የኖቤል ተሸላሚዉ ሙዚቀኛ ዝምታ     | ባህል | DW | 27.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የኖቤል ተሸላሚዉ ሙዚቀኛ ዝምታ   

የኖቤል ተሸላሚዉ ሙዚቀኛ ዝምታ    

የዘንድሮዉ የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ተሸላሚ አሜሪካዊዉ ድምፃዊና ገጣሚ ቦብ ዳይላን ፤ የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ አሸናፊነታቸዉን ካሳወቀ ጊዜ ጀምሮ ይኸዉ እስካሁን ፤ ከተደበቁበት አልወጡም ያገኛቸዉም የለም። መገናኛ ብዙኃን ግን ስለመሰወራቸዉ የተለያዩ የሥነ-ጽሑፍ ሰዎችን፤ የሚመለከታቸዉን ምሁራኖች አስተያየትን በመጠየቅ ይጽፋሉ። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:43
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
14:43 ደቂቃ

ቦብ ዴይላንና የኖቤል ሽልማት

 

«ጥሩ ሥነ-ጽሑፍ አቅርቡና አንድ ሚሊዮን ዶላር ትሸለማላችሁ የሚል ማስታወቂያ ቢወጣ ምናልባትም በርካታ የዓለማችን የሥነ-ጽሑፍ  ባለሞያዎች ሥራዎቻቸዉን ያቀርቡ ነበር » ይላል፤ ሮይተርስ በድረ-ገጹ ትናንት ያስነበበዉ የጽሑፍ መንደርደሪያ። ጤና ይስጥልኝ አድማጮች እንደምን አመሻችሁ፤ እዉቅ የተባሉ የዓለም የብዙኃን መገናኛዎች የዘንድሮ የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ተሸላሚ ቦብ ዴይላን ደብዛ መጥፋት በግርምት ብሎም ለሙዚቀኛ የኖቤል ሽልማት ሲሉ በምጸት የተለያዩ መጣጥፎችን እያስነቡ ይገኛሉ። በዚህ ዝግጅታችን ስለ ቦብ ዴይላን ደብዛ መጥፍት በተመለከተ የተጻፉትን ጽሑፎች እያየን የእዉቁን ሙዚቀኛ ገጣሚ ሥራዎች እንቃኛለን።   

« የጎርጎረሳዊዉ 2016 ዓ,ም የሥነ-ጽሑፍ የኖቤል ሽልማት ለቦብ ዴላን ተጥቶአል። ቦብ ዴላን ለዚህ ሽልማት የበቃዉ በታላቅዋ አሜሪካ የአሜሪካ የሙዚቃ ባህል አዲስ ዓይነት አገላለጽ የዜማ ግጥም በመድረሱ ነዉ።» 

የ75 ዓመቱ ቦብ ዴይላን ሽልማቱ እንደደረሳቸዉ በይፋ ከተነገረ በኋላ መሰወራቸዉ ምናልባትም የሥነ-ጽሑፍ ሽልማቱ የሚያስገኘዉን የ 900 ሺህ ዶላር ሽልማት ማየት አልፈልግም ማለታቸዉ ሳይሆን አልቀረም ሲሉም መላምትን የሚሰጡ አልጠፉም።  

እዉቁ አሜሪካዊ፤  የሙዚቃ ግጥም ደራሲ በተለይ በጎርጎረሳዊዉ 1960 ዓ,ም በአሜሪካ ባህላዊ የሙዚቃ አዲስ የፈጠራ ሥራን በማሳየት ለየት ያለ ሙዚቃን በማቅረባቸዉና በርካታ ተከታዮች ማፍራታቸዉ ተዘግቦላቸዋል።  እንደ ደንቡ አንድ የኖቤል ተሸላሚ ከኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ሽልማቱን ከመቀበሉ በፊት ባሉት ስድስት ወራቶች ዉስጥ በተሸለመበት ዘርፍ ልዩ ሥራዎቹን ዳግም ማሳየት ፤ እንዲሁም ሞያዊ  እና ትምህርታዊ ትንተናን  ማቅረብ ይኖርበታል።  የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ተሸላሚም ከሽልማቱ በፊት ሥነ-ጽሑፍን በተመለከተ ትምህርታዊ ገለጻ እንዲሰጥ ይጠበቃል። የዘንድሮዉ የሥነ ጽሑፍ ተሸላሚ አሜሪካዊ ቦብ ዳይላን ግን ለሽልማት ባበቃቸዉ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ትምህርታዊ ገለጻን መስጠት ባይፈልጉ እንኳ ቢያንስ አንድ የሙዚቃ ድግሥን ማሳየት እንደሚጠበቅባቸዉ ገና የኖቤል ሽልማት አካዳሚዉ ከመጀመርያዉ እንደ አማራጭ ያስቀመጠዉ።

የስዊድን የኖቤል ሽልማት ኮሜቴ ቃል አቀባይ ጆና ፔተርሰን ለሮይተርስ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ከኖቤል ተሸላሚዉ የምንጠብቀዉ ትምህርታዊ መግለጫን ነዉ።  አዎ፤  ከቦብ ዴይላን ደግሞ ቢያንስ የሙዚቃ ድግስን እንዲያሳይ ነዉ ስምምነት ላይ የደረስነዉ ሲሉ ተናግረዋል።

በጎርጎረሳዊዉ 2007 ዓ,ም በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ የኖቤል ሽልማትን የተቀበሉት ብሪታንያዊትዋ ደራሲ ዶሪስ ሌሲንግ ፤ ሽልማቱን ማግኘታቸዉ እንደተነገረ በጠና ታመዉ መጓዝ እንደማይችሉ ተረጋግጦ ፤ ከሽልማቱ በፊት የሚያቀርቡትን ጥናታዊ ጽሑፍ ለስዊድን አንድ አሳታሚ ድርጅት ልከዉ ስቶክሆልም በሽልማት ሥነ-ስርዓቱ ላይ ተነብቦላቸዋል።   

የስዊድን የኖቤል አካዳሚ አባል የሆኑትና የሽልማቱን ማሸነፍ ዜና ያበሰሩት ፔተር ዋስትበርግ የዳይላን ዝምታና መሰወር ፤ «ነዉር ፤ እብሪተኝነት» ሲሉ ነዉ የገለፁት። 

በስዊድ ነዋሪ የሆነዉ ዘጋቢያችን ቴድሮስ ምህረቱ እንደሚለዉ አካዳሚዉ ተሸላሚዉን መፈለጉን አሳዉቋል፤ ለመገናኛ ብዙሃንም ጉዳዩ ዋንኛ የመነጋገርያ ርዕስ ሆንዋ ይላል።

እንደ ስዊድኑ የኖቤል ሽልማት አካዳሚ የዘንድሮ ማለት የጎርጎረሳዊዉ 2016 ዓ,ም የሥነ-ጽሑፍ ተሸላሚዉ ቦብ ዴይላን አካዳሚዉ የሚሰጠዉን የሽልማት ገንዘብ ወሰዱ አልወሰዱ ፤ የዘንድሮዉ ተሸላሚ መሆናቸዉ በመዝገቡ መስፈሩ አይቀሬ ነዉ፤ እንዲያም ሆኖ የኖቤል ሽልማት አካዳሚዉ በዘንድሮዉ የሥነጽሑፍ ሽልማት ምርጫዉ ሙዚቀኛን መምረጡ ከመጀመርያዉ ነዉ ከፍተኛ ትችትን ያሰነዘረበት፤

ቦብ ዴይላን በጎርጎረሳዊዉ 1960 ዓ,ም "Blowin' in the Wind", "The Times They Are A-Changin'", "Subterranean Homesick Blues" እና "Like a Rolling Stone" የተሰኙት ፀረ አመጽ ሰባኪና ፀረ ጦርነት መንፈስ አዘል ሙዚቃዎች በዘመኑ ከዝያም በመለጠቅ የነበሩትን ወጣት ትዉልዶች ለሰላም ያበረታታና ተወዳጅነት ያተረፉ ሙዚቃዎች እንደሆን ይነገራል።  በስዊዲን ስቶክሆልም የሚገኘዉ ወኪላችን ቴድሮስ ምህረቱ እንደሚለዉ ሰሞኑን የቦብ ዴይላንን መጥፋት በትችት መልክ ሳይሆን በመደገፍ መልክ የሚወጡ ጽሑፎች እየታዩ ነዉ፤

ከ 100 ዓመት በላይ ያስቆጠረዉ የስዊድኑ የኖቤል ሽልማት አካዳሚ እስካሁን ስድስት የሥነ-ጽሑፍ ተሸላሚዎች ሽልማቱን አንቀበልም ማለታቸዉ በታሪክ ተመዝግቦአል። ከእነዚህ ተሸላሚዎች መካከል በጎርጎረሳዊዉ 1964 ዓ,ም ተሸላሚ የሆኑት ፈረንሳዊዉ የፍልስፍና ሥነ-ጽሑፍ ደራሲ ዦን ፖል ሳትሪ ይገኙበታል። ፈረንሳዊዉ ሳተሬ ሽልማቱን አልቀበልም ካሉ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የገንዘብ ችግር ደርሶባቸዉ በጠበቃ በኩል ለኖቤል ሽልማት አካዳሚዉ ገንዘቡ እንዲሰጣቸዉ ጠይቀዉ መከልከላቸዉ ታዉቋል።   

የስዊድን ኖቤል ይፋዊ የሽልማጥ አሰጣጥ ሥነ-ስርዓት የፊታችን ታህሳስ መጀመርያ በስቶክሆልም ይካሄዳል። እስከዚያ የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ተሸላሚዉ እዉቁ አሜሪካዊ ሙዚቀኛ አለሁ እንደሚሉ ተስፋ በማድረግ ልሰናበት አዜብ ታደሰ ነኝ ጤና ይስጥልኝ፤ 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic