1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የንብረት ታክስ እና የብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጆች ለፓርላማ ቀረቡ

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 2016

የከተሞችን የመንግሥት አገልግሎት በተሻለ ጥራት ለማቅረብ የሚያስችል ገቢ የሚያስገኝ ነው የተባለለት የፌዴራል የንብረት ታክስ አዋጅ ተገቢነት ላይ ጥያቄ ተነሳ። የፌዴራል የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ሁለት ምድቦች ያሉት ሲሆን በከተማ ቦታ መጠቀሚያ መብት ላይ የሚጣል እና በከተማ ቤት ባለቤትነት ላይ የሚጣል ታክስን/ግብርን/ የሚይዝ ነው።

https://p.dw.com/p/4hJlP
የኢትዮጵያ ፓርላማ
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምስል Solomon Muche/DW

የንብረት ታክስ እና የብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጆች ለፓርላማ ቀረቡ

የከተሞችን የመንግሥት አገልግሎት በተሻለ ጥራት ለማቅረብ የሚያስችል ገቢ የሚያስገኝ ነው የተባለለት የፌዴራል የንብረት ታክስ አዋጅ ተገቢነት ላይ ጥያቄ ተነሳ። ረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያዊያን ተቸግረውና ተበድረው በሚሠሩት ቤት ላይ ግብር ለመሰብሰብ ያለመ መኾኑ፤ ሕዝቡ ካለው አቅም ጋር የማይጣጣም ከመሆኑ በላይ ተጎጂ የሚያደርገው የቤት ተከራዮችን በመሆኑ በጥንቃቄ እንዲታይ ተጠይቋል። ዛሬ መደበኛ ጉባኤውን ያደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ ላይም ተወያይቶ ጉዳዩን ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።

የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች ? 

የፌዴራል የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ሁለት ምድቦች ያሉት ሲሆን በከተማ ቦታ መጠቀሚያ መብት ላይ የሚጣል እና በከተማ ቤት ባለቤትነት ላይ የሚጣል ታክስን/ግብርን/ የሚይዝ ነው። «ከተሞች የመንግሥት አገልግሎቶችን እና የመገልገያ ቦታዎችን በተሻለ ጥራት፣ በዘመናዊ ዘዴ እና ከፍ ባለ ጥራት ለማቅረብ፣ ለማደስ እና ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ወጪ ከንብረት ታክስ እንዲሰበሰቡ ለማድረግ» አዋጁ አስፈላጊ ነው ተብሏል።

አንድ የምክር ቤት አባል ግን ይህንን ረቂቅ አዋጅ ከሕዝቡ የመክፈል አቅም መነሻ በማድረግ ተቃውመውታል። «ኢትዮጵያዊያን በሚያስቆጭ ድህነት ውስጥ ላይ ነን» በማለትም ለክርክራቸው አስረጂ ጠቅሰዋል።

በዚህ በስፋት ታይቶት በቀጣዩ ዓመት ይፀድቃል የተባለው ረቂቅ አዋጅ ላይ አስተያየት የሰጡ ሌሎች የምክር ቤት አባላት የሕጉን አስፈላጊነት የደገፉ ሲሆን ሌላ የምክር ቤት አባል ደግሞ ኢትዮጵያውያን ቤት የሚሠሩበት እውነታ በዕድሜ ልክ ጥረት መሆኑን በማንሳት ረቂቁ በጥንቃቄ እንዲታይ ተማጽነዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ቤት ላይ የሚጣል የንብረት ታክስ የመክፈል አቅም እንደሌለውም ማሳያዎችን ጭምር በመጥቀስ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምስል DW/H. Melesse

የብሔራዊ ባንክ እና የባንክ አሰራር ረቂቅ አዋጆች

ምክር ቤቱ ሌላው የተመለከተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅን ነው። ረቂቁ «ክሪፕቶ ከረንሲ ወይም ሌላ ማንኛውም ዲጂታል ወይም የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ እንደ መገበያያ ገንዘብ አድርጎ በኢትዮጵያ ውስጥ መጠቀም የተከለከለ ተግባር ነው» ይላል። በሌላ በኩል «በፍራንኮ ቫሎታ ዕቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ለገንዘብ ሚኒስቴር ተሰጥቶ የነበረው ሥልጣን ተሽሮ ለብሔራዊ ባንክ ተሰጥቷል» ሲል ይደነግጋል።

ሌላው በዛሬው መደበኛ ጉባኤ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ተጽፎ ነገር ግን በምክትል ዐፈ ጉባኤዋ ለውይይት ያልቀረበው የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ ብዙ አዳዲስ እና መሠረታዊ የባንክ ሥራ ድንጋጌዎችን አካትቷል።

በረቂቁ አዋጁ ከተካተቱት ድንጋጌዎች መካከል «ማንኛውም የውጭ ባንክ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በባለቤትነት የሚይዘው የውጭ ባንክ ተቀጥላ እንዲያቋቁም ወይም የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ እንዲከፍት ወይም የባንክ አክሲዮኖችን እንዲይዝ ሊፈቀድለት ይችላል» በሚል ይገኛል። በተመሳሳይ «የውጭ ሀገር ዜጎች ወይም በውጭ ሀገር ዜጋ ባለቤትነት የተያዙ የኢትዮጵያ ድርጅቶች የባንክ አክሲዮን እንዲይዙ ሊፈቅድ ይችላል» በሚል ተደንግጓል። «የውጭ ሀገር ዜጎች በባንክ ውስጥ ልዩ እውቀት ወይም ሙያ በሚጠይቁ የሥራ መደቦች ላይ በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ከአምስት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ» ሊቀጠሩ እንደሚችሉ፣ «የውጭ ባንኮች ነባር የሀገር ውስጥ ባንኮችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በግዢ አማካኝነት እንዲይዙ» ፣ « የውጭ ዜጎች እና ሙሉ በሙሉ በውጭ ሀገር ዜጎች በባለቤትነት የተያዙ የኢትዮጵያ ድርጅቶች በአንድ ባንክ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉት በውጭ ሀገር ገንዘብ ብቻ» ስለመሆኑ፣ «ማንኛውም ሰው ከባንክ በተገኘ ብድር የአንድ ባንክ አክሲዮን መግዛት» እንደማይችልም ተደንግጓል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሁለት የመንግሥት እና 30 የግል ባንኮች መኖራቸው፣ ጠቅላላ ሀብታቸውም 3.3 ትሪሊዮን ብር መሆኑ እና ሰባት ባንኮች ደግሞ በምስረታ ሂደት ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ