የንቦች ሳዉና | ጤና እና አካባቢ | DW | 20.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የንቦች ሳዉና

ከአየር ንብረት ለዉጡ ጋ ተገናኝቶ ይሁን ግልፅ ባይሆንም በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ሃገራት የክረምቱ የቅዝቃዜ ደረጃ መለዋወጥ ከጀመረባቸዉ ዓመታት ወዲህ ያልተጠበቁ ክስተቶች እየታዩ እንደሆነ ይነገራል። ከለዉጦቹ አንዱ ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ በመላዉ ዓለም የታየዉ ማር የሚሠሩት ንቦች ቁጥር እያነሰ የመሄዱ ጉዳይ ነዉ።

ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2006ዓ,ም አንስቶ የንቦች ቁጥር በመላዉ ዓለም መቀነሱ ይነገራል። የዩናይትድ ስቴትስ የግብርና ሚኒስቴር በቅርብ ያወጣዉ መረጃ እንደሚያመለክተዉ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመታት የክረምት ወራት 23 በመቶ የሚሆነዉ የሀገሪቱ የንብ ሃብት ጠፍቷል። ከግብርና ሰብል ምርቶች እጅግ ከፍተኛ ገቢ የምታገኘዉ አሜሪካ ከንብ ማንባቱ ዘርፍም ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ እንደምታስገባ ይነገራል። ይህን ታሳቢ ያደረገዉ የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ መመሪያ ታዲያ ቀሪዎቹን ንቦች ከጥፋት የሚያድን ግብረኃይል እንዲቋቋምና መፍትሄ እንዲያፈላልግ ያዛል። ግብረኃይሉ ሥራ ላይ ከሚያዉላቸዉ መፍትሄዎች አንዱ ታዲያ ንቦችን የሚያጠፉትን ጥገኛ ትሎች የሚያጠፋ ፀረ ተባይ መድሃኒት መጠቀም ነዉ። ምንም እንኳን እቅዱ የንቦችን ሕልዉና ለማስቀጠል ያለመ ቢሆንም አንዳንድ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ኬሚካል መጠቀሙ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላል የሚል ስጋታቸዉን ማሰማታቸዉ አልቀረም።

Prototyp Bienensauna

ከዚህ በፊት ሥራ ላይ ይዉል የነበረዉ የንቦች ሳዉና

የጀርመን የገበሬዎች ማኅበርም እንዲሁ ቀደም ሲል ለንቦች ሊደረግ የሚገባዉ ጥንቃቄ ቅድሚያ እንዲሰጠዉ ሲያሳብ ነበር። ካለፉት ዓመታት ጋ ሲነፃፀር ዘንድሮ በአብዛኛዉ የምዕራብ አዉሮጳ ሃገራት ክረምቱ እጅግም ጠነከረ የሚባል ዓይነት አይደለም እስካሁን። ባለፉት ዓመታት የቅዝቃዜዉ ሁኔታ ለትላትሎች መበራከት እድል በመስጠቱ 15 በመቶ የሚሆኑት ንቦች በጥገኛ ትሎች መፈጀታቸዉን የሚያስታዉሱት ንብ የሚያነቡት ሪቻርድ ሮሳ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ አደገኛ መሆኑን ነዉ የሚናገሩት።

«ንቦች በእነዚህ ጥገኛ ትሎች ሲወረሩ የሚመለከት ሰዉ ከመደናገጥ ዉጭ ሊያደርግ የሚችለዉ ነገር አይኖረዉም።»

መነሻዉ ከእስያ መሆኑ የተገለጸ ጥገኛ ትል በመላዉ ዓለም የንብን ዝርያ እያሰጋ ነዉ። አንድን ንብ ከያዘ ደሟን መጥጦ ከመግደል በቀር አትተርፍም። ለሪቻርድ ሮሳ እጅግ ዘግናኝ ሂደት ነዉ። አንዷ ንብ በሶስት ጥገኛ ትሎች ተወራ ሕይወቷ ሲያከትም አይተዋል። በትሉ የሚወረሩት ንቦች እንቅስቃሴ በጣም የሚያሰቅቅ ነዉ ከዚያም ብዙም ሲይቆዩ እንደሚደርቁ ሮሳ ይገልፃሉ። ይህን በሚገልፁበት ጊዜ ንብ አንቢዉ ሪቻርድ ሮሳ የመዘግነኑ ስሜት ከፊታቸዉ ይነበባል። በዚህ ዘርፍ እንደተሰማራ ባለሙያም ሥራቸዉ ስጋት አንዣቦበታል። እናም ይህ እንዲቀየር ይሻሉ። በምህንድስና የዶክትሬት ዲግሪ የያዙት ንብ አንቢ እዉቀታቸዉን ተጠቅመዉ መፍትሄ ለመሻት ወደስዊድን ተሻገሩ።

Richard Rossa Bienensauna Erfinder

ሪቻርድ ሮሳ

«ሶስት ጥገኛ ትሎች ለያዟቸዉ ንቦች የበኩሌን የሕክምና እርዳታ መስጠት ጀመርኩ። በጣም ዘግናኝ ነበር። ለዓመታት እንዲህ ላለዉ ችግር የሚሰጠዉ እርዳታ ሁልጊዜም አንድ አይነት እና አዎንታዊ ዉጤት የማያስገኝ ተደርጎ ነዉ የሚታወቀዉ። ይህን ለመለወጥ ፈለኩ። የንቦቹን ቀፎ በጣም ማሞቅ እንዳለብኝ አሰብኩ። ይህ ላለፉት ከ30 ዓመታት በላይ የሚታወቅ ስልት ነዉ። በተቃራኒዉ ግን እንዲህ ያለዉ ሁኔታ ለንቦች ተስማሚ አይደለም።»

እሳቸዉ የሚሉት ስልት ማለትም የንብን ቀፎ በከፍተኛ ሙቀት ማፈን በሩሲያና በምሥራቅ ጀርመን ዓመታትን ያስቆጠረ የንቦች ደህንነት መጠበቂያ ስልት ነዉ። የንቦች ሳዉና ይሉታል። እጅግ ከፍተኛ ሙቀት ያለዉ ንፋስ ወደቀፎዉ እንዲገባ ይደረጋል። ያኔ ንቦቹን ሊቀራመቱ የገቡት ትሎችም ሆኑ ጉንዳኖች ሙቀቱን መቋቋም ስለማይችሉ ይንጠባጠባሉ። ችግሩ ይህን ሞቃት አየር የሚተነፍሰዉ መሣሪያ ከአንድ ማቀዝቀዣ ማለትም ሪፍሪጅሬተር ስለሚበልጥ እንደተፈለገ ከሞታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የማይመች እና ለንብ አንቢዎችም አዳጋች መሆኑ ነዉ የሚነገረዉ። ሪቻርድ ሮሳ ግን የንቦቹን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል በእነሱ በኩል ስለሚደረገዉ ጥረት እንዲህ ይላሉ።

«ዓላማዉ በተቻለ መጠን በርካታ ጥገኛ ትሎቹን በአንድ ጊዜ መፍጀትና አብዛኞቹን ንቦች ከእነሱ መገላገል ነዉ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ንብ አንቢዎች ይህን ለመጠቀም እንዳይቸገሩ መሣሪያዉን በርካሽ በማቅረብ እናበረታታለን።»

በአሁኑ ጊዜ ብዙዎቹ ንብ አንቢዎች እነዚህን ትሎችና የጉንዳን ዘሮች ከንቦች ቀፎ ለማስገድ ሲሉ የሚረጩ ፀረ ተባይ መድሃኒቶችን ይጠቀማሉ። ችግሩ ግን መድሃኒቱ ጥገኞቹን የንብ ፀሮች ብቻሳ ይሆን ንቦቹንም የሚጎዱ መሆኑ ነዉ። ሪቻርድ ሮሳ እንዲህ ያለዉን መድሃኒት መጠቀም ነዉር ነዉ ባይ ናቸዉ።

«አሲዱ ጥገኛ ትሎቹንም ሆነ ጉንዳኖቹን ጎድቶ ከንቦቹ ላይ እንዲወርዱ ያደርጋል። ግን ደግሞ አሲዱ ጥገኞቹን ብቻ ሳይሆን ንቦቹንም ጭምር ነዉ የሚነካዉ። ይህ መድሃኒት ከተረጨ በኋላ ንቦቹን ብንመለከት አካላቸዉ ተበሳስቶ ነዉ የሚገኘዉ። አይናቸዉ እግራቸዉ ይጎዳል። የተጎዳ ንብ ደግሞ ይበልጥ በሌሎች ተሐዋሲያን ለመጠቃት የተመቻቸ ነዉ። ጉዳታቸዉ ከፍተኛ ስለሚሆንም በቀጣዩ ዓመት ማር የማዘጋጀቱ አቅም አይኖራቸዉም። ይህ እንደዉም እንስሳት ላይ የሚፈጸም ጭካኔ ነዉ።»

ይህን ችግር ከተመለከቱ በኋላም ለዚች ትንሽ ሆኖም በታታሪነቷ ለምትታወቀዉ ንብ ይበጃል ያሉትን መሣሪያ ፈለሰፉ። እሳቸዉ እንደሚሉት ለአጠቃቀምና ለማንቀሳቀስ እጅግ አመቺ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪም ሙቀቱ ወደቀፎዉ ሲለቀቅ ጥገኞቹን ትሎችና ጉንዳኖች እንጂ ንቧን አይጎዳም። የንብ አፍቃሪዉ ሌሎች መሰል ንብ አንቢዎች ለመግዛት ችግር እንዳይገጥማቸዉ መሳሪያዉ ቢያንስ ለ30 ዓመታት የሚያገለግል ሲሆን ዋጋዉም መጠነኛ እንደሆን መጣራቸዉን ነዉ የሚገልፁት። እሳቸዉ ያዘጋጁት የንቦች ሳዉና ማለትም በንብ ቀፎ ዉስጥ ከፍተኛ ሙቀት መልቀቅ የሚችለዉ መሣሪያ ከቀፎዉ ስር ተቀምጦ በቱቦ በባትሪ አለያም በአካባቢዉ በተገኘዉ የኤልክትሪክ ኃይል መስጫ ከ40 እስከ 42 ዲግሪ የሚደርስ ሙቀት ያመነጫል። የሚሽከረከር ማራገቢያ ሙቀቱን በቀፎዉ ዉስጥ ያናፍሳል። ንቦቹ ያለዉን የሚቀት መጠን መቋቋም ሲችሉ ጥገኞቹ ግን ከ38 ዲግሪ በላይ በሆነ በሆነ ሙቀት መቆየት አይችሉም። ያላቸዉ እድል ሙቀቱን ለመሸሽ ወደታች መዉረድ ነዉ እዚያ ደግሞ ያልጠበቁት ያገኛቸዋል። የኤልክትሪክ ንዝረት ያደግሞ ይፈፅማቸዋል ይላሉ ሮስ።

«እነዚያ ጠፍጣፋ ብረቶች የኤሌክርቲክ ማስተላለፊያዎች ናቸዉ። በዚህ አማካኝነት ነዉ ሙቀቱ የሚመጣዉ። ተሽከርካሪዎቹ ማራገቢያዎች ደግሞ ነፋስ እንዲፈጥሩ የተሠራ ነዉ። በዚያ ላይ ኤሌክትሮኒኮቹ አሉ። እነዚህ ሁሉ በአንድ ላይ ተጠርዘዉ እንደሳጥን የተዘጋጁ ናቸዉ። በዚያ ላይ ነዉ የንቡ ቀፎ የሚቀመጠዉ። መሣሪያዉን ያዘጋጀነዉ ማንኛዉም ሰዉ ያለምንም ችግር እንዲገለገልበት አድርገን ነዉ። መሳሪያዉ በቂዉን ሥራ ከሰራ በኋላ ራሱ ይጠፋል። ከዚያም አንዱን ቀፎ አፅድቶ ወደሌላቸዉ መሻገር ይችላል።»

Skizze einer Bienensauna

ሪቻርድ ሮሳ የፈለሰፉት የንቦች ሳዉና

የሪቻርድ ሮሳ አነሳስ ለራሳቸዉ ንቦች መፍትሄ ፍለጋ ነዉ። ሆኖም ሌሎች ንብ አንቢዎችም የንቦች ሳዉናን ጠቀሜታ ስላስተዋሉ ሃሳቡን ወደዱት። የመሣሪያዉ ፈልሳፊ አጀማመራቸዉ ለራሳቸዉ እንደመሆኑ ለገበያ የሚሆነዉን ምርት ለማቅረብ አቅሙ የላቸዉም። እናም የገንዘብ አቅም ያለዉና ፕሮጀክቱን የሚደግፍ አካል መፈለግ ግድ ሆነባቸዉ። ፍሎሪያን ዳይዚንግንም አገኙ። ቮልቮና ማን ለተሰኙት ተሽከርካሪዎች የሚሠሩት ዳይዚንግ የአካባቢ ጥበቃ ኤኮኖሚ ባለሙያ ናቸዉ። ከሪቻርድ ሮሳ ጋ በመተባበር አንድ ድርጅት መሠረቱ። ዳይዚንግ ገንዘብ እና ገበያ በማፈላለግ ይሠራሉ፤ ሮሳ ደግሞ እዉቀታቸዉን ስራ ላይ ያዉላሉ። ባካሄዱት የገንዘብ ማሰባሰብ ጥረትም የጀርመን የንብ ወዳጆች ማኅበርን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ወደ50 ሺ ዩሮ አገኙ። አንዱን መሣሪያ ለመስራት 1,500 ዩሮ ያስፈልጋል። ባትሪዉ 400 ዩሮ ያወጣል። በዚህም ዘርፍ የተሻለ ንግድ እየሠሩ እንደሆነ የሚገልፁት ሪቻርድ ሮሳ የማምረቻ ዋጋዉ በዝቶ መሣሪያዉ በገበያዉ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ከሚሆን 50 ዩሮ የሚሸጥ ሆኖ 100 ንብ አንቢዎች ገዝተዉ መጠቀም ቢችሉ እንደሚመርጡ ገልጸዋል።

«ሰዎች ምን ያህል መሳሪያዉን እንደፈለጉት እያየሁ ነዉ። እናም የሰዉ ፍላጎት ይህን ያህል ከሆነ እጅግም ሊያሳስበኝ አይገባም ስል አሰብኩ። ሰዎች ከፈለጉት መሳሪያዉን ለሰዎች እሰጣለሁ። በርካሽ እንዲያገኙት ነዉ እኔ የምፈልገዉ፤ ያ ነዉ የእኔ ግብ። የሰዉ ፍላጎት እንዲህ ከፍ ይላል ብዬ በፍፁም አልገመትኩም።»

በመስክ ላይ በተደገፈ ሙከራ የታጀበዉ የንብ አንቢዎችን ሥራ ለመደገፍ የተነሳዉ የሪቻርድ ሮስ ጥረት መሳሪያዉን በተለያዩ ወቅቶች ለመፈተሽ አስቧል። የሮስ የንብ ቀፎዎች አሁን ንቦቹን ከሚያጠፉት ጥገኛ ትሎች ነጻ ሆኗል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic