1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአላማጣ ሰሞናዊ የፀጥታ ሁኔታ

ሰኞ፣ ሰኔ 10 2016

“ከትናንት ወዲያ ሌሊት ላይ አስፋልት ዳር ያለውን የቀበሌ 3 መሰብሰቢያ አዳራሽ ገብተው አድረዋል፣ ያ ቦታ ዋናውን አስፋልት መንገድ የሚዘጋ፣ እዛ አካባቢ ያለውን የ3 ቀበሌዎች ነዋሪዎች አዋሳኝ ቦታ በመሆኑ ወጣቱ ስጋት አድሮበታል“

https://p.dw.com/p/4h8vP
የአላማጣ ከተማ በከፊል
የአላማጣ ከተማ በከፊልምስል Fikru Eshsiebel

የአላማጣ ሰሞናዊ የፀጥታ ሁኔታ

በራያ አላማጣ ከተማ በህወሓት ታጣቂዎችና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ውጥረት መኖሩን ነዋሪዎችና የአላማጣ ከተማ አስተዳደር አስታውቀዋል፣ የደቡባዊ ትግራይ አስተዳዳሪ ደግሞ “ህገወጥ” ያሉት አስተዳደር መፍረሱንና አካባቢው አሁን የሚያስተዳድረው አካል  የለውም ብለዋል፡፡
ከጥቅምት 2013ቱ የሰሜኑ ጦርነት በኋላ በአማራ ክልል አስተዳደር ስር የነበረውንና የትግራይና የአማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸውን የራያ አላማጣና አካባቢውን የትግራይ ኃይሎች ካለፉት 2 ወራት ወዲህ ተቆጣጥረዋል፡፡
የራያ አላማጣ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በአካባቢው የትግራይ ታጣቂዎች ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንደሚፈፅሙ በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡
ሰሞንን ደግሞ በከተማዋ የሚገኝን አንድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የትግራይ ታጣቂዎች መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ሌላ ውጥረት በከተማዋ መፈጠሩን አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
“ከትናንት ወዲያ ሌሊት ላይ አስፋልት ዳር ያለውን የቀበሌ 3 መሰብሰቢያ አዳራሽ ገብተው አድረዋል፣ ያ ቦታ ዋናውን አስፋልት መንገድ የሚዘጋ፣ እዛ አካባቢ ያለውን የ3 ቀበሌዎች ነዋሪዎች አዋሳኝ ቦታ በመሆኑ ወጣቱ ስጋት አድሮበታል፣ ከትናንት ጀምሮ አስፋልቱን በዝጋት አስወጡልን የሚል ጥያቄ እያነሳ ነው ያለው፣ አስፋልቱ እስከ ማታ ዝግ ነው የነበረው፣ ዋጃ ላይና አላማጣ ላይ ዛሬም ቀጥሏል፡፡
የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ኃይሉ በበኩላቸው በከተማዋና አካባቢው ያለውን የሰብአዊ ጥሰት በመቃወም ወጣቶች መንገድ ዘግተው ጥያቂያቸው ባግባቡ ምላሽ እንዲሰጠው እየጠየቀ መሆኑን አረጋግጠውልናል፡፡
የወሎ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢና የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራም በራያ አላማጣ ነዋሪዎች ላይ የሚደርሰው ስቃይና ግፍ ቀጥሏል ሲሉ አመልክተዋል፡፡
“መሳሪያ እየያዙ ከነትጥቃቸው፣ ከተማ እገቡ ሰው እያፈኑ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው፣ ዝርፊያም እከናወኑ ነው፣ የዛቻና የማስፈራሪያ መልዕክት ያለው ወረቀትም እየበተኑ ነው፣ ስለዚህ ህዝቡ ተሰባስቦ ከዚህ ከተማ ውስት የገባው ኃይል ይውጣልን መውጣት ካልቻለ መኪናዎች አናሳልፍም ብሎ መንገድ ዘግቶ ነው ያለው፡፡” ብለዋል፡፡
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ “ህገወጥ” ብለው የጠሩት አስተዳደር አሁን በአካባቢው እንደሌለ ጠቁመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በራያ አላማጣ አካባቢ እንዲያወም ተሸሽሏል ነው ያሉት፡፡
በአላማጣ ነዋሪዎችና አስተዳደር የቀረበውን ስሞታ የማይቀበሉት አቶ ሀፍቱ፣ “ በእኛ እምንት ከሁለት ወራት በፊት የነበረው የሰብአዊ መብት ጥሰት እጅግ በጣም አስከፊና... በየቦታው ኬላዎች ተዘርግተው የነበረበት ነው፣ ሰዎች በማንነታቸው በአካባቢው የማይኖሩበት፣ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፣ አሁን የተወሰነ መሻሻል እየታየ ነው፡፡” ሲሉ ነው ለዶይቼ ቬሌ ያስረዱት፡፡
አሁን የራያ አላማጣ አካባቢ በየትኛውም አካል አይተዳደርም ያሉት አቶ ሀፍቱ ይህ ይህም በመሆኑ በአካባቢው አገልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ብለዋል፡፡
“አንዳንድ ሁኔታዎች አሉ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርም ቢሆን ከዚህ በፊት ከነበረው “ህገ ወጥ ነው” ተብሎ ከፈረሰው አስተዳደር በኋላ የህዝብ አስተዳደር ስሌለለ በዚህ ምክንት የተፈጠሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች አሉ፣ የህክምና፣ የትምህርት ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ አይደለም... አካባቢውን አሁን ማንም አያስተዳድረውም፡፡”
በወቅቱ የነበረው የጦርነት ሁኔታ በፈጠረው አጋጣሚ “ህግወጥ” ያሉት አስተዳደር ተመስርቶ እንደነበር የገለፁት አቶ ሀፍቱ በወቅቱ ከፌደራል መንግስት በጀት ሳይመደብለት በአማራ ክልል መንግስት በጎ ፈቃድ እገዛ ይደረግለት ነበር ብለዋል፣ ያ ማለት ግን አካባቢውን  የአማራ ክልል መንግስት ያስተዳድረው ነበር ማለት አይደለም  ነው ያሉት፡፡
በአከባቢው የተረጋጋ አስተዳደር እንዲዘረጋና ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ግልጋሎት እንዲያገኝየፕሪቶሪያው ስምምነትእንዲተገበር የፌደራሉ መንግስት ግፊት እንዲያደርግም አቶ ሀፍቱ ጠይቀዋል፡፡
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸውን አካባቢዎች በህገመንግስቱ መሰረት እንዲፈቱ ሁለቱ አካላት መስማማታቸውን የሚያትት ነው፡፡ከአማራ ክልል በኩል ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግሁት ጥረት አልተሳካም፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
አዜብ ታደሰ