የኔቶ ዘመቻ ፍፃሜና ሊቢያ | ዓለም | DW | 31.10.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የኔቶ ዘመቻ ፍፃሜና ሊቢያ

ኔቶ ከኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ተቃዋሚዎች ጎን ሆኖ መዋጋቱ ግን በርግጥ የፈጠጠ ሐቅ ነዉ።የሰዉ ልጅ በእስከ ዛሬ እድገቱ ሊያመርት የሚችለዉን ልዩ የጦር መሳሪያ የታጠቀዉ ብቸኛዉ ዓለም አቀፍ የጦር ተጓዳኝ ድርጅት ካንድ ወገን አብሮ መዋጋቱ በርግጥ አጠያያቂ ነዉ።

default

ራስሙስን

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ የሊቢያ ዘመቻ ዛሬ አበቃ።ምክንያቱም፥-«ምክንያቱም ወታደራዊ ሥራችን አሁን ተከናዉኗል።»
አንድረስ ፎግሕ ራስሙስን።የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድረጅት ኔቶ ዋና ፀሐፊ።በርግጥም የሊቢያ የአርባ ሁለት ዘመን ገዢ ተገደሉ።ተቀበሩም።የኔቶ ተልዕኮም-ከኒዮርክ-ብራስልስ እንደተሰማዉ በታላቅ ድል ተጠናቀቀ።የኔቶ ተልዕኮ ምንነት፥ የድሉ አተረጓጎም እንዴትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።

ሊቢያን የደበደበዉ የኔቶ ጦር አዛዥ ጄኔራል ቻርልስ ቦሻርድ ሥለ ጦራቸዉ ዘመቻ ሲናገሩ ሁሌም መጋቢት አጋማሽ ላይ ያሉ ነዉ-የሚመስለዉ። «ተልዕኳችን የፀረ-ቃዛፊ ሐይላት የበላይነትን እንዲያገኙ መደገፍ አይደለም።ይልቅዬ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመዉን ጥቃት መከላከል-እንጂ።»

መጋቢት አጋማሽ።በትክክለኛዉ አቆጣጠር መጋቢት አስራ-ሰባት ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ፈረንሳይና ብሪታንያ በጋራ ያረቀቁትን፥ዩናይትድ ስቴትስ አስቀድማ የተስማማችበትን የዉሳኔ ሐሳብ አፀደቀ።ዉሳኔ ቁጥር 1973 ከሚያካትታቸዉ አንቀፆች «የሊቢያን ሠላማዊ ሕዝብና ሠላማዊ ሕዝብ የሚኖርበትን አካባቢ ከጥቃት ለመከላከል አስፈላጊ እርምጃዎችን ሁሉ መዉሰድ» የሚለዉ አንዱ ነዉ።

Libyen Ausmaß der Zerstörung in Bani Walid Flash-Galerie

በኒ ዋሊድ-ሊቢያ

«አስፈላጊዉ እርምጃ» የምትለዉ ሐረግ መልዕክት ለጄኔራል ቦሻርድ ዛሬም-እንደ ያኔዉ ሰላማዊ ሰዎችንና ሰላማዊ ተቋማትን መከላከል የሚለዉ ጥቅል ሐሳብ ማስረገጪያ መሆኗ በርግጥ ያነጋግር ይሆናል።የሚያዙት ጦር ዘመቻዉን ከተረከበበት-ዛሬ እስካበቃበት ጊዜ ድረስ ድፍን ሰባት ወር ያደረገዉ ግን አዛዡ ከሚሉት ብዙ መቃረኑን ለማወቅ ሁለቴ ማሰብን ሌሎች መጠየቅንም አይጠይቅም።

«አስፈላጊዉን እርምጃ-መዉሰድ» የምትለዉን ሐገር ከረቂቅ ዉሳኔዉ ያካተቱን መንግሥታት መሪዎች ያን ሐገረግ እንዳሻቸዉ መመንዘር የጀመሩት ግን የዉሳኔ ቁጥር 1973 አንቀፆች-ይዘት ቀርቶ ብዛታቸዉም በቅጡ ተንትኖ ሳያበቃ-ዉሳኔዉ ከኒዮርክ በተሰማ-ማግስት ነበር።

«ካሁን ጀምሮ የጦር አዉሮፕላኖቻችን ቤንጋዚ በሚገኙ አማፂያን ላይ ሊፈፀም የሚችለዉን ጥቃት ይከላከላሉ።ሌሎች የፈረንሳይ አዉሮፕላኖች ደግሞ ሰላማዊ ሰዎችን ለመከላከል ዝግጁ ናቸዉ።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኒካላ ሳርኮዚ።መጋቢት አስራ-ዘጠኝ።የፈረንሳይ፥ የብሪታንያና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የጀመረዉ ድንደባ ዓላማዉም የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ያሳለፈዉን ዉሳኔ በጣሙን «በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመዉን ጥቃት መካለከል ሊሆን ይችላል።የሳርኮዚ አዋጅ ከፓሪስ፥ የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን መግለጫ ከለንደን በተሰማበት ዕለት ማታ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦማባ ዘመቻዉ ቤንጋዚ አጠገብ መጀመሩን አረጋግጠዉም ነበር።«የዩናይትድ ስቴት ጦር ሐይል የሊቢያ ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ለመከላከል የሚደረገዉን አለም አቀፍ ጥረት በመደገፍ በሊቢያ ላይ የተወሰነ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወስድ አዝዣለሁ።እርምጃዉ አሁን ተጀምሯል።»

የመጀመሪያዎቹ ቦምቦች ከሰማይ፥የመጀመሪያዎቹ ሚሳዬሎች ከባሕር ሊቢያን ማንፈር የጀመሩት ግን ሳርኮዚ እንዳሉት ያኔ ቤንጋዚ የመሸጉ አማፂያንን ለመታደግ አለያም የቃዛፊን ወታደራዊ ጡንቻ ለመሰባበር እንጂ ሰላማዊዉን ሰዉ ለማዳን አልነበረም።ሰወስቱ የኔቶ ዋና አባል ሐገራት የጀመሩትን ድብደባ ኋላ የተረከበዉ የኔቶ ተልዕኮም የድርጅቱ-የዓለምም አድራጊ ፈጣሪዎች ካስጀመሩት ድብደባ፥ ከሚሹት አላማ የተለየ ነበር ማለት ያሳስታል።

የኔቶ ጦር ድብደባ ዋና ፀሐፊ አንረስ ራስሙስን በቀደም እንዳሉት በድርጅቱ ታሪክ በጣም ከተሳኩ ተልዕኮዎች አንዱ ነዉ።«ዘመቻ-የተባበሩት መከለካያ በኔቶ ታሪክ እጅግ የተዋጣለት ዘመቻ ነዉ።»

በርግጥም ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ከሥልጣን ተወገድዉ-ተገድለዋል።እና ራስሙስን እንዳሉት ለኔቶ ታላቅ ድል።ቶማስ ሲ ማዉንቴን በ1987 ወደ ሊቢያ የተጓዘዉ የዩናይትድ ስቴትስ የሰላም ልዑካን ቡድን አባል ነበር።ዛሬ ከአፍሪቃ በግሉ የሚዘግብ ጋዜጠኛ ነዉ።ጋዜጠኛ ማዉንቴን እንደሚገምተዉ እስከ ሰኔ ማብቂያ ድረስ ብቻ ኔቶ ሊቢያን በሰላሳ ሺሕ ቦምቦች ወይም ሚሳዬሎች ደብድቧል።

እያንዳዱ ቦምብ ሚሳዬል በአማካይ ሁለት ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል።ድምሩን ያስሉት።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ሐገራቸዉ የምትመራዉ ድርጅት አንድም የአሜሪካ ወታደር ፥ሳይሞት ሳይቆስል ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ማቁሰሉ ወይም ማስገደሉ፥ነዉ-ድርብ ድሉ።

«ሊቢያ ዉስጥ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መገደል የሊቢያን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከልና የአምባገነናዊ አገዛዝ ቀንበርን ሰብረዉ ነፃ እንዲወጡ ያደረገነዉ አስተዋፅ ተገቢ እንደነበር ያረጋግጣል።ጀግና ፓይለቶቻችንና ባልደረቦቻቸዉ ጭፍጨፋን ለመከላከል ረድተዋል፥የማይቆጠር ሕይወትን አድነዋል።አንድም የአሜሪካ ወታደር ሊቢያን ሳይረግጥ፥ የሊቢያ ሕዝቦች እንዲያሸንፉ እድል ሰጥተዋቸዋል።»

ኦባማ የዳነዉን ቁጥር እንደማያዉቁት ሁሉ የሞተዉንም ቁጥር በቅጡ የሚያዉቀዉ ወይም ማወቁን-ማስታወቅ የሚፈልገዉ፥ የሚፈቀድለት፥ የለም።አዲሶቹ የሊቢያ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ባለሥልጣናት ባለፈዉ መስከረም እንዳስታወቁት በሊቢያዉ ጦርነት ባጠቃላይ ሰላሳ-ሺሕ ሰዉ ተገድሏል።ከሟቾቹ ስምንሺዉ የቀድሞዉ የሊቢያ መንግሥት ጦር የገደላቸዉ ናቸዉ።ከሐምሳ ሺሕ በላይ ቆስሏል።

የኔቶን ድብደባና በኔቶ የሚደገፉት አማፂያንን ጥቃት ሽሽት ከሊቢያ ሊሰደድ ሲሞክር በየሥፍራዉ ያለቀዉን አፍሪቃዊ ከልብ የጣፋዉ ጥቂት እጅግ በጣም ጥቂት መሆኑ ነዉ-የአስደሳቹ ድል-አሳዛኝ ሰብአዊ ድቀት።ኔቶ እራሱ እንዳስታወቀዉ-በሃያ-ስድስት ሺሕ የበረረራ ምልልስ፥ እና በዘጠኝ ሺሕ ስድስት መቶ የኢላማ ምት ሊቢያን ደብድቧል።በእያንዳዱ ጥቃት አራት ቦምቦች ሊቢያን አጋይተዋል።እና ለኔቶ መሪዎች ታላቅ ድል።

በኮሎኝ ዩኒቨርስቲ የአለም አቀፍ ፖለቲካ አጥኚ ፕሮፌሰር ቶማስ ያግነር እንደሚሉት ለታላቁ ድል ያበቃዉ ዘመቻ በርግጥ አወዛጋቢ ነዉ።

«ከዓለም ሕግ አኳያ ሲታይ ኔቶ ያስፈፀመዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሳለፈዉን ዉሳኔ ነዉ።ማለት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ያሳለፈዉን ዉሳኔ ያስከበረ ድርጅት ነበር።የሊቢያዉ ሁኔታ ጦርነት እንደነበር የሚያዉቁ የማሕበራዊ ጉዳይ ሳይንቲስቶች ግን ይሕን አይቀበሉትም።ጦርነቱ የርስ በርስ ጦርነት ነበር።በዚሕ የርስ በርስ ጦርነት (ኔቶ) ግራ-ቀኝ ከተሰለፉ ተፋላሚዎች አንዱን ወገን እንደደገፈ ነዉ-የሚታየዉ።»

Superteaster NO FLASH Libyen Aufständische haben den Stützpunkt Bab al Asasija in Tripolis gestürmt

ሊቢያ


ኔቶ ያደረሰዉን ጥፋት ጄኔራል ቦሻርድ በይፋ አይቀበሉትም።የበላይ አለቆቃቸዉ፥ ሳርኮዚ፥ ካሜሩን፥ ኦባማም ሆኑ ተባባሪዎቻቸዉ ሊያምኑት አይፈልጉም።ሌላዉ ቀርቶ የሊቢያን የገዢነት ሥልጣን የያዙት ወገኖች እራሳቸዉ እንዲነሳባቸዉ አይፈልጉም።የፖለቲካ ፕሮፌሰሩ እንዳሉት ቃላት እየሰነጠቁ የሚናገሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲፕሎማቶችም የሚያድበሰብሱበትን ብልሐል ማፈላለጋቸዉ አይቀርም።

ኔቶ ከኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ተቃዋሚዎች ጎን ሆኖ መዋጋቱ ግን በርግጥ የፈጠጠ ሐቅ ነዉ።የሰዉ ልጅ በእስከ ዛሬ እድገቱ ሊያመርት የሚችለዉን ልዩ የጦር መሳሪያ የታጠቀዉ ብቸኛዉ ዓለም አቀፍ የጦር ተጓዳኝ ድርጅት ካንድ ወገን አብሮ መዋጋቱ በርግጥ አጠያያቂ ነዉ።ኔቶ በተካፈለበት ጦርነት ብዙ ሺ ሰላማዊ ሰዎች ማለቅ-መቁሰላቸዉ ደግሞ ካጠያያቂነቱም በላይ አሳዛኝ።

MI 5 የተሰኘዉ የብሪታንያ የስለላ ድርጅት የቀድሞ ባልደረባ አኒ ማሾን እንደሚሉት ኔቶ ሰብአዊ ያለዉ ዘመቻ ጥፋት በጠፋዉ የሰዉ ሕይወት ብቻ አይለካም።«ሊቢያዎች ሐገር ዉስጥም ዉጪም በነፃ የመማር፥ በነፃ የመታከም እድል ነበራቸዉ።ሲያገቡ መንግሥት መቋቋሚያ ይሰጣቸዉ ነበር።ብዙ የአፍሪቃ ሐገራት የሚቀኑባቸዉ ነበር።አሁን ግን» አከሉ የቀድማዋ የስለላ ባለሙያ «የኔቶ ድብደባ በርግጥ ሊቢያዎችን ወደ ድንጋይ ዘመን መልሷቸዋል።» የከንግዲሁ ጥያቄ-ሊቢያ መቼ እና እንዴት ሊቢያን ትመስላለች፥ የሊቢያዎችስ ትሆናለች ነዉ።ለዛሬዉ ግን ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ


Audios and videos on the topic