የናይጀሪያ መንግስት ፀረ ሽብር ርምጃ | አፍሪቃ | DW | 02.11.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የናይጀሪያ መንግስት ፀረ ሽብር ርምጃ

ባለፈዉ እሁድ ናይጀሪያ ዉስጥ ቦኮ ሃራም ሰሜን ካዱና በሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን ላይ ያደረሰዉ ጥቃት በአካባቢዉ የአመፅ ተግባር እልባት የሌለዉ አስመስሎታል የተባለ ነዉ።

የሽብር ተግባርን ለመግታት መንግስት የሚወስደዉ ርምጃም አዎንታዊ ዉጤት ከማምጣት በተቃራኒዉ ችግሩን እንዳያባብስ ስጋት እንዳለዉ ዓለም ዓቀፉ የመብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽል አመልክቷል።

ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ በሰሜናዊ ካዱና ሙስሊም ናይጀሪያዉያን የኢድ አልአድሀን በዓል ክርስቲያን ጓደኞቻቸዉን ጋብዘዉ በጋራ ዕለቱን በደስታና በሰላም እንዳከበሩ ነዉ ኢማም ሙሐመድ ኑራይኒ አሻፋ የሚናገሩት፤

«ከብት አርደን፤ ልጆችም ሆኑ ሁላችንም በአንድ ላይ በላን ጠጣን፤ ከሙስሊሞች ጋ ብቻ ሳይሆን ከክርስቲያን ጓደኞቻችንም ጋ ነዉ። አብረዉን እንዲያከብሩም ለክርስቲያን ጓደኞቻችን ምግብ ወስደናል።»

ከአንድ በኋላ እሁድ ዕለት ግን የተፈጠረዉ ሌላ ነዉ፤ እዚያዉ በሚገኝ ቤተክርስቲያን አንድ ተጠርጣሪ የጣለዉ ቦምብ ቢያንስ የስምንት ሰዎችን ህይወት አጠፋ። ከመቶ ከሚበልጡ ደግሞ ጉዳት ደረሰባቸዉ። የጥቃቱ አቀነባባሪም ቦኮ ሃራም የተሰኘዉ እስላማዊ ጽንፈኛ ቡድን ነዉ። ቡድኑ በሰሜን ናይጀሪያ በሚገኙ ቤተክርስያናት ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት በማድረስ ይታወቃል።

ይህም በሃይማኖቶች መካከል የሚካሄደዉን ዉይይት ሊያሰናክል እንደሚችል ታዛቢዎች እየገለፁ ነዉ። ምክንያቱም ጥቃቱ ሙስሊምን ከክርስቲያን የሚያፋጥጥ ርምጃ መሆኑን የሚያሳየዉ፤ ከእሁድ ጥቃት በኋላ ደማቸዉ የፈላ ክርስቲያኖች ሶስት ሰዎች መግደላቸ እንደሆነም ተጠቅሷል። ግጭቱን ለማብረድም ሆነ ጥቃቱን ለመከላከል ከመንግስት ወገን የሚወሰደዉ ርምጃም ችግር እያስከተ እንደሆነ ነዉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ባልደረባ ሉሲ ፍሪማን የሚያስረዱት፤

«ህዝቡ በዚህ መካከል የተቸገረዉ በሃይማኖታዊዉ ምክንያት ብቻ አይደለም። በአንድ ወገን ታጣቂ ቡድን ቦኮ ሃራም አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ይፈፅማል፤ በሌላዉ በኩል ደግሞ የጦር ኃይሉ አለ። ከዚህ ወገን የሚሰነዘረዉ አፀፋም በቦኮ ሃራም እጅ የሚሰቃየዉ ኅብረተሰብ ላይ የከፋ ስቃት የሚያስከትል ነዉ።»

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የናይጀሪያን አመፅ አስመልክቶ ትናንት ይፋ ባደረገዉ ዘገባ፤ በርካታ ሰዎች ሳይከሰሱ እንደሚታሰሩ አመልክቷል። ካለ ፍትህ ሰዎች እንደሚገደሉም ጠቅሷል። የቀድሞ የጦር ኃይል አባል የሆኑት ያህያ ሺንካም ጥፋተኞችን ችላ ይላል ሲሉ መንግስትን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ምክንያቱም ችላ የተባሉ ስለሚመስላቸዉ የተበሳጩ ክርስቲያኖች ጥፋተኛ ያሏቸዉ ሙስሊሞች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ።

«ምናልባት መንግስትም ሆኑ ፖለቲከኞች የሰሜን ናይጀሪያ እንዳይረጋጋ እጃቸዉን አስገብተዋል ወይ በሚል ሰዎች ጥያቄ ያቀርባሉ፤ ሰሜን ናይጀሪያ ዉስጥ ክርስቲያንና ሙስሊሙ የማይተባበር ከሆነ እነሱ የሚፈልጉትን ማድረግ ይችሉ ይሆናል።»

እሳቸዉ እንደሚሉትም በሰሜን ናይጀሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች ስጋት ስለሚያድርባቸዉ ከለላ ለማግኘት ከፕሬዝደንት ጉድላክ ጆነተን ጎን ለመቆም ይገደዳሉ። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ ያመለከተዉ ታዲያ በፀረ ሽብር ዘመቻ ስም የመንግስት ኃይሎች ያልታጠቁና የማያሰጉ ያላቸዉን ሰላማዊ ሰዎች እንደሚያንገላቱ፤ ያም በስጋት በሚተያዩት ወገኖች መካከል ይበልጥ ችግሩን ማባባሱን ነዉ። ከዚህ በመሳትም ድርጅቱ ማባሪያ ያጣዉን የሽብር ጥቃትም ሆነ የአፀፋዉን ትርጉም የለሽ አመፅ ርምጃ ሲል ፈርጆታል። እማኞችን ዋቢ ያደረገዉ ዘገባ የዘፈቀደ እስራትን፤ ግድያን በግድ አካባቢን መልቀቅን እንዲሁም ለሞት እስኪዳረጉ ድረስ ሰዎችን መደብደብ ሁሉ በመንግስት ኃይሎች እንደሚፈፀም አመልክቷል። ይህም ቦኮ ሃራም ከናይጀሪያ መንግስት የቁጥጥር አቅም በላይ ሆኗል ወይ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱን ጠቁሟል።

ፊሊፕ ሳንድነር

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic