የናይጀሪያው የቦምብ ጥቃት | አፍሪቃ | DW | 14.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የናይጀሪያው የቦምብ ጥቃት

የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን በአገሪቱ መሰል ጥቃቶችን የሚያደርሰው ቦኮሃራም በጥቃቱ ተጠርጣሪ መሆኑን ተናግረዋል ። አደጋው የደረሰበትን አካባቢ የጎበኙት ፕሬዝዳንቱ ሃገሪቱን ወደ ኋላ ለመጎተት የሚፈልጉ ባሏቸው ኃይሎች ተቀነባበረ ያሉትን ጥቃት አውግዘዋል ።

በናይጄሪያ መዲና አቡጃ አቅራቢያ በሚገኘው የንያንያ ሰፈር ዛሬ በአንድ የአውቶቡስ መናኸሪያ በተጣሉ ሁለት ጥቃቶች ቢያንስ 71 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ124 በላይ መቁሰላቸውን ፖሊስ አስታወቀ። ቦምቡ በፈነዳበት ጊዜ፣ ወደ ስራ ቦታቸው ለመሄድ አውቶቡስ ይጠብቁ የነበሩ በርካቶች በዚያ ይገኙ እንደነበር ፖሊስ አክሎ አስታውቋል። እንደ አይን እማኞች ግምት፣ የሟቾቹ ቁጥር 200 ይደርሳል። የፀጥታ ኃይላት ጥቃቱን በማጣራት ላይ ይገኛሉ። በሀገሪቱ የሚገኘው አክራሪ የሙሥሊም ቡድን ቦኮ ሀራም ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ በተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት ጥሏል። ባለፈው እሁድ ብቻ የቦኮ ሀራም ሚሊሺያዎች በሰሜን ናይጄሪያ በጣሉት ጥቃት ቢያንስ 60 ሰዎች ሲገደሉ ፣በርካቶች ቆስለዋል። ቦኮ ሀራም እአአ ከ 2009 ጀምሮ በብዛት ሙሥሊሞች በሚኖሩበት ሰሜናዊ ናይጄሪያ እሥላማዊ መንግሥት ለማቋቋም በመዋጋት ላይ ይገኛል። የተጣለውን አደጋ አስመልክቶ በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ የሚገኙት ያካባቢው ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንደራሴ አህመድ ዛናህ ዛሬ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት፤ የዛሬው ጥቃት በ2015 በሀገሪቱ በሚካሄደው ምርጫ ላይ አሉታዊ ሚና ይኖረዋል።

«የጥቃቱ ዓይነት ተቀይሯል። አደጋው የሚጣልባቸው አካባቢዎች ጨምረዋል። በሰሜን ምስራቅ ወይም በምዕራብ ወይም በማዕከላይ ናይጄሪያ ብቻ አይደለም። ይህ የሚያመላክተው ለአስመራጩ ኮሚሽን በነዚህ አካባቢዎች ምርጫ ማካሄድ ከባድ እንደሚሆንበት ነው። ምንም እንኳን የምርጫ ሊቀመንበሩ ምርጫው እንዲካሄድ ቢያዝም፤ እርግጠኛ ነኝ ፤ አንዳንድ በምርጫው ሂደት ላይ በበጎ ፈቃደኝነት የሚሰሩ ሰዎች ወደነዚህ አካባቢዎች በመሄድ ለምርጫ ብለው በፍፁም ሕይወታቸውን አይሠዉም። ምርጫም አያካሂዱም። »

እስከ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ድረስ ለጥቃቱ ሃላፊነቱን የወሰደ ወገን የለም ። ሆኖም የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን በአገሪቱ መሰል ጥቃቶችን የሚያደርሰው ቦኮሃራም በጥቃቱ ተጠርጣሪ መሆኑን ተናግረዋል ። አደጋው የደረሰበትን አካባቢ የጎበኙት ፕሬዝዳንቱ ሃገሪቱን ወደ ኋላ ለመጎተት የሚፈልጉ ባሏቸው ኃይሎች ተቀነባበረ ያሉትን ጥቃት አውግዘዋል ።ጥቃቱ እየተጣራ ሲሆን የደህንነት አዋቂዎች ግን ጥቃቱ የደረሰው መኪና ውስጥ በተጠመደ ፈንጂ ሳይሆን እንዳልቀረ ገምተዋል ።

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic