የናይጀሪያ ጦር ርምጃና የሲቭሉ ማ/ሰብ ተቃውሞ | አፍሪቃ | DW | 11.06.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የናይጀሪያ ጦር ርምጃና የሲቭሉ ማ/ሰብ ተቃውሞ

በናይጀሪያ ብዙ ታዛቢዎች ከቁጥጥር ውጭ ሆኖዋል የሚሉት የጦር ኃይል በካኖ ግዛት የሀገሪቱ ጋዜጦች እንዳይታተሙ ማከላከል መያዙ ተገለጸ። ከዚህ በተጨማሪ በካኖ አዲስ በተሾሙት ኤሚር እና በአመራረጣቸው ላይ ብርቱ ወቀሳ አፈራርቋል።

የናይጀሪያ ሲቭል ማህበረ ሰብ ይህንኑ የጦር ኃይል ርምጃ የዴሞክራሲያዊውን ሥርዓት የሚሸረሽር ነው በሚል በጥብቅ ተቃውሞታል።

በተለያዩት የናይጀሪያ ከተሞች ሂስ አዘል ርዕስ የሚነበብባቸው በርካታ ጋዜጦች የሚሸጡ የጋዜጣ መሸጫ መደብሮች በየጥዋቱ በስው ተሞልተው ነው ይታያሉ። ከዚህ በተጨማሪም ብዙ ወጣቶች በየመንገዱ በትራፊክ መጨናነቅ ሰበብ ለቆሙት ተሽከርካሪ ሾፌሮች እና ለሌሎች የመጨረሻው ትኩስ ዜና የሚነበብባቸውን ጋዜጦች እያዞሩ ይሸጣሉ። ይህም ሆኖ ግን፣ በህትመቱ ዘርፍ የተሠማሩ ጋዜጠኞች እና አሳታሚዎች በአሁኑ ጊዜ ትልቅ ችግር አጋጥሟቸዋል። የናይጀሪያ ጦር ኃይል «ሊደርሺፕ» ወይም « ዘ ፓንች »ን የመሳሰሉትን ትላልቅ ጋዜጦችን ሕትመት ባለፉት ጥቂት ቀናት በተደጋጋሚ በመውረስ የጋዜጦቹን ስርጭት አከላክሎዋል። ይኸው የጦር ኃይሉ ርምጃ የናይጀሪያ የጋዜጠኞች ህብረት ፕሬዚደንትን ጋርባ መሀመድ አሳስቧቸዋል።

« ይህ ለዴሞክራሲያችን በጣም በጣም አሳሳቢ ስጋት፣ ለናይጀሪያ የጋዜጠኝነት ሙያም ስጋት እንደሆነ ይሰማናል። አሁን እየተደረገ ያለው የናይጀሪያን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ይሸረሽረዋል። የመገናኛ ብዙኃንን እና ጋዜጠኞችን የሚያስፈራራ ርምጃ ነው። በመሆኑም በጥብቅ አውግዘነዋል። »

የጦር ኃይሉ ይኸው ርምጃው የሚያስከትለውን መዘዝ በሚገባ ሊረዳው እንደሚገባ ጋርባ መሀመድ አሳስበዋል። የጦር ኃይሉ ይህንኑ ርምጃ የወሰደው የጋዜጦቹን ይዘት ለማገድ ሳይሆን ከፀጥታ ጥበቃ ጋ የተዛመደ መረጃ እንዳይወጣ ለማከላከል ብቻ ያደረገው እንደሆን አስታውቋል። ይሁንና፣ በትልቋ የሰሜን ናይጀሪያ ከተማ፣ ካኖ የሚገኘው መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት፣« ዴሞክራቲክ አክሽንግሩፕ» አባል ሙሀማድ ሙስጠፋ ያህያ እንዳስታወቁት፣ ይህ ዓይነቱ አንጋገር ናይጀሪያ ውስጥ ማንንም፣ የሲቭሉን ማህበረሰብም አያረጋጋም። « ይህ በፍፁም ኢዴሞክራሲያው እና የማያበረታታ አሰራር ነው። እና የሀገሪቱ ፕሬዚደንት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሥልጣኖች ይህንን የጦር ኃይሉን ርምጃ እንዲያወግዙ እጠብቃለሁ። »

ነገር ግን፣ በናይጀሪያ ይህ ይሆናል ብሎ የሚጠብቅ ሰው የለም። እስካሁን መንግሥት ስለዚሁ ጉዳይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቦዋል። የጦር ኃይሉ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖዋል በሚል ስለሚሰማው ዜና ጋዜጠኞች ለሚያቀርቡት ጥያቄ በመዲናይቱ አቡጃ የሚገኙ ፖለቲከኞችም ሆኑ የመንግሥት ተወካዮች መልስ ለመስጠት ዝግጁ አልሆኑም። በአንፃራቸው ሙሀማድ ሙስጠፋ ያህያ ስለ ጦር ኃይሉ እንዲህ ይላሉ።

« አዎ፣ አዝማሚያዎች ሲታዩ፣ የጦር ኃይሉ በርግጥ እየተጠናከረ ነው። ይህ ለዴሞክራሲያችን ጤናማ አይደለም። »

ከዚሁ ጎን ደግሞ የቀድሞው የሀገሪቱ ማዕከላይ ባንክ ፕሬዚደንት ሳኑሲ ላሚዶ ባለፈው እሁድ የካኖ ኤሚር ሆነው መሾማቸው ብዙ እያነጋገረ ነው። እንደሚታወቀው፣ በናይጀሪያ ሙሥሊሞች እና በካኖ ባህላዊ ልማድ ዘንድ ኤሚር ከሶኮታ ሱልጣን ቀጥሎ ሁለተኛው ከፍተኛ ሹመት ነው። እና ከጥቂት ወራት በፊት ከማዕከላዩ ባንክ 20 ቢልዮን ዶላር መጥፋቱን ካጋለጡ በኋላ የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን ከሥልጣናቸው ያሰናበቱዋቸው ሳኑሲ ለዚህ ከፍተኛ ሥልጣን መብቃታቸው ብዙዎችን አላስደሰተም።

ከሁለት ዓመት በፊት ከፕሬዚደንት ጆናታን በመራቅ የተቃዋሚውን የሕዝብ ኮንግረስ ፓርቲን የተቀላቀሉት የካኖ ግዛት አስተዳዳሪ ራቢ ሙሳ ክዋንክቫሶም ፣ ከ51 ዓመት ሥልጣን ዘመን በኋላ የሞቱትን ኤሚር አዶ ባየሮን እንዲተኩ ከቀረቡት ሦስት ተወዳዳሪዎች መካከል ሳኑሲ ላሚዶን መርጠዋል፣ ይሁንና፣ እንደ ሙሀማድ ሙስጠፋ ያህያ አስተያየት፣ ተቀናቃኞቹ ቡድኖች አሁን የሥልጣን ሽኩቻቸውን ሊያበቁ ይገባል።

« አሁን ሳኑሲ ላሚዶ ኤሚር ሆነው በመመረጣቸው የቆዩ ችግሮች ሊረሱ እና ይቅር ሊባሉ ይገባል። የሀገሪቱ ፕሬዚደንት እና አዲሱ ኤሚር ጥሩ የስራ ግንኙነት መፍጠር ይኖርባቸዋል፣ ይህ ለሀገሪቱ እና ለሕዝቧ ጥሩ መፍትሔ ነው። »

እርግጥ፣ ገዢው የናይጀሪያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ዓርቲ ሳኑሲን የእንኳን ደስ ያልዎት መልዕክት ቢያስተላልፍም፣ አዲሱ ኤሚር ስራቸውን ከፖለቲካ ጥቅም በመራቅ በገለልተኝነት እንዲያከናውኑ ከማሳሰብ ወደ ኋላ አላለም። የናይጀሪያ መንግሥት የአዲሱ ኤሚር ሹመት ይፋ ከሆነ ወዲህ በካኖ አጠናክሮ መውስደ የጀመረው ርምጃ በዚያ በክርስትያኖች እና በሙሥሊሞች መካከል አለመተማመኑ እንዲባባስ ያደርጋል በሚል የፖለቲካ ታዛቢዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል። ያም ቢሆን ግን፣ መንግሥት እና የጦር ኃይሉ አንፃራቸው ሂስ በሚሰነዝሩ የተቃዋሚ ቡድን አባላት እና የመገናኛ ብዙኃን ላይ በዚሁ ርምጃቸው ለመቀጠል የወሰኑ መስሎዋል።

ካትሪን ጌንስለር/አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic