«የኔን እዉነት እጽፋለሁ» ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ  | ባህል | DW | 28.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

«የኔን እዉነት እጽፋለሁ» ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ 

«የማይፃፍ ገድል»በሚል ርዕስ በቅርቡ ለንባብ የበቃዉ የዶክተር በድሉ ዋቅጅራ መጽሀፍ ከ160 ሽህ በላይ ወጣት ኢትዮጵያዉያን በግዳጅ እንደተሳተፉበት በሚነገርለት የብሔራዊ ዉትድር ታሪክ ላይ ያተኩራል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:34

«ሸፋፍኖ መጻፍ አያስተምርም»


መጽሀፉ በእዉነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የዚያን ዘመን ወጣቶችን ታሪክ በማሳየት ረገድ አስተዋጽኦ እንዳለዉ የሥነ-ፅሁፍ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ደራሲና መምህር ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ከአሁን ቀደም 6 መጽሀፍትን ለአንባብያን አቅርቧል።  በቅርቡም «የማይፃፍ ገድል« በሚል ርዕስ ሰባተኛዉን መጽሀፍ እንካችሁ ብሏል። 

«ይህ የእኛ የአንድ መቶ ስልሳ ሶስት ሽህ ስድስት መቶ አስራ ስድስቱ ብሄራዊ ወታደሮች ስንክሳር ነዉ።ያልተጻፈዉ ታሪካችን ሳይሆን ያልተነገረዉ ወጋችን ።ይህ ሀገርና ወገን በዘመን እየቃኘ ካዜመልን የአዘቦት ዜማ አፈንግጠን ለወጣትነታችን የቀመርነዉ የሰንበት ዜማ ነዉ።»ይላል «በማይፃፍ ገድል »መጽሀፍ የኋላ ሽፋን የሰፈረዉ ፅሁፍ።«የማይፃፍ ገድል » በኢትዮጵያ ከ1970ወቹ  ጀምሮ በ5 ተከታታይ ዙሮች  በብሄራዊ ዉትድርና ስም  ተገደዉ ወደ ዉትድርና ስለገቡ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች  የሚተርክ መጽሀፍ ቢሆንም በመደበኛዉ የዉትድርና  ታሪክ እምብዛም አያተኩርም።ይልቁንም የያኔዎቹ ወጣቶች በዚህ የግዳጅ ተልዕኮ ላይ ያከናዉኗቸዉ ስለነበሩ ዘወትራዊ  ክንዋኔወች ይዘረዝራል።የመጽሀፉ ርዕስም ከነዚህ ታሪኮች ጋር የተሳሰረ መሆኑን   ደራሲዉ  ያስረዳል።

298 ገጾችና 11 ታሪኮችን በዉስጡ የያዘዉ ይህ መጽሀፍ ከአሁን ቀደም በግልም ይሁን በሰራዊት ደረጃ  የተጻፉ ታሪኮች ላይ የምናየዉን   የጦር ሜዳ ዉሎዎችና ጀብዱዎችን ከመተረክ ይልቅ  ከዚህ ጀርባ ላሉ ሁነቶች ሰፊ ጊዜ ሰጥቷል።ከትምህርት ቤት እስከ ስልጠና ጣቢያ፣ከስልጠና ጣቢያ እስከ መሸታ ቤት ጨዋታዎች ድረስ ሁሉም በግልጽ ተጽፏል።ደራሲዉ የታሪኩ አካል እንደመሆኑ መጠን እነዚህን ታሪኮች እኔ ካልፃፍኳቸዉ ማንም ሊጽፋቸዉ አይችልም ይላል።«በመትረየስ  ጠላት መለብለብህን እንጅ መትረየስህን ለግመል ጥለህ መሸሽህን የትኛዉ የታሪክ ጸሀፊ ሊጽፍልህ ይችላል?ናቅፋ ላይ የጠላት ምሽግ ስለገባ ወታደር እንጅ ስልጠና ለይ ራሱን ለሌሎች ሲል ስለጠፋ አሰልጣኝስ ማን ይነግርሃል» ሲል ያትታል።የመጽሀፉን መታሰቢያም ለዚሁ አሰልጣኝ መቶ አለቃ  አድርጎታል።።የብሄራዊ ዉትድርና ታሪክ የበርካታ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች ታሪክ ቢሆንም እስካሁን እነዚህን ወጣቶች በሚመለከት የተጻፈ ነገር አለመኖሩንም ያብራራል ።

ደራሲዉ ከመጸህፍቱ ባሻገር በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንና በግል ጋዜጦች ፖለቲካዊ ማህበራዊ ጉዳዩችን የሚተቹ ጽሁፎችን ያቀርባል።በዚህ የሚያዉቁት አንባቢያን ከዘመን ተጋሪ ጓደኞቹ ጋር ያሳለፈዉንና ከምልመላ እስከ ስንብት ያለዉን ያልተቀባባ የወጣትነት ህይወት በመፅሀፉ ማካተቱን በማህበራዊ ኑሮ ተቀባይነትን ሊያሳጣ ይችላል በሚልም ግር የተሰኙ እንዳሉ ይገልጻል።ይሁን እንጅ ሸፋፍኖ መጻፍ ያስተምራል የሚል እምነት የለዉም።

በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የስነ-ጽሁፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ተሻገር አስማረ ፤የደራሲዉን ስራወችም በቅርብ ያዉቋቿዋል።በቅርብ የወጣዉን «የማይጻፍ ገድል»መጽሀፍ በሚተቹ መድረኮችም ጽሁፍ አቅርበዋል።ደራሲዉ በዚህ መጽሀፍ በኖረበትን ዘመን እዉነትና የኖረበትን ህይወት የሚተርክ በመሆኑ ፤መጽሀፉ የትዝታ ዘዉግ ያለዉ ነዉ ይሉታል።  በዚህም የዚያን ዘመንና የዚያን ትዉልድ ታሪክ ምን ይመስል እንደነበር አሳይቷል ሲሉ ይገልጻሉ። 


እንደ ሥነ ጽሁፍ ባለሙያዉ ፤ደራሲዉ ራሱም ይሁን ሌሎች ያለፉበትን ህይወትና የነበራቸዉን አመለካከት የሚያሳዩ ታሪኮችና ሁነቶች መርጦ በመተረክ ረገድ ጥሩ ስልት ተጠቅሟል።የማይነኩ ጉዳዮችን ደፍሮ በማቅረብ ረገድም መጽሀፉ አስተማሪ ነዉ።የተጠቀመበት ቋንቋና ያነሳዉ ጭብጥም እንዲሁ።

በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ  በሥነ-ጽሁፍ ትምህርት ክፍል በማስተማር  ላይ የሚገኘዉ  ዶክተር በድሉ ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ የልቦለድ መጽሃፍትን ማንበብ ይወድ እንደነበረ ይናገራል። በተለይ «እንደ ወጣች ቀረች» የሚለዉን የልቦለድ መጽሀፍ በቃሉ እስከመያዝ ደርሶ እንደነበር ያስታዉሳል።ለዚህም  የታላቅ ወንድሙ የንባብ ፍቅር አስተዋፅኦ እንዳለዉ ያስባል።ያም ሆኖ ግን  12ኛ ክፍልን እስኪያጠናቅቅ  ድረስ መፃፍ እችላለሁ የሚል ስሜት አልነበረዉም። የመጀመሪያ ዲግሪዉን የያዘበት አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ግን «እፅፋለሁ» የሚል ስሜት እንዳጫረበት ይገልጻል።  እናም በ1996 ዓ/ም የሥነ-ጽሁፍ ና የቋንቋ ማስተማሪያ መጽሀፍ  ለህትመት አበቃ።ቀጥሎም ለትምህርት በሄደበት ኖሮዌ ሀገር «ፍካት ናፋቂወች» የሚል የግጥም ስብስብ በ1999 ዓ/ም ለንባብ አቀረበ። እዉነት ማለት የኔ ልጅ ፣የተስፋ ክትባት፣ያልተከፈለ ስለት ፣አገሬ ገመናሽና በቅርብ የወጣዉን የማይፃፍ ገድል ጨምሮ 7 መጻህፍትን ጽፏል።በእነዚህ የሥነ-ጽሁፍ ስራወቹ ታዲያ ለራሴ የሚታየኝን  እዉነት ከማሳየት ያለፈ ስብከትም ይሁን ፕሮፖጋንዳ ማቅረብ አልሻም ባይ ነዉ።
ጥበብ ለጥበብነቱ ብቻ መሰራት አለበት የሚለዉን ፍልስፍና በከፊል ቢቀበለዉም ፤መልዕክት ቢታከልበትም ችግር እንደሌለዉ ያምናል።ነገር ግን አንድ የጥበብ ስራ ለመልዕክቱ ተብሎ የጥበብ ደረጃዉ በፍጹም ለድርድር መቅረብ እንደሌለበት ያስረግጣል።

ለደስታም ይሁን ለሀዘን ስሜቶች ቅርብ ነኝ የሚለዉ ደራሲና መምህር ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ክረምት፣ሌሊትና ገጠራማ አካባቢ ለመጻፍና ሀሳቡን ለመሰብሰብ ይመርጣል።«የህይወት ግቤ መኖር ፤የመኖሬ ምክንያት ደግሞ መጻፍ ነዉ»። የሚል ፍልስፍና አለዉ።የምጽፈዉ ደግሞ የራሴን እዉነትና የማምንበትን ነዉ ይላል።
 

ፀሀይ ጫኔ 
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic