የኔፈርቲቲ 100ኛ ዓመት | ባህል | DW | 10.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የኔፈርቲቲ 100ኛ ዓመት

«አንዳንድ ፀሐፍት ኔፈርቲቲ ራስዋ ንግሥት ሳባ ናት ይላሉ። የኢትዮጵያና የዓረብ መንግሥት ንግጉስ ሠለሞንን እንደጎበኘችዉና ንግሥት ሳባ እንደሆነች ዘግበዋል»።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 17:10

ኔፈርቲቲ


ሲሉ ስለ ዉቢትዋ አንገተ መለሎ ጥንታዊት የግብፅ ንግሥት ፤ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን ወደ ዓለም አቀፍ የቅርስ ማኅደር የሚገቡ የኢትዮጵያ የቅርስ አስተዳደር ሰነድ ዝግጅት ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉን ነበር ተናግረዋል።

BdT Berlins Nofretete

ኔፈርቲቲ እንደተገኘች የነበረዉ ዓዉደ ርዕይ

የዛሬ 100 ዓመት በጎርጎሪዮሳዊው ታሕሳስ ስድስት ፤ 1912 ዓ,ም በጀርመናዊዉ የግብፅ ታሪክ ጥናት ተመራማሪ ሉድቪግ ቦርቻርት፤ የሚመራዉ ወደ 150 የሚሆኑ በመሪት ዉስጥ የተቀበሩ ቅርሶች ታሪክ ጥናት ቡድን ነበር ፤ የዉቢትዋን የግብፅ ንግሥት የኔፈርቲቲን ቅርፅ ግብፅ ውስጥ ያገኘዉ። የእጅግ ታዋቂዋ የነፍረቲቲ ቅርፅ በጀርመኑ ተመራማሪ ወደ ጀርመን መጥቶ ዋና ከተማ በርሊን በሚገኝ ሙዚየም ከተቀመጠ ዘመናትን አስቆጥሮአል። የንግሥት ኔፈርቲቲ ምስል የትነትና ዉብ የሥነ-ጥበብ ሥራ ይታወቅ እንጂ፤ በርግጥ ሥለ ኔፈርቲቲ ማንነት አሁንም የተለያዩ መላምቶችና ጥናቶች ሲነዘሩ ነዉ የሚደመጠዉ። የእለቱ ዝግጅታችን የተገኘችበት 100ኛ ዓመት ስለሚታሰብለት የንግሥት ኔፈርቲቲ ቅርፅ ያስቃኘናል ።

የዛሬ 100 ዓመት የግብጻዊትዋ ንግሥት የኔፈርቲቲ ቅርፅ በጀርመናዊዉ የግብፅ ታሪክ ጥናት ተመራማሪ በሉድቪግ ቦርቻርት፤ የሚመራዉ በመሪት ዉስጥ የተቀበሩ ቅርሶች ታሪክ ጥናት ቡድን፤ አንድ ቅርጻ ቅርስና ስዕል ተሰብስቦ የተቀመጠበት ከምድር በታች የተቀበረ ጥንታዊ ቤት ዉስጥ ነበር ያገኘዉ። የአንገተ መሎሎዋ ኔፈርቲቲ ቅርፅ በባልዋ በፈርዖን «አክሄናተን» ዘመን የተሰራ መሆኑም ተመልክቷል። በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን ወደ ዓለም አቀፍ የቅርስ ማኅደር የሚገቡ የኢትዮጵያ የቅርስ አስተዳደር ሰነድ ዝግጅት ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ ስለ ግብፃዊትዋ ኔፈርቲቲ እንዲህ ገልፀዋል።

Ausstellung 100 Jahre Fund der Nofretete

በበርሊን የኔፈርቲቲ የመጀመርያዉ ዓዉደ ርዕይ


ንግሥት ኔፈርቲቲ ከዛሬ 3400 ዓመታት በፊት “አክሄናተን” ከተባለው ፈርዖን ባሏ ጋር ግብፅ ላይ ነግሣ እንደነበር የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። በኒህ ዓመታትም ፈርዖን አክሄናተን በአገሪቱ ሊያስፋፋው በሞከረው “አተን” የተሰኘው ሥርዓተ-አምልኮ ላይ የበኩላን ሚና ተጫውታ ነበር። በተለይም አከሄታተን (ወይ አማርና) በተባለው አዲስ ከተማቸው የዚህን አምላክና የቤተሰቧን ምስሎች በሰፊው አስቀርፃ ነበር። የኢትዮጵያ የቅርስ አስተዳደር ሰነድ ዝግጅት ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ፤ አንዳንድ የታሪክ ፀሐፍቶች ኔፈርቲቲን ከንግሥት ሳባ ጋር እንደሚያዛምድዋት ተናግረዋል።

በበርሊን ሙዚየም የሚገኘዉና የግብፅዋ ኔፈርቲቲ ቅርፅ ከቻይና እስከ አዉሮጳ የሚመጡ በርሊን የሚገኘዉን ይህን ሙዚየም እንዲጎበኙ ይጋብዛል፤ በዓለማችን ስለ ኔፈርቲቲ የሚናገረዉም ሆነ የሚያዉቀዉ ሰዉ ቁጥር እጅግ ጥቂት መሆኑ ይታወቃል። የኔፈርቲቲ ቅርፅ የተገኘችበትን መቶኛ ዓመት በማስመልከት ለየት ያለ ዓዉደ ርዕይ በርሊን ላይ ሲከፈት፤ በመሪት ዉስጥ የተቀበሩ ቅርሶች ታሪክ ጥናት አዋቂዎች በአዲስ ቴክኖሎጂ ምርምርና ኤክስሪ በሚያነሳ ልዮ ፎቶግራፍ ምናልባትም የኔፈርቲቲን መካነ መቃብር ሳያገኙ እንዳልቀሩ ይፋ አድርገዋል። ይኸዉም በልዩ ፎቶግራፍ ማንሻ ታየ የተባለዉ መካነ መቃብርዋ ከፈርዖን ቱታንቻሙንስ መካነ መቃብር ጀርባ ባለ ክፍል ዉስጥ እንደሆነ እንጊሊዛዊዉ የግብፅ ታሪክ ጥናት ተመራማሪ ኒኮላስ ሪቭስ ባለፈዉ ሰሞን ካይሮ የጥንታዊ ታሪክ ጉዳይ ቢሮ ቀርበዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰተዋል።

«ቀደም ሲል የነበረዉ ትዉልድ ያላገኘዉና በአዲስ ቴክኖሎጂ ያየነዉ አንድ ምልክት አግኝተናል። በዚህ የፎቶግራፍ ቴክኖሎጂ ማለትም ስካን በማድረግ ነዉ የደረስንበት። ይኸዉም በምዕራብና ሰሜን በኩል በሚገኘዉ ስዕልና ቅርፅ በሚታይበት ግድግዳ በስተጀርባ የሆነ ኮሪዶር መንገዶችን አግኝተናል። እና ከነዚህ ኮሮዶር መንገዶች መካከል ምናልባትም አንዱ ወደ ንግሥት ኔፈርቲቲ መቃብር ቦታ ሳያመራን አይቀርም።»

Neues Museum Berlin, Nofretete

የኔፈርቲቲ ዓዉደ ርዕይ በበርሊን


በርግጥ በልዩ ቴክኖሎጂ በፎቶ ወይም ስካን ማድረግያ ልዩ መሣርያ ታየ የተባለዉ መካነ መቃብር በአስቿኳይ እንዲመረመር ጥሪ ቀርቧል። የግብፅ የጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶች ሚኒስትር ማምዱህ ኧል- ዳማቱም ከጥንታዊዉ መካነመቃብር ግድግዳ ጀርባ ታየ የተባለዉን ነገር ተመራማሪዎች ቶሎ እንዲያዩትና እንዲመረምሩት ጓጉተዋል። ቢሆንም ግን የኔፈርቲቲ መካነ መቃብር ስለመሆኑ ይጠራጠራሉ።

«እንደኔ ይህ የኔፈርቲቲ መቃብር ቦታ ነዉ ብዬ አላምንም። ምናልባት ግን የንጉሳዊ ቤተሰብ የፈርኦን ቱት ፤ የፈርኦን ኪያ ንግሥቲቶች ይሆናሉ። ወይም ደግሞ የንጉስ ቱት እናት መቃብርም ሊሆን ይችላል። »
በተለይ በምዕራቡ ዓለም በተለያዩ ፊልሞች የስዕል ፊስቲቫሎች ላይ የኔፈርቲቲ የዉበት ምልክት ዘዉድዋንና ፤ መቃ አንገትዋ ምልክት እያደረጉ ያቀርቡታል። ቅርጽዋ በጥንታዊ ስልጣኔ ከተሰሩ ድንቅ ቅርጾች አንዱ መሆኑ ይታወቃል። የኢትዮጵያ የቅርስ አስተዳደር ሰነድ ዝግጅት ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ኃይለመለኮት ጀርመኖች ኔፈርቲቲን እንደ በርሊን መገለጫ አድርገዉም ያዩዋታል ሲሉ ተናግረዋል።
ንግሥት ኔፈርቲቲ ፈርዖን አክሄናተን ከሞተ በኋላም ለጥቂት ዓመታት ብቻዋን ግብፅን ታስተዳድር እንደነበር አንዳንድ መረጃዎች አሉ። ከእርሷም በኋላ የነገሠው እውቁ ህፃን ንጉሥ “ቱታንክሐመን” ነበር። ኔፈርቲቲ ስድስት ሴቶች ልጆችና አንድ ወንድ የእንጀራ ልጅ እንደነበራት በታሪክ ተፅፎአል ሲሉ አቶ ኃይለመለኮት ተናግረዋል።
“ኔፈርቲቲ” በጥንታዊ የግብጥ ቋንቋ “ቆንጂትዋ መጣች” የሚል ትርጓሜ አለው። እስከዛሬም ድረስ ዝናዋ የናኘው በውበቷ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። በአገራችንም ቢሆን ረዘም ያለ አንገት ያላት ጉብል “ውብ እንደ ኔፈርቲቲ” ትባላለች።


የኔፈርቲቲ መቃብርና ሬሳ እስከዛሬ ድረስ በመፈለግ ካሉት ቅርሶች ዋነኛው ነው። የግብፅ የጥንታዊ ቅርፅ ሚኒስቴር ተገኘ ስለተባለዉ ጥንታዊ መካነ መቃብር አጣርቶ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታዉቋል። «ቱትሞስ» የተባለዉ ቀራጭ ሀውልቱን እንደ ሞዴል ተጠቅሞ የንግሥቷን ምስል እስከዛሬው ትውልድ ሊያስተላልፍ ችሏል። በበርሊን የግብጽ ሙዚየም በርካታ የኔፈርቲቲ ቅርጾችና ሀውልቶች ይገኛሉ። የንግሥት ኔፈርቲቲ ከትከሻ በላይ ቅርፅ (Bust)፤ በዓለም በፎቶ ተሰራጭቶ ይገኛል። “ኔፈርቲቲ” የተሰኘው ስሟ በጥንት የግብዝ ቋንቋ “ቆንጂትዋ መጣች” የሚል ትርጓሜ እንዳለዉ የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። እስከዛሬም ድረስ ስሟ ሊቆይ የቻለው በዚህ ዝነኛ ውበቷ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል። በአገራችንም ቢሆን ረዘም ያለ አንገት ያላት ጉብል “ውብ እንደ ኔፈርቲቲ” ይባል የል? ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ


ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic