የናፍታ መኪናዎች ዕጣ ፈንታ | ጤና እና አካባቢ | DW | 19.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የናፍታ መኪናዎች ዕጣ ፈንታ

የተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት የናፍታ መኪናዎች ወደዋና ከተሞቻቸዉ እንዳይገቡ በይፋ ለማወጅ የጊዜ ገደብ ቆርጠዋል። የበርካታ ተሽከርካሪዎች ፋብሪካዎች ባለቤት የሆነችዉ ጀርመንም ይህንኑ ርምጃ ለመውሰድ ዳርዳር እያለች ነዉ። ዋና አላማዉ የከባቢ አየር ብክለትን መቀነስ መሆኑ የሚነገርለት ይህ ዉሳኔ ግን በቀላሉ ተግባራዊ የሚሆን አይመስልም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:00
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:00 ደቂቃ

«በመኪናዎች የሚመጣዉን ብክለት ለመቀነስ በኤክትሪክ የሚዘወሩት አማራጭ ናቸዉ»

ሽቱትጋርት ከተማ፤ «አዉቶ ሽታት፤ ማለትም የአዉቶሞቢል ከተማ» በሚል ቅጽል ትታወቃለች። ይህን ስያሜ ያገኘችዉም ለሁለቱ የጀርመን ጠንካራ የአዉቶሞቢል ኢንዱስትሪዎች ማለትም የፖርሸ እና ዳይምለር መገኛ ቤት በመሆኗ ነዉ። የከተማዋ ፍርድ ቤት ባለፈዉ ነሐሴ ወር ናፍታ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ሽቱትጋርት ዉስጥ እንዳይንቀሳቀሱ ሊያግድ መዘጋጀቱን ማሳወቁ ተሽከርካሪዎቹ የሚመረቱባቸዉ ፋብሪካዎችን ተቀጣሪዎች እና ባለሃብቶች ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚዎችንም ስጋት ላይ መጣሉ ነዉ እየተነገረነዉ። ጉዳዩ አልፎ ተርፎም የፊታችን እሁድ በጀርመን የሚካሄደዉ አጠቃላይ ምርጫ ላይም የራሱን ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም። እንዲያም ሆኖ ፍርድ ቤቱ ሙሉ በሙሉ ናፍታ የሚጠቀሙ መኪናዎችን ያግድ ወይንስ ከፍተኛ ብክለት የሚያደርሱትን መርጦ እገዳዉን ያሳርፍባቸዉ የሚለዉ እያነጋገረ ነዉ። የእገዳዉ ሃሳብ የመጣዉ መንግሥታዊ ያልሆነዉ የጀርመን ለአካባቢ ተፈጥሮ ርዳታ የተባለዉ ድርጅት እና ሌሎች በተመሳሳይ ለአካባቢ ተፈጥሮ የሚቆረቆሩ ቡድኖች ከባቢ አየርን የሚበክሉ እንዲታገዱ ለፍርድ ቤት ባቀረቡት ክስ መሠረት ነዉ። የሽቱትጋርቱ ብቻ ሳይሆን የሙኒክ ከተማ ፍርድ ቤትም ተመሳሳይ የእገዳ ርምጃ እንዲወስድ ተጠይቋል። ይህን ግፊት የቀሰቀሰዉ ደግሞ የጀርመኑ የመኪና ፋብሪካ ፎልክስቫገን ምርቶቹ መጠነኛ ብክለት ብቻ እንደሚያስከትሉ አስመስሎ የሚያጭበረብር ፕሮግራም እንደገጠመላቸዉ መጋለጡ ነዉ።  ፎልክስቫገን ክስ በቀረበበት ወቅት 11 ሚሊየን መኪናዎቹ በፍተሻ ወቅት የሚያስከትሉትን የብክለት መጠን የሚያሳስት ሶፍቶዌር እንደተገጠመላቸዉ አምኗል። 
ታሪኩ ሲፈተሽ ላለፉት 20 ዓመታት የመኪና ፋብሪካዎች እና የአዉሮጳ መንግሥታት ናፍታ አነስተኛ ካርቦን ያለዉ ነዳጅ ነዉ በሚል ሲያወድሱት እና አዉቶሞቢሎቻቸዉንም ሲቸበችቡ ኖረዋል። አልፈዉ ተርፈዉም እንደ ጀርመን እና ብሪታንያ ያሉ ሃገራት በናፍታ የሚንቀሳቀሱ መኪናዎችን ለሚገዛ የግብር ቅነሳ እያደረጉም ሲያበረታቱ ከርመዋል። የኋላ ኋላ እንደታየዉ ግን ምንም እንኳን የናፍታ መኪናዎች የካርቦን ዳይኦክሳይድ ብክለታቸዉ የቀነሰ ቢሆንም ለጤና ከፍተኛ አደጋ መሆኑ የሚነገርለትን ናይትሮጅን ኦክሳይድ የሚያስከትሉ መሆናቸዉ ታወቀ። ባለሙያዎች የናፍታ መኪና ሞተር በከፍተኛ የሙቀት መጠን ነዳጁን ማቃጠሉ መልካም መሆኑን ቢገልፁም በዚህ ሰበብ የሚፈጠረዉ ከፍተኛ ናይትሮጂን ኦክሳይድ አደገኛ መሆኑን ይናገራሉ።  


በአሁኑ ወቅት በመላዉ አዉሮጳ  ጎዳናዎች ላይ 35 ሚሊየን ናፍጣ የሚጠቀሙ መኪናዎች ይሽከረከራሉ። መቀመጫዉን ብራስልስ ላይ ያደረገዉ መንግሥታዊ ያልሆነዉ የመጓጓዣ እና የአካባቢ ተፈጥሮ ተከታታይ ተቋም እንደሚለዉ ታዲያ በእነዚህ ተሽከርካሪዎች ምክንያት ከባቢ አየር ዉስጥ ከፍተኛ ብክለት የሚያስከትለዉ የናይትሮጅን ኦክሳይድ መጠን በሦስት እጅ ከፍ ይላል። የአዉሮጳ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቋም፤ ናይትሮጂን ዳይኦክሳይድ ባስከተለዉ የከባቢ አየር ብክለት ምክንያት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012ዓ,ም ብቻ በመላዉ አዉሮጳ 75 ሺህ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸዉን መዝግቧል። በቅርቡም የተደረገ ተመሳሳይ ጥናት ይኸዉ በናፍታ መቃጠል ሂደት የሚወጣ በካይ ጋዝ ከመጠን በላይ በከባቢ አየር ዉስጥ በመከማቸቱ እዚሁ አዉሮጳ ዉስጥ ከ11 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች መሞታቸዉን ያሳያል። የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋች የሆነዉ ግሪን ፒስ በመባል የሚታወቀዉ ድርጅት ባልደረባ ቤንጃሚን ሽቴፋን የከባቢ አየርን ንሕጽና የሚጎዱ ተሽከርካሪዎች መታገድ አለባቸዉ የሚል ፅኑ አቋም አላቸዉ።
«የእኛ ጥያቄ ግልፅ ነዉ፤የከባቢ አየርን የንፅህና ደረጃ የማይጠብቁ መኪናዎች ከተሞች ዉስጥ እንዲሽከረከሩ ሊፈቀድላቸዉ አይገባም ነዉ የምንለዉ። በዚያም ላይ ዝቅተኛ የብክለት ደረጃ እንዲኖር ማስተካከያ እንዲደረግ እንፈልጋለን፤ ይህን ደግሞ ከተሞች በቀላሉ ሊያደርጉት ይችላሉ።»
እዚህ ጀርመን ሀገር በናፍታ የሚሽከረከሩ መኪናዎች ተፈላጊዎች ሆነዉ ቆይተዋል። የነዳጁም ዋጋዉ ርካሽ ነዉ። መኪኖቹም ቢሆኑ የተሻሉ የሚባሉ ነበሩ። አሁን ግን ናፍታ የአካባቢ ተፈጥሮ ላይ ጉዳት የሚያስከትል ነዉ በሚል እየተተቸ ነዉ። ለዚህ ትችት ዋናዉ መንስኤ ደግሞ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰዉ በመቃጠሉ ሂደት የሚመጣዉ ናይትሮጅን ኦክሳይድ ነዉ። ይህ ለጤና ጠንቅ መሆኑ የሚነገርለት ጋዝ ሳንባን የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ አፈርንም አሲዳማ እንደሚያደርግ ነዉ የሚገለጸዉ። ናፍታ በመኪና ሞተር ዉስጥ ሲቃጠል የሚፈጠረዉ ናይትሮጂን ኦክሳይድ አስጊነቱ እየተወራ ሲመጣም የጀርመን የመኪና ፋብሪካ ፊልክስ ቫገን ብክለቱን የሚቆጣጠር ስልት በስዉር ገጠመለት። ይህ የብክለት መቆጣጠሪያ ደግሞ የሚሠራዉ መኪናዉ በመደበኛ እንቅስቃሴ ላይ ሳለ ሳይሆን የብክለት ፍተሻ ሲደረግለት ብቻ መሆኑን የአሜሪካን ባለሙያዎች ደርሰዉበት የመኪናዉ አምራች ፋብሪካ ከፍተኛ ቅሌት እና የገንዘብ ቅጣት ከያለበት ወርዶበታል።

ይህ ከታወቀ በኋላ ታዲያ የናፍታ ብክለት ማስከተል ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት በመሆኑ በዚህ ነዳጅ የሚሽከረከሩ መኪናዎች ዕጣ ፈንታ በጣት የሚቆጠር ነዉ የሚል ግምትን በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል። 
ያም ሆኖ ግን  ምንም እንኳን ናፍታ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች የሚያስከትሉት የከባቢ አየር ብክለት አነጋጋሪ ቢሆን አሁንም የአዉሮጳ ሃገራት ከተሞች የየራሳቸዉን ርምጃ እንዲወስዱ የተተዉ መስሏል። ለምሳሌ የፓሪስ፣ የማድሪድ እና የአቴንስ ከተማ ከንቲባዎች በካይ ተሽከርካሪዎች ቀስ በቀስ እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2025ዓ,ም ድረስ በየከተማዎቻቸዉ ጎዳናዎች ላይ እንዳይንቀሳቀሱ እናደርጋለን የሚል ዉሳኔያቸዉን ያሰሙት ከአንድ ዓመት በፊት ነበር። የብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን እና ግሪክ ይህን መሰሉ የተጠናከረ አቋም በቅርቡ ከተሰማ በኋላም ቮልቮ የተባለዉ የመኪና አምራች ኩባንያ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አዉቶሞቢሎችን ወደማምረት ፊቱን ሊያዞር መሆኑን ጠቁሟል። ባለፈዉ ሳምንት በጀርመኗ የንግድ ከተማ ፍራንክፈት ላይ የታየዉ የተሽከርካሪዎች አዉደርዕይ ላይም የመኪና አምራች ኩባንያዎቹ የየበኩላቸዉን የፈጠራ አቅም ተጠቅመዉ የብክለት መጠናቸዉ የቀነሰ አዉቶሞቢሎችን የማቅረብ ዕቅዶቻቸዉን ሲናገሩ ተደምጧል። ከእነሱ አንዱ ደግሞ የጀርመኑ ዳይምለር እህት ፋብሪካ የሜርሴዲስ ቤንዝ ኃላፊ ዲተር ዜትሸ ነበሩ።
«ሜርሴዲስ ቤንዝ ከብክለት ነፃ ወደሆነ የመኪና ማሽከርከር ስለመሸጋገር ማሰብ ከጀመረ ቆይቷል።  ለእኔ በጣም አስፈላጊ የሆነዉ የጀርመን የአዉቶሞቢል ኢንዱስትሪ የፈጠራ ኃይል እና የወደፊት ስኬት ነዉ። ባለፉት ወራት በነበረዉ ክርክር የነበረዉ ተአማኒነት መታጣቱ ፍፁም አያጠራጥርም፤ እመኑኝ ይህ አሳዝኖኛል።  እናም የመፍትሄ  አካል መሆናችንን የማሳየቱ ኃላፊነት የእኛ ነዉ።» 
በዚህ አጋጣሚም ኩባንያቸዉ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2022ዓ,ም ጀምሮ ለገበያ የሚያቀርባቸዉ አዉቶሞቢሎች  በኤሌክትሪክ የሚሽከረከሩ እንደሚሆኑም ሜርሰዲስ ቤንዝ ጠቁሟል። በናፍታ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደትላልቅ ከተሞች እንዳይገቡ የተጀመረዉ የማገድ እንቅስቃሴ ግን በቀላሉ ሁሉም የሚስማሙበት እና የሚቀበሉት አይመስልም። ለምሳሌ እዚሁ ጀርመን የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች መጠኑ ያለፈ ናይትሮጂን ዳይኦክሳይድ ብክለትን ወደከባቢ አየር የሚለቁ ናፍታ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎችን ባፋጣኝ ማገድ ይገባል በሚል ግፊት እያደረጉ ነዉ።

የጀርመን የመጓጓዣ ዘርፍ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዶብሪንት ግን «የናፍታ መኪናዎችን በጥቅሉ ማገድ የተሳሳተ የፖለቲካ አካሄድ ነዉ፤» በማለት ይተቻሉ። አብዛኞቹ የአዉሮጳ ከተሞች የናፍታ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ላይ ጠንካራ ርምጃ ለመዉሰድ በተዘጋጁበት በዚህ ሰዓት ታዲያ ጀርመን በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠሩትን የመኪና ፋብሪካዎች ለማትረፍ ሙግት ዉስጥ የገባች አስመስሏታል። የአዉሮጳ ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር ኤልዛቤት ቢንኮቭስኪ ለየሃገራቱ የመጓጓዣ ሚኒስትሮች በጻፉት ደብዳቤ የፖሊሲ አዉጭዎች አቋም ስጋት እንዳሳደረባቸዉ ጠቁመዋል።  
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች ደግሞ ከፖሊሲ አውጪዎቹም ሆነ ብክለትን እንዲቀነስ ከሚሟገቱት የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች በኩል ሆነዉ ሁኔታዉን ሲመዝኑት፤ ብክለታቸዉ ከፍተኛ የሆነ ናፍታ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ይታገዱ ቢባል የቅርብ ጊዜ ሞዴሎች ብቻ ሊተርፉ እንደሚችሉ ይናገራሉ። የብሪታንያ የመጓጓዣ እና ማኅበረሰብ ማዕከል ዳይሬክተር ግርሃም ፓንክረስት እንደሚሉትም በዚህ ዉሳኔ ሃገራት ቢፀኑ ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ የተፈበረኩ አዉቶሞቢሎች ብቻ ናቸዉ በአዉሮጳ ጎዳናዎች ላይ የመሽከርከር ፈቃድ የሚያገኙት። እናም አሁን የሚታየዉ ነገር ሁለት ፈርጅ ያለዉ ይመስላል፤ ፖለቲከኞች ብክለትን ለመቀነስ የሚወሰደዉ ርምጃ ተጠቃሚዎችንም ሆነ መኪና የሚያመርተዉን ኢንዱስትሪ ሳይጎዳ ተግባራዊ እንዲሆን ይሻሉ። የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ደግሞ የብክለት መጠኑን የሚያልፉ የናፍታ መኪናዎች ሁሉ ከጨዋታ ዉጪ እንዲሆኑ ግፊት ያደርጋሉ። ሁለቱን የሚያቀራርበዉ አንድነገር ይመስላል፤ ኤሌክትሪክ ተጠቅመዉ የሚንቀሳቀሱ መኪናዎችን ማምረት። ኢንዱስትሪዉ ዝግጁ ነኝ እያለ ነዉ። አዉሮጳ በዚህ መፍትሄ ከናይትሮጅን ዳይኦክሳይድ ብክለት መላቀቅ የሚሳካላት ከሆነ የኃይል አቅርቦት እጥረት የሚያሰቃያቸዉ የአፍሪቃ እና ሌሎች አካባቢ ሃገራት ዕጣ ምን ይሆን የሚለዉ ለጊዜ ጥያቄ ሆኖ ይቆያል። 
ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic