የኔቶ ወደ ኖርዲክ ሃገራት መስፋፋት | ዓለም | DW | 23.05.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የኔቶ ወደ ኖርዲክ ሃገራት መስፋፋት

የምዕራባውያን ሃገራትን ትኩረት የሳበው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መንስኤ ሳይሆን እንዳልቀረ የሚገመተው የኔቶ በምሥራቅ አውሮጳ አባላቱን የማብዛት እንቅስቃሴ የተገታ አይመስልም። ለሩሲያ የምትጎራበተው ፊንላንድና ስዊድንም የኔቶ አባል ለመሆን መነሳታቸው በኪየቭ ሞስኮ መካከል የተጫረውን የጦርነት እሳት አድማስ እንዳያሰፋው የሚሰጉ ጥቂት አይደሉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:20

የኔቶ ወደ ኖርዲክ ሃገራት መስፋፋት

የጦር መሳሪያ እሽቅድድምን ሲቃወሙ የኖሩ፤ ገለልተኖች፤ ሰላም ወዳዶች እና ጦርነት ጠሎች ናቸው የሚባሉት ስዊዲንና ፊንላንድ ዘድሮ የዓለም ትልቁ የጦር ድርጅት፤ የስሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ኔቶ አባል ለመሆን ባለፈው ሐሙስ ብራስልስ ለሚገኘው ዋናው ጽሕፈት ቤት ማመልከቻቸውን አስገብተዋል። ጥያቄያቸው በ30 ዎቹ አባል አገሮች በተለየ ሁኔታ እንደሚታይ እና በፍጥነትም ውሳኔ እንደሚሰጠው እየተገለጸ ነው። የእነዚህ ለረጅም ጊዜ የገለልተኝነት ፖሊሲን ሲያራምዱ የነበሩ አገሮች በዚህ ወቅት የጦር ድርጅት አባል ለመሆን ማሰብ መፈለጋቸው ብዙ እያነጋገረ ነው።

አሁን በዩክሬን እየተካሄደ ያለው አውዳሚ ጦርነት በዋናነት በሩሲያ ወረራ ምክኒያት የተከሰተ እንደሆነ ቢታመንም፤ የኔቶ የመስፋፋት አባዜ በተለይም እንደዩክሬን የመሳሰሉትንና የቀድሞ የሶቭየት ህብረት ግዝቶች የነበሩትን ማማለሉና ብዙዎቹንም አባሎቹ ማድረጉ ሩሲያን ለጦርነቱ አልጋበዛትም አይባልም። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማግስት አንድ ደርዘን በሆኑ የምዕራብ አገሮች የተቁቋመው ኔቶ፤ ያኔ ሶስት አላማዎችን ይዞ እንደትቋቋመ ይጠቀሳል። የሶሻሊስት ሶቭየትን ርእዮተአለምንና ምናልባትም ጥቃት መከላከል፤ በአውሮፓ ዳግም ብሄረተኝና ጦረኛ ድርጅቶች ወደ ሥልጣን  እንዳይመጡ መከላከል፤ የአውርፓን ፖለቲካዊ አንድነት ማፋጠን። በሶቭየቱ የሶሻሊስት ጎራ ወገንም የዋርሶ ፓክት የሚባል የጦር ድርጅት የነበር መሆኑ የሚታወስ፤ ሲሆን ሁለቱ በኒውክለር ጭምር የታጠቁ የጦር ድርጅቶች፤ እ እ እ  በ1989 የበርሊን ግንብ ፈርሶ የቀዝቃዛው ጦርነት እስካበቃ ድረስ፤ የምዕራቡ  የካፒታሊቱ ጎራና የሶሻሊስቱ  ቡድን የጦር ክንፎች በመሆን ዘልቀዋል። እ እ አ በ1991 ዓም የሶቭየት ህብረት  ስትበተን ግን ዋርሶ ፓክት (የዋርሶ ስምምነት) ፈረሰ። ኔቶም ከእንግዲህ አስፈላጊነቱ እንዳበቃና ሊፈርስም እንደሚችል ያያኔዎቹ የአሜርካ ባለሥልጣኖች ጭምር ይናገሩ እንደነበርና ሩሲያኖቹም ይህንኑ አምነው ይጠብቁ ነበር ይባላልም ። ሆኖም ግን ሩሲያ በተለይ በአስቸጋሪው የሽግግር ወቅት በነበረችበት ወቅትና ከዚያም በኋላ፤ ኔቶ ቀድሞ የሶቭየት ግዛቶች የነበሩትን የቦልቲክና የምሥራቅ አውሮፓ አገሮችን አካቶና  ተስፋፍቶ፤ ዛሬ አሜሪካን፣ ካናዳንና አውስትራሊያን ጨምሮ 30 አገሮችን ያቀፍ ግዙፍ የጦር ድርጅት ለመሆን በቅቷል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በገለልተኛነታቸው  የሚታወቁት ሁለቱ የኖርዲክ አገሮች ስዊድንና ፊንላንድ ድርጅቱን ለመቀየጥ ጥያቄ አቅርበዋል። 

US-Präsident Biden empfängt Magdalena Andersson und Sauli Niinisto

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የስዊድን እና ፊንላንድ መሪዎችን ተቀብለው ሲያስተናግዱ

ፊንላንድ ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል የሩሲያ አካል የነበረች ሲሆን፤  እ እ እ በ1917 የሩሲያ አብዮት ወቅት ነጽነቷን እንዳገኘች ነው የሚታወቀው፡፤ ፊኒሾች ከዚያም ወዲህ ከሶቭየቶች ጋር ተዋግተው የነበረ  ቢሆንም፤ እ እ እ በ1948 ዓም ግን የወዳጅነት ውል ተፈራርመውና ፊንላንድም ገለልተኛነቷን ጠብቃ በሰላምና በጥሩ ጉርብትና ዘልቀዋል። ስዊድን ግን የገለልተኛ መርኋ ከ200 ዓመት በላይ እንደዘልቀ ነው የሚነገረው። የጦር መሣሪያ እሽቅድድምን የምትቃወምና ዓለም አቀፍ ችግሮችም በውይይትና ድርድር እንዲፈቱ የምትፈልግ፤ ለዚህም አስተዋጾ በማድረግ የምታወቅ አገር ነበረች።  ሁለቱም ነባር አቋሞቻቸውን እንዲለውጡና ኔቶን እንዲቀላቀሉ ያደርጋቸው ገፊ ምክኒያት፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የወሰደችው ወታደራዊ እርምጃ ነው ባዮች ናቸው።  

የስዊድኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ማግዳሌን አንደርሰን ዋሺንግተን ላይ ከፕሬዝዳንት ባይደንና ከፊንላዱ ፕሬዝዳንት ሳውሊ ኒኒስቶ ጋር ሆነው በሰጡት መግለጫም «ስዊድን ከ200 ዓመት  የወታደራዊ ገለልተኝነት አቋም በኋላ ዛሬ ይህን አዲስ አቋም መርጣለች» ማለታቸው ለእሳቸውና መንግሥታቸው  ውሳኔ ዋናው ምክኒያት ይኸው የዩክሬን ጦርነት መሆኑን የሚገልጽ ነው። 

ይህን የሁለቱን አገሮች የአባልነት ጥያቄ ኔቶና አባል መንግሥታቱ በደስታ እንደተቀበሉትና በተለየ ሁኒታ በፍጥነት ውሳኔ እንደሚያገኝም እየገለጹ ነው።

የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ የን ሽቶልተንበርግ የሁለቱን አገሮች ማመልከቻ እንደተቀበሉ፤

 « የፊንላድንና ስዊድንን የአባልነት ጥያቄ በደስታ ነው የተቀበልኩት። የቅርብ አጋሮቻችን ሁናችሁ ብትቆዩም አባል ስትሆኑ ግን ለጋራ ደህንነታችን ዋስትና የሚሰጥ ይሆናል» በማለት ጥያቄያቸው በፍጥነት ምላሽ የሚያገኝ መሆኑን አረጋግጠዋል። ዋናዋ የኔቶ አባል የሆነችው አሜሪካ ፕሬዝዳንት ባይደንም ባለፈው ሐሙስ የሁለቱን አገሮች መሪዎች በኋይትሀውስ ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት፤ የስዊድንና ፊንላድ ወደ ድርጅቱ መግባት ይልቁንም ከፍተኛ ጥቅምና ጉልበት የሚያስገኝ መሆኑን ነው የገለጹት፤ «የእነዚህን ትልቅና የዳበረ ዴሞክርሲ ሥርዓትና ባህል ያላቸውንና አቅምና ብቃታቸው የተረጋገጠውን አገሮች የአባልነት ጥያቄ አሜሪካ ስታበርታታና በከፍተኛ ድረጃ  ስትደግፍ ነው የቆየችው» በማለት ዛሬ ጥያቄው መምጣቱ ያስደስታቸው መሆኑን ገልጸው፤ ኔቶ ከመቼውም ግዜ ይበልጥ በአሁኑ ወቅት አስፈልጊ ሁኗል ብለዋል። 

NATO-Beitritt Finnland und Schweden I Jens Stoltenberg

የኔቶ ዋና ጸሐፊ የፊንላንድ እና ስዊድንን የአባልነት ማመልከቻ ሲያሳዩ

  

የኔቶ አባል ለመሆን ቢያንስ የገበያ መር የካፒታሊስት ስርዓት  አራማጅ መሆን፣ የዘመናዊና ብቁ ሠራዊት ባለቤት መሆንና ለመከላከያ በጀት ከጠቅላላ ገቢ 2 ከመቶ የመደበ ወይም ሊመድብ የተዘጋጀ መሆን ይጠበቅበታል። የአባልነት ጥያቄው በሁሉም አባል አገሮች ተቀባይነት ማግኘትና በየፓርላማዎቻቸውም መጽደቅ የሚኖርበት ሲሆን፤ አጠቃላይ ሂደቱም ቢያንስ አንድ አመት እንደሚወስድ ነው የእሳክሁኑ አሰራር የሚያሳየው። የስዊድንና ፊንላንድ ጥያቄ ግን አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ ነው የሁሉም ፍላጎት።

በርግጥ ሁለቱም አገሮች የዳበረ የካፒታሊስት ሥርዓት ያላቸውና ሠራዊታቸውም የዘመነና ከኔቶ ሠራዊት ጋርም በአጋርነት ሲሳተፍና ሲለማመድ የነበረ ነው። ዋናው ሂደቱ መፍጠን ያለበት ግን ጥያቄውን በማቅረባቸው ደስተኛ ያልሆነችው ሩሲያ ጥቃት ብትሰነዝርባቸው ድርጅቱ በደንቡ አንቀጽ አምስት  መሰረት ጣልቃ ለመግባትና ለመከላከል የሚያስችል ሕጋዊነት እንዲኖረው ለማስቻል እንደሆነ ይታመናል።  ሆኖም ግን ቱርክ ተቃውሞ በማንሳቷ ሂደቱ በታቀደው መሰረት የሚጓዝ አይመስልም።አንካራ፤ ስዊድንና  ፊንላድ እሷ ሽብርተኛ ላለችው  የኩርድ ሠራተኖች ፓርቲ ፒኬኬ ድጋፍ ያደርጋሉ፤ ለአባላቱም መጠለያ ይሰጣሉ በማለት ለጥያቄው ይሁንታ እንደማትሰጥ አስታውቃለች።

የሁለቱ አገሮች በዚህ ወቅት ወደ ኔቶ መግባት፤ በተለይ  ከሩሲያ አንጻር ላለው ፖለቲካዊ ትግልና ወታደራዊ ፍጥጫ ሚዛኑን የሚለውጥ ይሆናል በሚል እምነት አባል አገሮች በጉጉት የሚጠብቁት ሆኖ ሳለ፤ ቱርክ እንደዚህ አይነት አቋም ማራመዷ የድርጅቱንና የአባል አገሮችን መሪዎች  አላስደነገጠም አይባልም። ስዊድንና ፊንላድ ግን ቱርክ ባነሳቻቸው ቅሬታዎች ዙሪያ ለመወያየት  ልዕካኖቻቸውን ወደ አንካራ መላካቸው ተስምቷል። የኔቶ ሹማምንት፤ አሜሪካና ሌሎች ሀያላን የኔቶ አባል አገሮች መሪዎችም ፕሬዝዳንት ኤርዶጋንን ለማግባባት በየበኩላቸው ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።   የድርጅቱ አንጋፋ አባል የሆነችው ቱርክ በድርጅቱ አባል መንግሥታት ላይ  በተደጋጋሚ ግዜ ቅሬታዎችን የምታሰማ ሲሆን፤ የአባልነት ድምጿንም በተለይ በእንደዚህ ዓይነት ወስኝ ግዜ ጥያቄዎቿን ለማሰማትና ለመደራደርም ትጠቀምበታለች ነው የሚባለው።

Türkei Rede Präsident Erdogan

የቱርክ ፕሬዝደንት ራሲፕ ጠይብ ኤርዶኻን

ፊንላንድና ስዊድን ካላቸው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ አንጻር  አባልነታቸው፤ ኔቶ በተለይ ከሩሲያ ጋር ለገባበት ወታደራዊ ፍጥጫ ከፍተኛ ጠቀሚታ እንዳለው ነው የሚታመነው። አገሮቹ ወደ ድርጅቱ ይዘውት ከመጡት የኢኮኖሚና ወታደራዊ እሴት በተጨማሪ፤ ኔቶን በስሜን አትላንቲክና ካስፒያን ባሕር ላይ ባለ ይዞታ ያደርገዋል። ይሁን እንጂ የኔቶ መስፋፋት ለአውሮፓ ሰላም ዋስትና ይሆናል ወይ የሚለው ጥያቄ ቁርጥ ያለ መልስ ያለው አይመስልም። በእርግጥ ኔቶ ከአውሮፓ ውጭ በሊቢያ፣ ኢራቅና አፍጋኒስታን ጥሩ ስም የለውም። በቆይታው አገሮቹን በብቸነት አውድሞና አፍርሶ እንደተመለሰ ነው የሚታወቀው። አሁን ግን በተለይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ እንዳደረገችው ሁሉ  በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ላይም ጥቃት እንዳትፈጽም ኔቶ አስታማማኝ ጋሻ ይሆናል ነው የኔቶን መስፋፍት የሚደግፉት ሀይሎች የሚሉት።  

በሩሲያ በኩል ግን  የፊንላድና ስዊድን ወደ ኔቶ ለመግባት መወሰን ብዙም እንዳላስደነቀ ነው የሚነገረው። በእርግጥ ፕሬዝዳንት ፑቲን እራሳቸው መንግሥታቱ በዚህ ውሳኔያቸው ትልቅ ስህተት ሰርተዋል ማለታቸው ተገልጿል። ስዊድንና ፊንላድ ቀድሞውንም ከምዕራባውያን ጋር የተጎዳኙ ስለነበር ሞስኮ ለግዜው የሁለቱን አገሮች  ወደ ኔቶ መግባት እንደስጋት ላትቆጥረው ትችላለች ነው አንዳንዶች የሚሉት። የቀድሞው የፊንላድ ጠቅላይ ሚኒስተር ሚስተ አሊክሳንደር  ስተብ እንደሚሉትም ሩሲያ የሁለቱ አገሮች ወደ ኔቶ መግባት ስጋት አልፈጠረባትም፤ «ሁለቱ  አገሮች ወደ ኔቶ ለመግባት በመወሰናቸው በሩሲያ የከረረ ምላሽ አልተሰማም ። እንደሚመስለኝ ምክኒያቱ ሩሲያ የፊንላድና ስዊድንን  ወደኔቶ መግባት ወታደራዊ ስጋት አድርጋ አላየችውም`።»  በማለት ኔቶ በስዊድናና ፊንላድ በኩል የሚያደርገውን መስፋፋት ሰላማዊና ጠብ  አጫሪነት የሌለበት ነው ብለውታል። 

Flagge der NATO sowie von Schweden und Finnland

የኔቶ፣ ፊንላንድ እና ስዊድን ሰንደቅ አላማዎች

ሌሎች ግን የሩሲያ አቋም አገሮቹ አባል በመሆናቸው ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን ኔቶ ወደፊት በእነዚህ አገሮች በሚያደርገው ወታደራዊ እንቅስቅሴና በአክባቢው በሚተክላቸው የጦር መሳሪያዎች የሚወሰን ነው የሚሆነው ባይ ናቸው ። ሁለቱ አገሮች የኔቶ አባሎች በመሆናቸው የአየር፤ ምድርና ባሕር ግዛቶቻቸውንም ለኔቶ ወታደራዊ እንቅስቅሲዎች ክፍት እንደሚይደርጉ ሁሉ፤ በኔቶ ላይ ለሚቃጣ ጥቃትም ኢልማ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ወደ ኔቶ መግባት በራሱ ከጦርነት ጥቃት መዳኛ መንገድ ነው ብሎ ማሰብ ዘመኑ አውዳሚ መሳሪያዎች የተፈልፈሉበት ዘመን ብቻ ሳይሆን  እነዚህ አሁን በባላንጣነት የቆሙት አሜሪካ መራሹ ኔቶና ሩሲያ ከኋላዋ ቻይናም ልትኖር ትችላለች፤  የነዚህ አውዳሚ የጦር መሳሪያዎች ብቸኛ ባለቤቶች መሆናቸው ማንም ለማንም የሰላም ዋስትና በእርግጠኘነት ሊሰጥ እንደማይችል የሚያሳይ ነው።  

ገበያው ንጉሤ

ሸዋዬ ለገሠ 

Audios and videos on the topic