የናይጀርያ የነዳጅ ዘይት | ጤና እና አካባቢ | DW | 05.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የናይጀርያ የነዳጅ ዘይት

ናይጀርያ ያለ ነዳጅ ዘይትዋ ምንም ነገርን ማንቀሳቀስን አትችልም። 80 በመቶዉ የሀገሪቱ ገቢ የሚገኘዉ ከዚሁ ከነዳጅ ዘይት ነዉ። ናይጀርያ የነዳጅ ዘይትዋን ከምድረ-ከርስ ማዉጣት ከጀመረችበት ከጎርጎረሳዉያኑ 1958 ዓ,ም ጀምሮ በከፍተኛ የነዳጅ ምርት አቅርቦት ከዓለም ስምንተኛ ደረጃን ይዛ ትገኛለች።

ይህ የነዳጅ ምርት በኒጀር ዴልታ ለሚኖሩ ህዝቦች ያስገኘላቸዉ አንዳችም ጥቅም የለም። በአንጻሩ በነዳጅ ምርቱ ሰበብ ህዝቦችዋ በተበከለ አካባቢ ላይ እንዲኖሩ መርዛማ ጋዝ አየርን በየቀኑ እንዲተነፍሱ ዳርጎቸዋል።

ቦዶ በሚሰኘዉ ወደብ ላይ አንድ አነስተኛ የሞተር ጀልባ ቆሞዋል። ቦዶ በኒጀር ዴልታ ደለል ላይ ከሚገኙት በርካታ መንደሮች እንዷ ናት። ደቡባዊ ምስራቅ ናይጀርያን ወጣ ብለዉ የሚገኙ ማህበረሰቦች ጀልባ እና አነስተኛ ታንኳ እጅግ አስፈላጊ የመጓጓዣ መሳርያቸዉ ነዉ።

አሳ ማስገርም ለምዕተ አመታት የኖረ ዋናዉ የገቢ ምንጫቸዉ ነዉ። በጎርጎረሳዉያኑ 2008 ዓ,ም መፀዉ ወራት ላይ በቦዶ ያለዉ ሁኔታ ከመቅስበት ተቀይሮአል። ይኸዉም ሼል ከተሰኘ የነዳጅ ማዉጫ ድርጅት የተዘረጋዉ የነዳጅ ዘይት ቧንቧ ተቀዶ የፈሰሰዉ ዘይት ከአንድ ሳምንት በላይ አካባቢዉን እና ዉሃን በክሎአል። የዚህ አደጋ ጠባሳ ከአራት አመት በኋላ ዛሪም አካባቢዉ ላይ በጉልህ ይታያል።

« እዚህ የዘይቱን ፍሳሽ እናያለን- በየመንገዱ፤ እዚያም በዉሃ ዉስጥ እንዲሁ። ይህን ዉሃ ተመልከት። በዉስጡ ምንም ህይወት ያለዉ ነገር አይታይም። እርግጠኛ ነኝ በቀድሞ ግዜ ሰዎች እዚህ የተለያዩ የዓሣ አይነቶችን ያዘምዱ ነበር። ኤኮነሚያችንም አድጎአል። ነገር ግን አሁን በነዳጅ ዘይት ብክለቱ ምክንያት እጅግ እየተሰቃየን ነዉ።»

ይላሉ-ቦዶ በተሰኘችዉ ገጠር የምክር ቤት ዋና ተጠሪ ሳይንት ኤማ ፔ። በዝያን ወቅት በዚህ ገጠር በደረሰዉ አደጋ ምን ያህል የነዳጅ ዘይት መፍሰሱን በተመለከተ የተለያዩ አመለካከቶች ነዉ የሚንፀባረቁት። እንደ ነዳጅ ዘይት አዉጭ ኩባንያ እንደ ሼል ገለፃ 4000 በርሜል ዘይት ፈስዋል፤ ዓለማቀፉ የሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅት Amnesty International በበኩሉ ከአስር ሳምንታት በላይ 311,000 በርሜል ዘይት መፍሰሱን እና ለመጠጥ ዉሃ ሊዉል በሚችለዉ በመሪት ዉስጥ በሚገኘዉ ዉሃ ዉስጥ ሰርጎ መግባቱን ነዉ የሚናገረዉ።

ፋራንሲስካ ዛቤ ይህ አደጋ በደረሰበት ሳምንት የነበረዉን ሁኔታ ሁሉ አሁንም በደንብ ታስታዉሳለች። በአካባቢዉ ላይ ትሰራ የነበረዉ ይህች አርሶ አደር እያደር ስራዋን እና የመተዳደርያ ገቢዋን ነዉ ያጣችዉ። «የነዳጅ ዘይቱ መሪት ዉስጥ ሰርጎ ከገባ ወዲህ፤ ወደ እርሻ መሄድ አልቻልኩም። ማንም እርሻ ቦታዉ ላይ አልነበረም። በአጠቃላይ ምንም አይነት ነገር ማምረት አልቻልኩም።» ያም ሆኖ ፋራንሲስካ ዛቤ ዘጠኝ ልጆችዋን እና እራስዋን አስተዳድራ ችግሯን ተወታለች። የምታዉቃቸዉ ሰዎች ረድተዋታል፤ በፊት ያስቀመጠችዉን ቆጥባ በመጠቀም ችግሯን አሸንፋለች። በችግር የጠወለገችዉ ይህች ሴት ወደፊት ህይወት በምን ሁኔታ እንደሚቀጥል ግን አታዉቅም። እስከ ዛሪ በነዳጅ ዘይት ስለተበከለዉ የእርሻ ቦታዋ ካሳ አገኛለሁ ብላም በመጠበቅ ላይ ናት። «ሼል እኛን መርዳት እና የሆነ ነገር ማድረግ አለበት። ከዚህ ቀደም መተዳደርያ ገንዘብ የምንሰራበት ቦታ ዛሪ መሄድ አንችልም። ይህ ሁሉ በፈሰሰዉ ዘይት ምክንያት ነዉ።»

በ1950ዎቹ ዓመታት ለመጀመርያ ግዜ በናይጀርያ የነዳጅ ዘይት መኖሩ በታወቀ ግዜ የሀገሪቱ የወደፊት አስተማማኝ መስሎ ነበር። ጥቁር ወርቅ ተብሎ የሚታወቀዉ የኒጀር ዴልታ የነዳጅ ዘይት ግኝት ለናይጀርያ እድገትን እና ሃብትን እንዲሁም በሃብታም ሀገሮች ተርታ በትንሹም ቢሆን የመሰለፍን ተስፋን አጎናፅፎ ነበር። ግን ይህ ሁሉ ተስፋ እና ምኞት ወድያዉ ጨለመ- በጎርጎረሳዉያኑ 1958 ዓ,ም የነደጅ ዘይቱ መዉጣት በጀመረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ። ከኦሞኩ የመጡት ጡረተኛዉ ሃኪም የኢኖሲንት ማሲም ሁኔታም ይኸዉ ነዉ። ኦሞኩ የኒጀር ዴልታ ትልቁ ከተማ ከሆነዉ ሃርኩርት ከሰሜናዊ ወደብ የአንድ ሰዓት የመኪና መንገድ ላይ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ናት።

«ሁሉ ነገር የነዳጅ ዘይት አዉጭ ድርጅቶቹ በጎርጎረሳዉያኑ 1962 ላይ ሲመጡ ተቀየረ። እኔ ራሴ በዝያ ወቅት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በመከታተል ላይ ነበርኩ። በ ጎርጎረሳዉያኑ 1976 ዓ,ም የከፍተኛ ትምህርቴን አጠናቅቄ ስመለስ የነበዉ ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ነበር። እንደ አንድ ሃኪምም ሁኔታዉ ሁሉ መቀያየሩንም ተረዳሁ። »

በለንደን የህክምና ሞያ ትምህርታቸዉን አጠናቀዉ ለመጡት ሃኪም፤ በአካባቢዉ ላይ የሚታየዉ የነዳጅ ዘይት ንግድ ሁኔታ ለጤና እጅግ አደገኛ ና አሳሳቢ ሆነባቸዉ። ነዳጁ በሚወጣበት ግዜ የሚቀረዉን ቆሻሻ ዝቃጭ ያለምንም ጥንቃቄ እና በርካሽ በማቃጠላቸዉ መርዛማ ጢስ ያስከትላል። ይህ ዘዴ እንዳይፈጸም ከጎርጎረሳዉያኑ 1984ዓ,ም ጀምሮ በህግ ተከልክሎአል። ነገር ግን በነዳጅ ዘይት ምርት የከባቢ አየርን እና አካባቢን በማቆሸሽ ረገድ ናይጀርያ በዓለም መዘርዝር ዉስጥ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ትገኛለች። በቅርቡ የዓለም ባንክ ያደረገዉ ጥናት እንደሚያሳየዉ የተቃጠለ ጋዝን በብዛት ወደ አየር በመልቀቅ ሩስያ ቀደምቱን ቦታ ይዛ ትገኛለች።

«በርካታ ሰዎች በቆዳቸዉ ላይ መርዛማ ጋዝ ንጥረ ነገር እንዳለ ይታያል። ከሌሎች አካባቢ ይልቅ ሴቶች የፅንስ ችግር ይገጥማቸዋል። በሌላ በኩል የቤቶች ጣርያም ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ እንደቀድሞዉ ጠንካራ አይደሉም። ይህን ሁሉ ነዉ ለመገንዘብ የቻልኩት።»

መርዛማ ጋዝ - የሚለዉን ርዕስ እንደ ሼል ያሉ የተለያዩ የነዳጅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሊያገናዝቡት ሊነጋገሩበት አይፈልጉም። ሼል በዓለማችን ከሚገኙ ታላላቅ የነዳጅ አምራች ድርጅቶች የሚመደብ ሲሆን በናይጀርያ ነዳጅን በማምረት ከ 50 ዓመታት በላይ አስቆጥሮአል። በናይጀርያ ሼል የነዳጅ አምራች ድርጅት ዉስጥ ለዘላቂ እድገት እና የማህበረሰብ ግንኙነት ክፍል ዋና ተጠሪ ፊሊፕ ምሸልቢላ ወቀሳዉን ይነቅፋሉ።

«እንደኔ አስተሳሰብ የነዳጅ ጋዝ ቆሻሻ የጤና ጠንቅ ነዉ፤ የሚለዉ አስተሳሰብ የተጋነነ ነዉ። በርግጥ በከባቢያችን አና በአየር ሁኔታ ላይ ተጽኖን ያሳድራል፤ ነገር ግን ይህ እንዳይከሰት እንዲሁም የህብረተሰቡን ጤንነት እና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እንጥራለን። ነዳጅ ጋዝ ከምድረ-ከርስ ሲወጣ የሚቀረዉን ዝቃጭ ማቃጣል የሚለዉን ዘዴ እያነሳን እንወያያለን።» ነዳጅ ጋዝ በሚወጣበት ግዜ ቀላል እና ርካሽ በሆነ የማቃጠያ ዘዴ ጥቅም ላይ ጨርሶ እንዳይዉል ከጎርጎረሳዉያኑ 2013 ጀምሮም ተነግሮአል። እንደ Petroleum Industry Bill ገለጻ ብዙ ዉይይቶች የተካሄዱበት እና ይህንን የሚደነግግ የህግ ረቂቂቅ ተካሂዶአል። ግን ይህ ህግ በታቀደዉ ሰዓት ገቢራዊ መሆኑ አሁንም አጠያያቂ ነዉ። እንዲያም ሆኖ ይህ የህግ ረቂቅ ቢፀና በኒጀር ዴልታ አካባቢ ያለዉን ህይወት በአወንታዊ መልኩ ሊቀይረዉ ይችላል። ፊሊፕ ምሸልቢላ በዚህ ጉዳይ እምነት አላቸዉ። እንደ ፊሊፕ ህጉ እስኪፀና ሼል ጥሩ እርምጃ መዉሰድ አለበት ባይ ናቸዉ፤

« በርግጥ በዓለም ዙርያም ሆነ በገጠሩ አካባቢ እኛ እንቅስቃሴ በምናደርግበት ሁሉ ተፅኖ እናደርጋለን። በዚህም በትክክለኛዉ መንገድ ፕሮጄዎችን እንፈልጋለን። እነዚህ ፕሮጄዎች ታድያ በመጀመርያ ደረጃ ጋዙ እና የነዳጅ ዘይቱን የሚያወጣ ሥራ ሊያስከትል የሚችለዉን አሉታዊ ጉዳዮች መቀነስ፤ በሁለተኛ ደረጃ በአካባቢዉ ላይ የሚኖረዉን ህብረተሰብ የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ነዉ» የዚህ ፕሮጄ ዋናዉ ተግባር በሼል እና በኔጀር ደልል አካባቢ በሚገኙ ማህበረሰቦች መካከል በጽሁፍ የረቀቀ ዉል መፍጠር ነዉ። እንደ ሼል ኩባንያ ገለጻም እስከ ጎርጎረሳዉያኑ 2011 ዓ,ም መጨረሻ ለዚሁ ጉዳይ 79 ሚሊዮን ዶላር ወጭ አድርጎአል።

Jan 26, 2005; Ogoni, Rivers State, NIGERIA; K-Dere Community; Farmer Bakpa Birabil stands in front of two leaking oil wells on his farm, which has been owned by his family for centuries. The oil well (on his property) has been leaking for the past year without attention from Shell. Multinational oil companies, including Shell Oil (the biggest oil company in the Niger River Delta) have drawn attention because of poor business practices and inability to work with local communities. Tension between Nigerians living in the area, the Nigerian government and the oil production industry has made the Niger River Delta one of the most dangerous and volatile places on earth to conduct business. Mandatory Credit: Photo by Mark Allen Johnson/ZPress +++(c) dpa - Report+++

ገንዘቡ በምን ላይ ይዋል ለሚለዉ ጥያቄ የአካባቢዉ የማህበረሰብ ተጠሪዎች እንደሚወስኑ ነዉ የተነገረዉ። አንዳንዶች የትምህርት ቤቶችን ህንጻ አድሰዋል፤ አልያም የሄሊኮፕተር ማረፍያ ሜዳዎችን ሰርተዋል። በሌሎች ቦታዎችም አነስተኛ የህክምና ጣብያዎች ተገንብተዋል። ከዚህ መካከል ታድያ፤ በሃር ኮርት ወደብ አቅራብያ የሚገኘዉ ኦቢዎ ኮቴጅ ሆስፒታል ይገኝበታል። ዶክተር አልፍሪድ ኤጊግባ አንድ ታካሚን ሰላምታ ያቀርባሉ። የዘጠኝ ወር ቅሪትዋ ሴት ፤ የተለመደዉን የህክምና ቁጥጥር ለማድረግ መጥተዉ ለአራት ሰዓታት ጠብቀዋል። ይህ ሆስፒታል በተለይ ለእርግዝና ክትትል እና በወሊድ እርዳታ ልዩ ስልጠና ያደረገ ሆስፒታል መሆኑን የህክምና ባለሞያዉ ወደ ምርመራ ክፍል እያመሩ ያስረዳሉ።

«እዚህ ምን እንደሚሰራ ተመልከት! ለምሳሌ በዚህ ጠረቤዛ ላይ አዲስ የሚመጡ ታካሚዎችን እንመዘግባለን። ይህ ደግሞ ሁሉ አይነት ምርመራን የምናካሂድበት ላብራቶሪያችን ነዉ። በተለይ ደግሞ የእርጉዝ ሴቶች HIV በደማቸዉ መኖር አለመኖሩን የምንመረምርበት ነዉ። ምርመራዉ የሚካሄደዉ በነፃ ነዉ። ይህ ሁሉ ሊሟላልን የቻለዉ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ከሼል ጋር በጥምረት በመስራቱ ነዉ።» በቤኒን በደቡባዊ የኤዶ ክፍለ ከተማ ዩንቨርስቲ ክሊንክ ዉስጥ በፕሮፊስርነት ማዕረግ የሚያገለግሉት የህክምና ባለሞያ፤ ለአንድ ዓመት ፈቃድ ወስደዉ በሼል የህክምና ማዕከል ዉስጥ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ሃኪሙ በሼል የህክምና ማዕከል ከሚገኙት የስራ ባልደረቦቻቸዉ ጋር ያለዉን ስራ በተለይም የስራ አጋራቸዉን የነዳጅ ዘይት አምራች ኩባንያ ከፍ በማድረግ ያወድሳሉ።

ህሙማኑም ቢሆኑ ከዚህ የተለየ አይደለም የሚሉት። ሼል ኩባንያ አነስተኛ የህክምና ጣብያ ዉስጥ መዋለንዋዩን ከማፍሰስ ይልቅ ሌላ ሰፋ ያለ የህክምና ማዕከል መገንባት አይገባዉምን? ለሚለዉ ጥያቄ ኦይኔዪ ቤን መልስ ይሰጣሉ። «እዚህ ያሉ ሰራተኞች ጠንክሮ ለመስራት በጣም ይጥራሉ። መድሃኒቱንም ቢሆን ከሼል ነዉ የምንቀበለዉ። ሁልግዜ የሚሰጡን መድሃኒቶች ከዉጭ የመጡ ናቸዉ። ለኛ የሚያደርጉት እንክብካቤ በጣም ያስደስተኛል። ለዚህም ነዉ እኔ ወደዚህ የመጣሁት። ፕሮፊሰሮቹ እና የጤና ረዳቶቹ በደንብ እንደሚንከባከቡን በግልጽ የሚታይ ነዉ። እጅግ ጥሩ ሆስፒታል በመሆኑ ሰዉ ወደዚህ እንዲመጣ እመክራለሁ።»

ዓሣ አጥማጅ ወደ በዛባት ወደ ቦዶ ገጠር እንመለስ። በሜዳ ላይ አንድ ሁለት ሰዎች ጀልባቸዉን ሲጠግኑ ይታያል። የቦዶ ገጠር መንደር ተጠሪ ሳይንት ኤማህ ፒ አካባቢዉ ላይ እየተዘዋወሩ ሁኔታዉን በመቃኘት ላይ ናቸዉ። እንደሳቸዉ አስተያየት የተሰራዉ ስራ በሙሉ ጥቅመ ቢስ እና አላስፈላጊ ነዉ። በአሁኑ ወቅት ዓሣ በማስገር ማንንም እራሱን ማስተዳደር አይችልም። አካባቢዉ ላይ ሌላ አይነት ስራም የለም። ይህንን ችግር ለመፍታት ሼል እስካሁን ምንም አይነት ጥረት አላደረገም ሲሉ ሳይንት ኤማህ ፒ ይከሳሉ።

«ሼል በቦዶ መንደር እስካሁን ምንም አይነት ፕሮጄ አላቋቋመም። በጎርጎረሳዉያኑ 2008 እና 2009 ዓ,ም ከደረሱት የነዳጅ ዘይት መፍሰስ አደጋዎች በኋላ ወደ ሼል ሄደን መታችሁ እድሳት አድርጉ፣ ከአደጋዉ የተረፈዉ በቀጣይ ህይወት እንዲኖረዉ፤ የሆነ ነገር አድርጉ ብለን ተናግረን ነበር። ግን ሁሉም ነገር እስኪወድም ድረስ ምንም ነገር አላደረጉም። በአንጻሩ ለ 69,000 ነዋሪ አምስት ጆንያ ባቄላ ነዉ የላኩት። አክለዉ መቶ ጆንያ ሩዝ እና ሁለት ቦንዳ ፓዉደር ወተት ነዉ የሰጡን። ይህ በእዉነቱ ቀልድ ነዉ!»

እንድያም ሆኖ ተስፋዉ ጨርሶ አልተሟጠጠም። የተ,መ,ድ,የከባቢ አየር ጥበቃ መረሃ-ግብር ባለፈዉ አመት ባደረገዉ ጥናት እንዳሳየዉ የቦዶ ገጠር መንደር ክልል የሆነዉና ከ800,000 በላይ ህዝብ የሚኖርበት የኦጎኒላንድ አካባቢ በነዳጅ ዘይት ተበክሎአል። የናይጀርያ መንግስት እና የነዳጅ ዘይት አምራች ድርጅቶች ሁኔታዉን በአፋጣኝ መከታተል እንዳለባቸዉ የተ,መ,ድ,የከባቢ አየር ጥበቃ መረሃ-ግብር ያሳስባል። በተጨማሪ ለዚሁ አላማ፤ ለምሳሌ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰብያ እንድያደርጉ ይመክራል። ይህ ገንዘብ በመጀመርያዎቹ አምስት አመታት ለፅዳት መረሃ-ግብሩ ማስፈጸምያ እንደሚዉል ያመለክታል። ቢሆንም ቅሉ ይህ ጥናት ይፋ ከሆነ ከአንድ ዓመት በላይ ግዜ ምንም የተፈጸመ ነገር ባለመኖሩ የቦዶ ነዋሪዎች ሁኔታዉን እራሳቸዉ ለማስተካከል ቆርጠዉ ተነስተዋል። ይኸዉም የቦዶ መንደር ተጠሪ ሳይንት ኤማህ ፒ እንደሚሉት፤ በአንድ እንግሊዛዉ ጠበቃ ረዳትነት፤ የነዳጅ ዘይት አምራች ኩባንያዉን በመክሰስ ለንደን ላይ ለፍርድ አቅርበዉታል። «የኛ ጉዳይ በለንደን ፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን እገልጻለሁ። በሼል ድርጅት ተቀባይነትን ያገኙ ጥሩ ጥሩ ማስረጃዎች አሉን። በነዳጅ ዘይት የተከሰተዉ አደጋ በርግጥ በቴክኒካዊ ችግሮች ነዉ። ስለዚህ መቼ ነዉ፤ የደረሰዉን ጥፋት አስተካክለዉ ለኛ ካሳ የሚከፍሉን በሌሎች ቦታዎች የደረሰዉንም ጥፋት እንደሚያስተካክሉ ሁሉ መቼ ነዉ የኛን የሚያስተካክሉት?»

በግብርና ስራ የምትተዳደረዉ ፍራንሲስካ ዛቤም ይህንኑ ነዉ ማወቅ የምትፈልገዉ። ግዜዉ ቀትር ላይ ነዉ። የምሳ መብያ ሰዓት ደርሶአል። ተነስታ በናፍጣ በሚሰራዉ ምድጃዋ ላይ ለምሳ የሚሆን ምግብ ማብሰል ትፈልጋለች። ለዛሪ ሩዝ ከመቀቀል በስተቀር ሌላ ነገር ለማዘጋጀት በቂ ገንዘብ የላትም። ግን ከለታት አንድ ቀን የተሻለ ምሳን ለቤተሰብዋ ማዘጋጀት ትችል ይሆናል፤ ለምሳሌ ሼል በርግጥ ካሳ ለቦዶ ነዋሪዎች ሲከፍል። ፍራንሲስካ ዛቤ ይህን የካሳ ገንዘብ ስትቀበል ታድያ ልታደርግ የምትችለዉን ነገር ጠንቅቃ ታዉቃለች። «ይህ ገንዘብ ከተሰጠኝ፤ አንድ ትንሽ ሱቅ ከፍቼ በማገኘዉ ገቢ ልጆቼን እና እራሴን አስተዳድራለሁ። »

ከቦዶ የመጡት ከሳሾች የማሸነፍ ተስፋ እንዳላቸዉ የህግ አዋቂዎች ይገልጻሉ። የነዳጅ አምራች ኩባንያዉ መስራ ቤት ዋና መቀመጫ በሆነዉ በኔዘርላንድ፤ ዴን ሃግ ፍርድ ቤትም በቅርቡ አንድ የናይጄርያ የገበሪ ቡድን ክስ መስርቶአል። ቡድኑ በናይጀርያ በቅርቡ የነዳጅ ቧንቧ ተሸንቁሮ የፈሰሰዉ ዘይት እንዲጠረግ እና ካሳ እንዲከፈዉ ይጠይቃል። ክሱ በሚቀጥለዉ ወር ዉሳኔ እንደሚያገኝ ይጠበቃል። ምናልባት ሼል ከተፈረደበት በተለያዩ ዓለም አገራት የተጠየቀዉን በቢሊዩን የሚቆጠር ካሳ መክፈል ይኖርበታል።

ካትሪን ጌንዝለር/አዜብ ታደሰ

ሸዋዪ ለገሰ

Audios and videos on the topic