኾናቸውን እንዲያቆሙ አበክረው ይመክራሉ፤ ያ በእርግጥ የመኾን እድሉ አጠራጣሪ ቢኾንም ማለት ነው። የፈረንሳይ መንግሥት ዝምታንም ይተቻሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተስፋለም ወልደየስ

Audios and videos on the topic