የንግድ ትርኢት በበርሊን | ኤኮኖሚ | DW | 21.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የንግድ ትርኢት በበርሊን

በጀርመኗ ዋና ከተማ በርሊን ላይ በአይነቱ ለየት ያለ የንግድ ትርኢት ተካሄደ። የወጪ እና ገቢ ንግድ ላይ ባተኮረው በዚህ ትርኢት በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትም ተሳትፈዋል። ትርኢቱን ያዘጋጀው የ አውሮጳ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና የአፍሪቃ የንግድ ትርኢት በምህጻሩ ኢኤምኢኤ በተሰኘው ተቋም አማካኝነት ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:20

የኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰብም ተሳትፏል

ዓላማው በአውሮጳ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪቃ መካከል የንግድ እና መዋዕለ ንዋይ ፍሰቱን ማጠናከር ነው። ማክሰኞ ዕለት በተከፈተው የአውሮጳ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪቃ ከኢትዮጵያ 15 የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት በንግድ ትርኢቱ ለመሳተፍ መጥተዋል። በንግድ ትርኢቱ ኢትዮጵያ በቡና፣ በቆዳ ፤ በእርሻ ፣ በጤና  እንዲሁም በገቢ እና ወጪ ዘርፍ መሳተፏን የንግድ ምክር ቤት የቦርድ አባል እንዲሁም የኦሮሚያ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዝደንትአቶ ታደ ገና ለDW ገልጸዋል። የልዑካኑ አስተባባሪ እና በእርሻው ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ታደሰ በርሊን ላይ ማክሰኞ ዕለት ስለተከፈተው የንግድ ትርኢት ምንነት እንዲህ ያስረዳሉ።

«ይሄ አውደርዕይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ ነው። ቦታውም ትልቁ የበርሊን አውደርዕይ የሚታይበት ቦታ አይደለም። ይኼ ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪቃ፣ አውሮጳ እና መካከለኛው ምሥራቅን ለማገናኘት የተጀመረ ነው።»

የስንዴ ዘርን በማራባት የእርሻ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ታደሰ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የንግድ አውደርዕይ ምንም እንኳን አነስተኛ መሆኑን ቢገልፁም አጋጣሚው ግን ኢትዮጵያውያኑ በሀገራቸው ያለውን ዕድል እና አጋጣሚ ለሌሎች ያስረዱበት መድረክ እንደበርም አመልክተዋል።

«የአድራሻ መለዋወጥ አለ፣ ጉባኤ ነበር እዚያ ላይ የእኛ ሀገር ጉዳይ የቀረበበት ሁኔታ አለ፤ ያ ማለት ምንድነው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ዕድል  በተመለከተ ቀርቧል። የተለመደው የቡና ማስተዋወቅ እና የቡና አፈላል ሥርዓት ፣ እንዲሁም ቦታ አግኝተን አንዳንድ ነገር ስለ ሀገራችን ለመጡት እንግዶች ለማስተዋወቅ ተሞክሯል።»

እንዲያም ሆኖ አዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ የቪዛ አሰጣጥ ሂደት በንግድ ትርኢቱ ለመሳተፍ ያሰቡትን  የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ለመድረኩ በሚገባ መልኩ ተዘጋጅተው እንዳይመጡ ችግር ፈጥሮባቸው እንደነበርም ነው አቶ ታደሰ የገለፁት።

በንግድ አውደርዕዩ የተሳተፉት የአውሮጳም ሆነ የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ኢትዮጵያ ውስጥ የመሥራት ፍላጎት እንደሚያሳዩ ሆኖም ግን የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው ነው የገለፁት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አባል እና የኦሮሚያ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዝደት አቶ ታደሰ ገና የገለጹት።

«አላቸው ፍላጎቱ ኢትዮጵያ እያደገች እየመጣች ያለች ሀገር መሆኗን ያውቃሉ፤ ግን ያው የተለመደውን ነገር ያነሳሉ ይኸውም ምንድነው የእኛ ችግር የውጭ ምንዛሪ ምደባው ላይ ፤ ትርፋቸውን ወደዚህ ለማምጣት ብንችል፤ በተለይ ያው ተጓዳኝም ሲያገኙ ከዚህ ኤክስፖርት የሚያደርጉት ነገር ላይ ሌሲ ለመክፈት የውጭ ምንዛሪ መጥፋት ምናምን ላይ ችግር ይሆና የሚል ነገር ያነሳሉ እንጂ ፍላጎቱ አለ።»

የንግድ ትርኢቱን ከአውሮጳ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና የአፍሪቃ የንግድ ትርኢት በምህጻሩ ኢኤምኢኤ በተሰኘው ተቋም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው በበርሊን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኢትዮጵያን የቡና ማፍላት ሥርዓት በዝግጅቱ ላይ ማቅረቡም ተገልጿል። በዛሬው ዕለትም ለሁለት ሰዓት የዘለቀ ስለወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ እና በመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ረገድ ስላሉ ዕድሎች ገለጻ እና ውይይት ተካሂዷል።

  ሸዋዬ ለገሠ 

አዜብ ታደሰ

 

Audios and videos on the topic