የአልቃይዳ የቦንብ ጥቃት በአልጀሪያ | አፍሪቃ | DW | 12.12.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአልቃይዳ የቦንብ ጥቃት በአልጀሪያ

ማክሰኞ ታህሳስ አንድ በአልጀሪያ ዋና ከተማ አልጀርስ በመኪና ላይ የተጠመዱ ሁለት ተከታታይ የቦንብ ፍንዳታዎች የሠባ ሁለት ሰዎችን ህይወት ቀጠፉ።በጥቃቱ የአልቃይዳ እጅ እንዳለበት የአልጀሪያ ባለስልጣናት ገልፀዋል።

የአልቃይዳ ጥቃት

የአልቃይዳ ጥቃት

በትላንቱ የአልጀርሱ ፍንዳታ ከስልሳ እስከ ሰባ የሚጠጉ ሰዎች ሲያልቁ፤ሁለት መቶ ሰዎች መቁሰላቸውም ታውቓል።የአልጀሪያ የአገር ውስጥ ሚንስትር ኑረዲን ያዚድ ዜርሆኒ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም፤ለጥቃቱ የአልቃይዳ አንዱ ቅርንጫፍ የሆነውና በሰሜን አፍሪቃ የሚንቀሳቀሰው እስላማዊ የማግሬብ ቡድን ኃላፊ እንደሆነ ገልፀዋል።

የማግሬብ እስላማዊ ቡድን እ.ኤ.አ. በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያዎቹ አፍጋኒስታን ከሶቪይት ኍብረት ጋር በነበራት ጦርነት ከሰሜን አፍሪቃ በተጓዙ ሙጂሀዲስቶች የተቓቓመ ነው።እነዚህ ራሳቸውን የቅዱስ ጦርነት ተፋላሚዎች ብለው የሚጠሩ የሰሜን አፍሪቃ ተወላጆች እ.ኤ.አ. በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ዓ.ም. ሶቪይት ኍብረት አፍጋኒስታንን ለቃ ስትወጣ ወደ ሰሜን አፍሪቃ በመመለስ የማግሬብ እስላማዊ ቡድንን አቓቁመዋል።የአልጀሪያው ቅርንጫፍ ሣላፊስተን ሲሰኝ፤በዋናነት የሚንወሳቀሰውም በአልጀሪያ እስላማዊ መንግስትን ለመመስረት ነው።

የማግሬብ ኢስላማዊ ቡድን ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት ከአልጀሪያ መንግስት ጋር ለገጠመው ግብግብ ቢያንስ የአንድ መቶ አምሳ ሺህ ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል።የትላንትናዎቹ ሁለት የመኪና ላይ አጥፍቶ ጠፊ ፍንዳታዎች በዋናነት ኢላማ ያደረጉትም የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ፅህፈት ቤት ህንፃ እና የአልጀሪያ ከፍተኛው ፍርድ ቤትን ነበር።

ትላንት የአጥፍቶ ጠፊዎች የቦንብ ጥቃት በርካታ ሠላማዊ ሰዎችን ሲጨርስ ዕለቱ እ.ኤ.አ. ዴሴምበር አስራ አንድ ነበር።በአፕሪል አስራ አንድ ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ መኪና ላይ የተጠመዱ ሁለት የቦንብ ጥቃቶች በዚህችው ዋና ከተማ አልጀርስ ላይ ነጉደው በርካታ ሰዎችን ፈጅተዋል።ሌላኛው የማግሬብ ቡድን በቱኒዚያ ባደረሠው የቦንብ ጥቃት በርካታ ሰው ያለቀውም በዚችው መከረኛ ቀን በዕለተ አስራ አንድ በፈረንጆቹ አፕሪል ሁለት ሺህ ሁለት ነበር።የስፔን ማድሪዱ የሁለት ሺህ አራት ጥቃትም እንዲሁ ማርች አስራ አንድ ነበር።

ዋነኛውና ከመላው ዓለም አዕምሮ እንዲህ በቀላሉ የማይጠፋው የዩናይትድ ስቴትሱ የአሸባሪዎች ጥቃት የደረሰውም እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር አስራ አንድ ሁለት ሺህ አንድ ነበር።ምናልባትም ይህች የፈረንጆቹ ወራት አስራ አንደኛ ቀን ለኦሳማ ቢን ላዲን የአሸባሪዎች መረብ ልዩ ትርጉም ይኖራት ይሆንን?