የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ዳግም ምርጫ ዘመቻ | አፍሪቃ | DW | 13.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ዳግም ምርጫ ዘመቻ

የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን በጎርጎሪዮሳዊው አዲስ ዓመት ለዳግም ዘመነ-ሥልጣን በመመረጥ እንደሚወዳደሩ መግለጣቸው በናይጄሪያውያን ዘንድ ከወዲሁ ቁጣ እና ደስታን የቀላቀለ ስሜት ፈጥሯል።

ፕሬዚዳንቱ ማክሰኞ ኅዳር 2 ቀን፣ 2007 ዓም ባሰሙት ንግግር በተደጋጋሚ ጥቃት እያደረሰ የሚገኘውን ቦኮሐራም የተሰኘውን ሽብርተኛ ታጣቂ ኃይል እንደሚያሸንፉ ቃል ገብተዋል። ቦኮሐራም በናይጄሪያ የተለያዩ ከተሞች ለአምስት ዓመታት ግድም ተከታታይ ጥቃቶችን በመሰንዘር ላይ ይገኛል። ፕሬዚዳንቱ ከሦስት ወራት ግድም በኋላ በሚካሄደው የናይጄሪያ አጠቃላይ ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩም ገልጠዋል።
«በሀገሪቱ የሚገባህን እና የሚመጥንህን ማንኛውንም ወንበር መያዝ ትችላለህ። ወንድሞቼ እና እህቶቼ፤ ይኽ ፅኑዕ ቃል-ኪዳኔ ነው። እናም ተግባራዊ የሚሆነው ከእናንተ ጋር ነው። አመሠግናለሁ። ፈጣሪ የናይጄሪያ ፌዴራል ሪፐብሊክን ይባርክ።»
ይኽ ፕሬዚዳንቱ ዳግም ለመመረጥ ያሰሙት ንግግር ሙስሊሞች በሚበዙበት ሰሜናዊ ናይጄሪያ ማስተዋል የጎደለው እና ጊዜውን ያልጠበቀ የሚል ትችት አስከትሏል። አብላጫ ክርስቲያኖች በሚገኙበት ደቡባዊ ናይጄሪያ ግን በተቃራኒው የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ጊዜውን የጠበቀ የሚል ሙገሳን አግኝቷል። የዶይቸ ቬለ ሐውሳ ቋንቋ ክፍል ዘጋቢ አርዶ ሃዛድ በበኩሉ ፕሬዚዳንቱ ለዳግም ምርጫ ንግግር በማድረጋቸው ተጃጅለዋል ባይ ነው።
የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን

የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን

«በጥቅሉ የምናኪያሂደው የመንግሥት አስተዳደር የከሸፈ ነው። ከደኅንነቱ አንስቶ እስከ ጤና ጉዳይ፣ ብሎም ሌሎች ተቋማት እያንዳንዱ ነገር ከሽፏል። ስለእዚህ ጉድላክ ጆናታን ለእኔ ሲበዛ ተጃጅለዋል። እናም ራሳቸውን ለናይጄሪያውያን እንዴት አድርገው እንደሚያቀርቡ እንጃ።»
ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ቦኮሐራምን ድል እንደሚነሱ እና የሀገሪቱን ደኅንነት እንደሚያስጠብቁ ንግግር ባሰሙ ማግስት ትናንት የቦኮሐራም አባል ናት ተብላ የተጠረጠረች አንዲት አጥፍቶ ጠፊ የፌዴራል ኮሌጅ የአስተማሪዎች ማሠልጠኛ ቤተ-መፀሐፍት ውስጥ በመግባት ራሷን እና ሌሎች ተማሪዎችን በፈንጂ ማጥፋቷ ተዘግቧል። እንደ ጋዜጠኛ አርዶ ሃዛድ አባባል ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን የሽብር ጥቃቱን ከማስቆም ባሻገር መፍትኄ ሊያፈላልጉላቸው የሚገቡ በርካታ የቤት ሥራዎች ይጠብቋቸዋል።
«መፍትኄ ሊያገኙላቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ። የሰርጎ ገቦቹ ጉዳይ አለ። በሰርጎ ገቦቹ ታፍነው አሁንም ድረስ የሚሰቃዩ፣ ነፃ የሚያወጣቸውን ኃይል የሚጠብቁ 200 የቺቦክ አካባቢ ልጃገረዶች አሉ። ሠርጎ ገቦቹ ቦኮሐራሞች ከ15 እስከ 20 ከተሞችን ተቆጣጥረዋል። እነዚህ ከተሞች በናይጄሪያ መንግሥት ነፃ አልወጡም።»
ቦኮሐራምን የሚቃወም ሠልፍ

ቦኮሐራምን የሚቃወም ሠልፍ

ቺቦክ በደቡብ ናይጄሪያ ቦኮሐራም የሚቆጣጠረው አካባቢ ነው። በቺቦክ ከ6 ወራት በፊት 200 ሴት ተማሪዎች ከትምኅርት ቤታቸው በቦኮሐራም ታጣቂዎች ተጠልፈው እንደተወሰዱ ዛሬም አልተመለሱም። ከሦስት ቀናት በፊት በሰሜን ናይጄሪያ ፖቲስኩም ከተማ ውስጥ የተማሪዎች የደንብ ልብስን ለብሶ ተማሪዎች መካከል የአጥፍቶ መጥፋት ድርጊት መፈጸሙ ይታወሳል። በጥቃቱ ቢያንስ 48 ሰዎች ሲገደሉ፤ 79 ተማሪዎች ቆስለዋል። የአጥፍቶ መጥፋት ድርጊት በናይጄሪያ በተደጋጋሚ ይስተዋላል።ፕሬዚዳንቱ ግን ዛሬም ቃል ይገባሉ።
«ከመላው ናይጄሪያውያን ጋር ለመሥራት ቃል እገባለሁ። ከሁላችሁም ጋር ለመሥራት ቃል እገባለሁ።»
በእርግጥም ጋዜጠኛ አርዶ ሃዛድ እንደገለፀው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ለዳግም ምርጫ ራሳቸውን ከማቅረባቸው በፊት መፍትኄ ሊያፈላልጉላቸው የሚገቡ በርካታ ፈተናዎች ተጋርጦባቸዋል። ሆኖም ፕሬዚዳንቱ ከምንም በፊት ለዳግም ምርጫ የቆረጡ ይመስላል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic