የአላሙዲ መፈታትና ካርታው | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 01.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የአላሙዲ መፈታትና ካርታው

ከአንድ ዓመት በላይ በሳዑዲ እስር ቤት የቆዩት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ቱጃር ሼህ መሀመድ አላሙዲ መፈታት በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለያዩ ስሜቶችን ፈጥሯል። ኢትዮጵያውያን ደማቅ ድል በተጎናጸፉበት የዱባይ ማራቶን ከደጋፊዎች መሀል ከፍ ተደርጎ የታየው የኢትዮጵያ ካርታ በርካታ ትውልደ-ኤርትራውያንን አስቆጥቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:32

በዱባይ ማራቶን የኢትዮጵያ ካርታ ውዝግብ ፈጥሯል

ከአንድ ዓመት በላይ በሳዑዲ እስር ቤት የቆዩት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ቱጃር ሼህ መሀመድ አላሙዲ መፈታት በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለያዩ ስሜቶችን ፈጥሯል። ሼሁ ለሀገር ጠቅመዋል የሚሉ የመብዛታቸውን ያኽል፤ የለም ከቀደመው አስተዳደር ጋር አብረው ሕዝቡን በድለዋል የሚሉ ሐሳቦች ተበራክተዋል። ኢትዮጵያውያን ደማቅ ድል በተጎናጸፉበት የዱባይ ማራቶን ከደጋፊዎች መሀል ከፍ ተደርጎ የታየው የኢትዮጵያ ካርታ በርካታ ትውልደ-ኤርትራውያንን አስቆጥቷል። አስተያየቶችን አሰባስበናል፤

የአላሙዲ መፈታት

የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ቱጃሮች አንዱ ናቸው። ያን ሰሞን፦ ከሦስት ወር እስር በኋላ ገሚሶቹ መፈታት እንደጀመሩ እሳቸውም ሊለቀቁ ነው ተብሎ ለአንድ ዓመት እስር ቤት ቆይተዋል፤ ኢትዮጵያዊው ቱጃር ሼህ መሀመድ አላሙዲ። ከአንድ ዓመት ከሦስት ወር እስር በኋላ ከሳዑዲ እስር ቤት የመለቀቃቸው ዜና በዚህ ሳምንት መሰማቱ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለያዩ አመለካከቶች እንዲንጸባረቁ አድርጓል።

ሼሁን የሚቃወሙ አስተያየት ሰጪዎች፦ ቱጃሩ ከሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አመራር ጋር ጥብቅ ቅርርብ ነበራቸው፤  ከወቅቱ አስተዳደር ጋርም ከፍተኛ ሙስና ፈጽመዋል ሲሉ ጠንካራ ትችት ይሰነዝራሉ። አስተያየት ሰጪዎች ሼሁ ፈጽመውታል ላሉት ወንጀል ኢትዮጵያ ውስጥም እስር ይገባቸዋል ሲሉ ይሞግታሉ።

አክቲቪስት እና የፖለቲካ ተንታኝ ጀዋር መሐመድ በትዊተር ገጹ፦ «አል አሙዲ በዘረፋ ሳዑዲ እስር ቤት ውስጥ ተከርችሞበት ነበር። ጠቅላላው መንግሥት በቁጥጥሩ ስር በነበረበት ወቅት ከኢትዮጵያ ምን ያኽል ዘርፎ እንደነበር አስቡት? ከቦሌ አየር ማረፊያ እጁን አስራችሁ የሜቴክ ተባባሪዎቹን እንዲቀላቀል ውሰዱት» ሲል ጽፏል።

ከጀዋር ሐሳብ በተቃራኒው፦ ቱጃሩ ሼህ መሀመድ አላሙዲ ለኢትዮጵያ ውለታ ፈጽመዋል እና ሊብጠለጠሉ አይገባም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም በርካታ ናቸው። ሼህ መሀመድ አላሙዲ የብዙ ኢትዮጵያውያን እንጀራ ፈጣሪ ናቸው፤ ሳዑዲ ውስጥ የታሰሩትም «በስልጣን ጥመኛው ልዑል ነው» የሚሉ አስተያየቶች ታይተዋል። አስተያየት ሰጪዎች፦ ሼሁ ከወያኔ ጋር በነበራቸው የጥቅም ግንኙነት ይታሰሩ የሚሉ በአሁኑ አስተዳደር ውስጥ አመራር የኾኑ ሰዎችም ይታሰሩ ሊሉ ይገባል የሚሉና ሌሎች መከራከሪያ ሐሳቦችን ሰንዝረዋል።

በብሪታንያ የኬል ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር ዶ/ር አወል አሎ የሼህ አል አሙዲ አሰተዋጽዖን በትዊተር ገጹ አጉልቶ ጽፏል። «አል አሙዲ ከወሰደው ይልቅ የበዛ ሐብት ለኢትዮጵያ አምጥቷል። ከቀደመው መንግስት ጋር ግንኙነቱ ምንም ይኹን ምን፤ ከሚያገኘው የበለጠ ሰጪ ነው። መሠሪ አክቲቪዚምህን አቁም» ሲልም የተቃውሞ ሐሳብ ሰንዛሪዎችን ተችቷል። 

እንዳልካቸው ጫላ በበኩሉ፦ «አላሙዲ የህዝባችንን ሃብት ዘርፎ እና የአከአባቢ ውድመት አድርሶ የሚጠበቅበትን የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት ስላልተወጣ በሕግ ይጠየቅ የሚሉ ሰውየው “ሲዘርፍ” ፈቅደው ያዘረፉት ባለስልጣናት ይታሰሩ ሲሉ አልሰማሁም» በማለት ጽፏል። ፈቅደው ያዘረፉ ያላቸውን ባለሥልጣናት ስም ዝርዝርም ጠቅሷል።

አባቦራ በሚል የትዊተር ተጠቃሚ ለእንዳልካቸው በሰጠው መልስ «የአላሙዲን መታሰር ለየትኛው ችግር መፍትሄ እንደሚሆን አልገባኝም። ሰውዬው ይታሰር ቢባል እንኳን ከርሱ በፊት የሚመጡ ብዙ ወንጀለኞች አሉ። ለTPLF ስላጎበደደ ብቻ ይታሰር ማለት ኢፍትሀዊነት ነው» ብሏል።

«የሼኽ ሞሐመድ አላሙዲ መፈታት መልካም ዜና ነው። ወደ ሀገሩም መምጣትና መስራትም መብቱ ነው። ለውጡን ለመቀልበስ ከሚሞክሩ ሀይሎች ራሱን ማራቅ ይኖርበታል። አለበለዚያ ፀቡ ከህዝብ ጋር ይሆናል። እንደ ድሮ ተራ ፀብ የሚሆን አይመስለኝም» የኪያ ጸጋዬ አስተያየት ነው።

አል አሙዲ የኢትዮጵያ ባለውለታ ናቸው እና የሀገሪቱ በዝባዥ በሚሉ ኹለት ጎራዎች ተከፍለው የተሰጡ አስተያየቶች በርካታ ቢኾኑም፤ የአብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች ሐሳብ ከላይ በቀሩበት ተቃራኒ ሐሳቦች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው።

አወዛጋቢው ካርታ

ሌላው በሳምንቱ መንደርደሪያ ላይ የብዙዎችን ቀልብ ገዝቶ ያነጋገረው ጉዳይ አርብ ጥር 17 ቀን፤ 2011 ዓ.ም. በተባበሩት አረብ ኤመሬት ዱባይ ከተማ የተካሄደው የዱባይ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ነው። በዓለም አቀፉ አትሌቲክሰ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የዱባይ ማራቶን ለ20ኛ ጊዜ በተከናወነበት ዕለት ከኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች መሀል ከፍ ተደርጎ የተያዘ የኢትዮጵያ ካርታ በርካታ ኤርትራውያንን አበሳጭቷል።

በእለቱ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተከታታይ በመግባት እንደተለመደው ለድል የበቁበት ሲኾን፤ በተለይ አትሌት ጌታነህ ሞላ 2 ሰዓት ከ3 ዲቂቃ ከ34 ሰከንድ  ሮጦ በመግባት ክብር ወሰን ሰብሮ ደጋፊዎቹን አስፈንጥዟል። በዕለቱ በርካታ ደጋፊዎች አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን በማውለብለብ ደስታቸውን ገልጠዋል። ከደጋፊዎች መካከል ግን አንድ ደጋፊ አረንጓዴ፤ ቢጫ ቀይ ቀለም የተቀባ የኢትዮጵያ ግዙፍ ካርታን ከፍ አድርጎ ታይቷል። ካርታው ኤርትራንም አጠቃሎ የያዘ ነው።

ይኽ ካርታ ያለበት ፎቶግራፍን ብሪታንያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በትዊተር ገጹ ላይ ማውጣቱ ነበር የቁጣው መንስዔ። በርካታ ኤርትራውያን የኤርትራን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ተግባር ነው፤ ኤርትራን ከዓለም ካርታ ላይ ያጠፋ ኾን ተብሎ የሰውን ስሜት ለመፈተሽ የተደረገ ተግባር ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ፦ ፎቶግራፉ ያለበት መልእክትን ከትዊተር ገጹ በማስወገድ ይቅርታ ጠይቋል።  

ኤምባሲው ባሳለፍነው ቅዳሜ በማኅበራዊ የመገናኛ ገጹ ላይ ቀጣዩን መልእክት በእንግሊዝኛ አስነብቧል። «በዱባይ ማራቶን ላይ የኢትዮጵያ ደጋፊዎች የያዙት የተሳሳተ የኢትዮጵያ ካርታ ፎቶግራፍን ዐርብ ዕለት በመለጠፋችን የተነሳ ለተፈጠረው ቁጣ ከልብ ይቅርታ እንጠይቃለን።»  ይላል የኤምባሲው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ። በማኅበራዊ ድረ ገጹ የተለጠፈው ጽሑፍ መነሳቱን፤ መሰል ነገሮች ወደፊት ዳግም እንዳይከሰቱ ለማረጋገጥ አስፈላጊው ርምጃ እንደሚወሰድም ጽሑፉ አክሎ ጠቅሷል።

«ይኽ በግልጽ ሊነገር ይገባል። ኤርትራ ሉዓላዊት ሀገር ናት። እውነታን አጣጣይ ከመኾን እንቆጠብ» ስትል አስተያየቷን ያሰፈረችው ገሊላ ስንታየሁ ናት።

በተቃራኒው ጌታሁን በሚል ስም የትዊተር ተጠቃሚ፦ «የኤርትራውያን ትዊተር እንዲህ ሲንቀለቀል ዐይቼ ዐላውቅም» ሲል ኤርትራውያን ቅድሚያ ሊሰጧቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች በቀጣዩ ጽሑፍ አስነብቧል። «በሺህ የሚቆጠሩ ኤርትራውያን በሜዲትራንያን አለቁ፤ ግድ አይሰጠኝም። በኤርትራ ሥራ የለም፤ አይመለከተኝም። ኤርትራ ውስጥ ጋዝ የለም፤ ምን ጨነቀኝ። ኤርትራውያን ሊቢያ ውስጥ በባርነት ተሸጡ፤ ምን ተዳዬ። የኾኑ ሰዎች የድሮውን የኢትዮጵያ ካርታ ያዙ፤ በንዴት መገንፈል» በማለት ጽፏል።

ዘ ናሽናል የተሰኘውን የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች የድረገጽ ዜና ያያዘው የምስራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ ዮሐንስ ገዳሙ ካርታውን አስመልክቶ ባሰፈረው ጽሑፉ፦ «የኤርትራን ነጻነት ዕውቅና ካለመስጠት ወይንም ክብር ከመንፈግ የተነሳ አይመስለኝም» ብሏል። «ይልቁንስ አንዱ ለአንዱ ካለው ፍቅር የተነሳ ነው» ሲል አክሏል። «በዚያም አለ በዚህ ግን መሰል ስህተቶች ወደፊት እንዳይከሰቱ ማድረግ ተገቢ ነው» ሲል ጽሑፉን አጠቃሏል።

ኤርትራን አጠቃሎ የያዘው የኢትዮጵያ ካርታ በታየበት የዱባዩ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደተለመደው በበላይነት አጠናቀዋል። የዱባይ ማራቶን ለ19 ጊዜት ያኽል ሲካሄድ በወንዶች 12 ጊዜ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሲያሸንፉ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ደግሞ ሦስት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ኾኖ መመዝገቡን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፌስቡክ ገጹ አስነብቧል። በሴቶቹ 14ቱን ውድድሮች ኢትዮጵውያቱ ሲያሸንፉ አትሌት አሰለፈች መርጊያም ለሦስት ጊዜያት በማሸነፍ በውድድሩ ስሟን በደማቅ መፃፍ የቻለች አትሌት መኾኗን ገጹ አክሎ ጽፏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic