የናይጀሪያ ምርጫ እና የአውሮጳ ህብረት ታዛቢ ቡድን | አፍሪቃ | DW | 30.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የናይጀሪያ ምርጫ እና የአውሮጳ ህብረት ታዛቢ ቡድን

በናይጀሪያ አጠቃላይ ምርጫ ሊጀመር ሶስት ሳምንታት ገደማ በቀሩት ባሁኑ ጊዜ የአውሮጳ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን አባላት ወደ ናይጀሪያ እንደሚልክ አስታውቋል፣ ይሁንና፣ ታዛቢዎቹ የፀጥታ ችግር ወደሚታይበት ሰሜናዊ የሀገሪቱ ከፊል እንደማይሠማሩ የታዛቢው ቡድን መሪ ሳንቲያጎ ፊሳስ ገልጸዋል።

የናይጀሪያ የምርጫ ባለሥልጣናት ምርጫው ፅንፈኛ የሙሥሊሞች ቡድን ቦኮ ሀራም ብዙ ቦታ በተቆጣጠረበት በሰሜናዊው ከፊል፣ በተለይም ፣ ጠንካራ ሰፈሩ በሚገኝበት ቦርኖ ግዛት ሊካሄድ እንደማይችል ከወዲሁ አመልክተዋል።

የአውሮጳ ህብረት እአአ የፊታችን የካቲት 14፣ 2015 ዓም በናይጀሪያ ለሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ ወደዚችው ሀገር ባለፈው ህዳር ወር ቀዳሚ የታዛቢ ቡድን መላኩ ይታወሳል። የህብረቱ ታዛቢ ቡድን ስምሪቱን አስመልክቶ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፣ ታዛቢዎቹን ወደ ሰሜናዊ ናይጀሪያ ላለማሠማራት መወሰኑን አስታውቋል። ይኸው ውሳኔው በዚሁ አካባቢ የሚታየው የፀጥታ መጓደል ምን ያህል ምርጫውን ሊጎዳ ይችላል በሚል በብዙዎች ዘንድ ስጋት ፈጥሮዋል። በምርጫ ሂደት ወቅት የሚደረግ ቁጥጥር ከፍተኛ ትርጓሜ መያዙ ሲታሰብ የህብረቱ ውሳኔ በናይጀሪያ ዴሞክራሲ ላይ አሳሳቢ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል የታዛቢው ቡድን መሪ ሳንቲያጎ ፊሳስ ገልጸዋል።

ለኛ ዋናው ነገር በምርጫ ዕለት ብቻ በዚያ መገኘት ሳይሆን፣ ለረጅም ጊዜ ማለትም በምርጫው ሂደት ሁሉ በዚያ መቆየት የምንችልበት አሰራር ነው፣ ይህ ግን አልተቻለም። በፀጥታ ጥበቃ የተነሳ ግን ይህንን ተልዕኮ በሌላው የሀገሪቱ ከፊል እንዳደረግነው ማሰማራት አልተቻለም። የአውሮጳ ህብረት በናይጀሪያ ታዛቢ በመላክ ታሪኩ ውስጥ አንዳንድ የራድዮ እና ቴሌቪዥን ስርጭቶችን እና አንዳንድ የህትመት ፕሬስ ውጤቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ የመቆጣጠር ስራ ለማስተዋወቅ ማቀዱን ፊሳስ አክለው አስታውቀዋል። የህብረቱ ታዛቢ ቡድን ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሀና ሮባትስ ይኸው ዕቅድ ስለምርጫው የሚቀርበውን ዘገባ ሚዛናዊነት ያረጋግጣል።

« 14 የኤሌክትሮኒክስ እና የሕትመት መገናኛ ዘዴዎችን ስራ እንከታተላለን፣ ለተለያዩት ፓርቲዎች የሚሰጡትን ሽፋን እና ሚዛናዊነቱን እንመለከታለን። ዕቅዱ በሀገሪቱ የሚገኙ የግል እና የመንግሥት ሚዲያዎችን ያጠቃልላል። »

የናይጀሪያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩ ማጣሪያቸውን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አጠናቀዋል። ግን አጠቃላዩን ምርጫ እና የሀገሪቱን ዴሞክራሲ አደጋ ላይ ሊጥል የቃጣ ስጋት ታይቶበት እንደነበር ሳንቲያጎ ፋሳሲ አስረድተዋል።

« የምርጫው ሥርዓት ችግር አለበት። ፓርቲዎች ማንን በዕጩነት በሚያቀርቡበት ሁኔታ ላይ ሙሉ ቁጥጥር አላቸው። ስለዚህ በነፃ መካሄዱን ማጣራት አይቻልም። ሕጉ የተወሰነ መመሪያ ብቻ ስለሚሰጥ ተግባራዊ የማስደረግ አቅም የለውም። ይህም መራጮች ን ምርጫ ይገድባል። ምርጫውንም ያዳክማል።

ህብረቱ ከ2011 ምርጫ በኋላ ይህንን በተመለከተ 50 የማሻሻያ ሀሳቦችን ቢያቀርብም፣ እስካሁን አንዱ ብቻ የመረጃ አቀራረብን የተመለከተው ብቻ ነው በተግባር የተተረጎመው። ስለዚህ ባለፈው ምርጫ የታዩ ችግሮች ዘሁንም ይኖራሉ። ጠንካራ ፉክክር ይኖርበታል የሚባለው የናይጀሪያ ምርጫ ነፃ ትክክለኛ እና ፍትሓዊ የመካሄዱ ሁኔታ ብዙዎችን እንዳሳሰበ ይገኛል።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic