የናይጀሪያ እጩ ፕሬዝደንታዊ ተፎካካሪዎች | አፍሪቃ | DW | 12.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የናይጀሪያ እጩ ፕሬዝደንታዊ ተፎካካሪዎች

ናይጀሪያ በመጪዉ በምታካሂደዉ የምርጫ ፉክክር ለፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩት እጩዎች ማንነት ታወቀ። ዋናዉ ተቃዋሚ ፓርቲ የእድገት ኃይሎች ምክር ቤት በምርህፃሩ APC በጡረታ ላይ የሚገኙትን የቀድሞዉ ወታደራዊ መሪ ሜጀር ጀነራል ሙሀማዱ ቡሀሪን እጩ ፕሬዝደንት አድርጎ አቅርቧል።

ገዢዉ የሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ PDP ስልጣን ላይ የሚገኙትን ፕሬዝደንት ጉድላክ ጆነተንን ያለተቀናቃኝ እንዲወዳደሩ ወስኗል። ናይጀሪያ አሁን ለገጠማት የፀጥታ ስጋት መፍትሄ የሚያመጣ መሪ እንደምትፈልግ ቢታመንም የትኛዉ እጩ ለዚህ እንደሚበቃ ምን የተጨበጠ ነገር የለም ።

ናይጀሪያ ቦኮሃራም የሚያደርሰዉ የጥቃት ርምጃ ተባብሶ ስጋት ቢወጥራትም የፊታችን የካቲት ወር አጋማሽ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅቷን እያገባደደች ነዉ።ተፎካካሪ እጩ ፕሬዝደንቶች ከተቃዋሚዉ ወገንም ሆነ ከገዢዉ ፓርቲ ተሰይመዋል።በተቃራኒዉ ጎራ ተፎካካሪዎቻቸዉን በሰፊ ልዩነት በልጠዉ ለእጩነት የተመረጡት የቀድሞዉ የናይጀሪያ ወታደራዊ መሪ ሜጀር ጀነራል ሙሀማዱ ቡሀሪ ከካኖ ግዛት ሴናተር ራቡ ኩዋንኳሶ እና ከቀድሞዉ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝደንት አቲኩ አቡባከር የላቀ ድምፅ ያገኙት በሌላ ሳይሆን ሀገሪቱ ከገባችበት የፀጥታ ስጋት የሚያወጣት አመራር ይሰጣሉ የሚል እምነት ስለተጣለባቸዉ እንደሆነ ነዉ የሚገልፁት።

Nigeria - nominierter Präsidentschaftskandidat Muhammadu Buhari

የቀድሞዉ የናይጀሪያ ወታደራዊ መሪ ሜጀር ጀነራል ሙሀማዱ ቡሀሪ

«የእኔ መታጨት ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ይበልጥ የተሻልኩ ስለሆንኩ አይደለም። ዉድ ሀገራችን ናይጀሪያ ከምትገኝበት ሀገራዊ አለመረጋጋት፣ እንዲሁም ሃይማኖታዊ መከፋፈል እና በሕዝቡ መካከል ተስፋ መቁረጥ የምትወጣበትን ፋና እጅ ለእጅ ተያይዘን በመተማመን እርምጃ እንድወስድ ኃላፊነት የሚሰጥ ይመስለኛል።»

ከዚህም ሌላ ገዢዉ የሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በስልጣን ላይ የሚገኙትን ፕሬዝደንት ጉድላክ ጆናተንን በምርጫዉ እንዲወዳደሩ ያለምንም ተቀናቃኝ በእጩነት አቅርቧል።እናም ባለፈዉ ምርጫ እንደሆነዉ ሁሉ ጆናተንና ቡሀሪ ለፕሬዝደንታዊ ምርጫ ፉክክር በመጪዉ የናይጀሪያ ምርጫ ይፋጠጣሉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ2011ዱ የናይጀሪያ ምርጫ ከዓመት አስቀድሞ በቀድሞዉ የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ዑማሩ ያራዱዋ ሞት ምክንያት ወደስልጣን የወጡት ጉድላክ ጆናተን የተከፋፈሉትን የሀገሪቱን ተቃዋሚዎች ልቀዉ ለድል በቅተዋል።የናይጀሪያ አክሽን ኤድ ባልደረባ ሁሳይኒ አብዱ አሁን ሁኔታዎች በመጠኑም ቢሆን የተለወጡ መሆናቸዉን ይናገራል።

Nigeria Anschlag 28.11.2014

የቦኮሃራም አጥፍቶ ጠፊ ጥቃት

«ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጫዉ የሚካሄደዉ ጠንካራ ተቃዋሚ ባለበት ነዉ። ከ1991ዓ,ም በቀር የትኛዉም ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እንደአሁኑ ያለ ጠንካራ ተቃዋሚ ኃይል አልተሳተፈበትም። አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሁለት ዓመት በፊት ተዋሕደዉ አዲሱን APC ፓርቲን መስርተዋል። ይህ ደግሞ የዚህን ሀገር የምርጫ አካሄድ ለዉጦታል። በጣም ጠንካራ ፉክክር እንጠብቃለን።»

ያ ማለት ግን ለAPCም ቢሆን ነገሮች ቀላል ይሆናሉ ማለት አይደለም። አፍሪቃ ዉስጥ ስልጣን ላይ ያለ ፕሬዝደንትን በምርጫ አሸንፎ ማስወገድ በጣም አስቸጋሪ መሆኑን አብዱ ሳይገልፅ አላለፈም። ለዚህም ዋናዉ ምክንያት መንግታዊ ተቋማትና የፀጥታ ኃይሉን ገዢዉ ወገን ስለሚጠቀም ነዉ። የቀድሞዉ በናይጀሪያ የፍሬዴሪሽ ናዉማን ተቋም ኃላፊ ሃይንሪሽ በርግሽትረሰር ከምርጫዉ አስቀድሞ በአንዳንድ አካባቢ መንግሥት በAPC ላይ ዘመቻ መክፈቱን ነዉ የሚናገሩት።

«ከምርጫዉ አስቀድሞ ኤኪቲ በተባለችዉ ግዛት መንግሥት በAPC ደጋፊዎች ላይ የፖሊስን የኃይል ርምጃ ጨምሮ ዘመቻዉን ጀምሯል። እናም በቃጣይ ሳምንታት በተቃዋሚዎች ላይ የሚደርሰዉ ማዋከብ እስከአካላዊ ጥቃት ድረስ እንደሚሄድ መጠበቅ አለብን።»

Nigerianischer Präsident Goodluck Jonathan 11.11.2014

ፕሬዝደንት ጉድላክ ጆናተን

ናይጀሪያዉ የፖለቲካ ተንታኝ ኮሌ ሼቲማ በሀገሪቱ ምርጫ ማግስት ያለፈዉን ጥቁር ታሪክ ያስታዉሳሉ። ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2011 በኋላ በተፈጠረዉ አለመረጋጋት ወደ973 ሰዎች ገደማ ሕይወታቸዉን አጥተዋል። አሁንም ተመሳሳይ እጩዎች ናቸዉ የሚፎካከሩት በዚህ ምክንያትም ስጋቱ ከፍ ያለ መሆኑን ያስገነዝባሉ። በዚህ ምርጫ ሊያሸንፍ የሚችለዉ ከቦኮሃራም ስጋት ኅብረተሰቡን የሚገላግልበት መፍትሄ ያለዉ እጩ እንደሚሆን ነዉ ብዙዎች የሚስማሙት። ፕሬዝደንት ጆነታን በሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል ያወጁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ጦርኃይላቸዉን አሰልፈዉ ቦኮሃራም ላይ የከፈቱት ዘመቻ ዉጤት ሳያሳይ እንደዉም በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እየተወቀሰ ከዓመት በላይ ዘልቋል። ተቀናቃኛቸዉ ቡሀሪም ቢሆኑ ለዚህ ችግር ያቀረቡት ይህነዉ የሚባል መፍትሄ አልተሰማም። በርካታ ታዛቢዎችም ቡሀሪ ስልጣን ቢይዙ ለናይጀሪያ አዲስ የሚባል ጅማሬ ማምጣታቸዉን ይጠራጠራሉ። እንደዉም እሳቸዉ ስልጣን ላይ በነበሩት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1983 እስከ 1985 ወታደራዊዉ አገዛዝ መገናኛ ብዙሃንን ሲያሳድድ መኖሩ ተመዝግቧል። እንዲያም ሆኖ በመጪዉ የየካቲት ናይጀርያ በምታካሂደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ጉድላክ ጆናተን ቢያሸንፉም ይህ ነዉ የሚባል ለዉጥ ለናይጀሪያዉያን አይጠበቅም፤ ለእሳቸዉ ግን በአንጋፋዉ ፖለቲከኛ ላይ ድል ተቀዳጁ ይባልላቸዋል።

ፊልፕ ዛንደነር/ ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic