የናይጀሪያው ውጥረት መባባስ | አፍሪቃ | DW | 04.01.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የናይጀሪያው ውጥረት መባባስ

ናይጀሪያ ውስጥ የሚገኝ እስላም ፅንፈኛ ቡድን ነው። የዚህ ታጣቂ ቡድን ስያሜ ቃል በቃል ሲተረጎም «የምዕራቡ ስልጣኔ አያስፈልገንም» እንደማለት ነው።

ቤተሰባቸውን በቦንቡ ጥቃት ያጡ ናይጀሪያዊያን በከፊል

ቤተሰባቸውን በቦንቡ ጥቃት ያጡ ናይጀሪያዊያን በከፊል

ከ3000በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች ለዘመናት ሲነገርባት የኖረች ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር ናት። ከ350 በላይ የተለያዩ ጎሳዎችንም አሰባጥራ ይዛለች፤ ናይጄሪያ። ቁጥሩ ብዙም ባልተበላለጠ ሁኔታ ደግሞ የእስልምና እና የክርስትና እምነት ተከታዮች ለምዕተ-ዓመታት በዚህችው ሀገር በአንድነት ኖረዋል። እንደ አብዛኛው የአፍሪቃ አህጉር ፖለቲከኞች ሲያሻቸው ቦይ የሚቀይዱለት ሄድ መለስ የሚል ሀይማኖታዊ ግጭትም ናይጄሪያን አላጣትም። በቅርቡ የገና በዓል ሥርዓተ-ቅዳሴ  በተያዘበት ዕለት የተከሰተው ግን ናይጀሪያ ውስጥ ከምን ጊዜው የባሰ ውጥረት አንግሷል። ራሱን ቦኮሐራም ብሎ የሰየመ እስላም ፅንፈኛ ቡድን በወሰዳቸው ተከታታይ የቦንብ ጥቃቶች በርካቶች ለህልፈት ተዳርገዋል።

«ሥርዓተ-ቅዳሴ በመካሄድ ላይ እንዳለ፤ ድንገት የተኩስ ልውውጥ ሰማን። ወደውጭ ፈትለክ ብለን በመውጣት በአጥር ተንጠላጥለን ወረድን፤ ወደ ውጭ እንደወጣሁ፤ ቦንብ ፈነዳ። አለፍ ብሎም ሁለተኛው ተደገመ።» 

በፍንዳታዎቹ ከ40 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል። በርካታ ሙስሊም ናይጀሪያውያንን ጨምሮ ዓለም የጥቃቱ ፈፃሚዎችን እኩዮች ሲልም ኮንኗል። ጥቃቱን ተከትሎ የናይጀሪያ ባለስልጣናት ክርስቲያኖች የበቀል ርምጃ እንዳይወስዱ በማስጠንቀቅ ቦኮሀራም ላይ ሰፊ የጥቃት ዘመቻ እንደሚከፍቱ አሳስበዋል።  በአንፃሩ ግን ጥቃቱን ሃይማኖታዊ ግጭት አድርገው የወሰዱትም ቀላል የሚባሉ አይደሉም። የናይጀሪያ ክርስቲያኖች ማኅበር ፕሬዚዳንት ፓስተር  አዮ ኦሪትሴጃፋሮ በበኩላቸው መሰል ጥቃት እንዳይደገም ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በቦንቡ ያጓናቸው መኪኖች ጋይተው እንደተጨራመቱ

በቦንቡ ያጓናቸው መኪኖች ጋይተ እንደተጨራመቱ

«በመላው ሐገሪቱ የምንገኝ የክርስቲያን ማኅበረሰብ፤  በአባላቶቻችን፣ በቤተ-ክርስቲያናችን እና ንብረታችን ላይ ዳግም መሰል ጥቃት ከተቃጣብን ተመሳሳይ አፀፌታ ከመውሰድ ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖረንም።»

በአንፃሩ  በናይጀሪያ የተከሰተው ግጭት መሰረቱ እምነት አይደለም የሚሉ አስተያየቶች ከየአቅጣጫው ተሰንዝረዋል። በርካታ ተንታኞችም ለግጭቱ ሰበብ ነው የሚሉትን ትንታኔያቸውን ማሰማት ቀጥለዋል።  የዓለም አቀፍ ሲቪል መብቶች ማኅበር የአፍሪቃው ክፍል ሃላፊ ዶክተር ኢማኑኤል ፍራንክሊን ኦቡንዌዜ ለዶቼቬሌ ሲገልፁ፤ ለናይጀሪያ ግጭት ሰበቡ በሀገሪቱ የተንሰራፋው ድህነት ነው በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዶቼቬሌ የሀውሳ ቋንቋ ክፍል ባልደረባው ናይጀሪያዊው ወጣት ጋዜጠኛ ኦስማን ሼሁ በበኩሉ የተለየ አመለካከት ነው ያለው። «የግጭቱ መንስኤ ሀይማኖታዊ ነው ወይስ ድህነት?»  ስል ላቀረብኩለት ጥያቄ ሁለቱም አይደሉም ሲል በመመለስ ትንታኔውን እንደሚከተለው አስቀምጧል፥

«ናይጀሪያ በወታደራዊው አገዛዝ ዘመንም እኮ በድህነት ማቃለች፤ ታዲያ ያኔ  ድህነቱ ለምን ግጭት አላጫረም? ግጭቱ ለምን አሁን ተከሰተ? ናይጀሪያ ከቅኝ አገዛዝ ዘመን ከተላቀቀች ከ50 ዓመታት ግድም በኋላ  ቦኮሐራም ለምን አሁን ተነሳ? የትኛውም ቆንስላ አለያም መስሪያ ቤት ብትሄድ ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች በአንድነት ያለምንም ችግር ሲሰሩ ታያለህ። እኔ ግጭቱ ከሀይማኖታዊ ሰበብ ይልቅ ፖለቲካዊ  ይዘት አለው ባይ ነኝ ። »

ናይጀሪያ ውስጥ በርካታ ክርስቲያኖች በደቡባዊ የሐገሪቱ ክፍል ሲኖሩ፤ አብላጫ ሙስሊሞች ደግሞ በሰሜን ናይጀሪያ እንደሚኖሩ ይነገራል። በናይጀሪያ ከፍተኛውን የመንግስት ስልጣን የያዙት የሁለቱም እምነት ተከታዮች ናቸው። በእርግጥ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን  ክርስቲያን ቢሆኑም በርካታ ሙስሊሞችም በከፍተኛ ስልጣን ላይ ይገኛሉ ሲል ኦስማን አክሎ ገልጿል። ለአብነት ያህል ሲያብራራም፤ የመከላከያ ሚንስትሩ፣ የፌዴራል ፖሊስ ሹሙ እንዲሁም  የአየር ሀይል አዛዡ ሙስሊሞች መሆናቸውን ጠቅሷል። ኦስማን እምነቱ ሙስሊም መሆኑን ገልጹ ቦኮሐራም የተሰኘው እስላም ፅንፈኛ ቡድን በተግባሩ እኛ ሙስሊሞችን አይወክልም፤ በርካታ ሙስሊም ናይጄሪያውያንም ይህንኑ ቡድን አውግዘዋል ሲል አክሏል። በናይጀሪያ ከፍተኛ የሙስሊም ሃይማኖታዊ መሪው፤ የሶኮቶው ሱልጣን ሙሐመድ ሳድ አቡባካር ለናይጄሪያውያን ያስተላለፉት መልዕክት በራሱ የኡስማንን አስተያየት የሚያጠናክር ይመስላል፥

 «ለመላው ናይጀሪያውያን ማረጋገጥ የምፈልገው፤ በሙስሊም እና ክርስቲያን፤ በእስልምና እና ክርስትና እምነት መካከል የተከሰተ ግጭት እንዳልሆነ ነው።»

ናይጀሪያ ውስጥ አቁስለኞቹ እየተረዱ

ናይጀሪያ ውስጥ አቁስለኞቹ እየተረዱ

በዶቼ ቬሌ የሀውሳ ክፍል ባልደረባ የሆነውና እና በክፍሉ ከ35 ዓመታት በላይ ያገለገለው ሌላኛው  ናይጄሪያዊ አንጋፋ ጋዜጠኛ ኦማር አሊዩ በበኩሉ በናይጄሪያ ለዘመናት የእምነት እና የጎሳ ልዩነት ከፍተኛ ችግር ሆኖ አያውቅም ብሏል። ኦማር እምነቱ ሙስሊም ነው። ሆኖም እንደኦማር ያሉ መሰል የሙስሊም ስሞችን ይዞ ክርስቲያን መሆን አለያም የክርስቲያን ስም ይዞ በሙስሊም ቤተሰቦች ማደግ በናይጄሪያ የተለመደ መሆኑን ናይጄሪያውያን ጋዜጠኞች ገልፀውልኛል። «ይህ በራሱ የተለያየው እምነታችን ኅብር ሆኖ ለመቆየቱ ማስረጃ ነውም» ሲሉ አብራርተውልኛል።  ጋዜጠኛ ኦማር ስለቦኮሐራም ሲያብራራ፤ ቦኮሐራም የተሰኘው ታጣቂ ቡድን በራሱ አነሳሱ እምነትን መሰረት ያደረገ አልነበረም ብሏል። ከትርጓሜው ብንነሳ  እንኳን ይላል ኦማር፤  ቦኮሐራም ማለት «የምዕራቡ ስልጣኔ አያስፈልገንም» እንደማለት ነው ሲል ገልጿል። የናይጀሪያውን የሰሞኑ ግጭት ሰበብ ሀይማኖታዊ አለመሆኑን ሲያብራራልኝ ደግሞ እንዲህ ብሏል፥

«ቦኮሐራም ከመምጣቱ በፊት በርካታ ግጭቶች ነበሩ። ግጭቶቹ መሰረታቸው ሐይማኖት አለያም ሌላ ሊሆን ይችላል። ቦኮሐሐራም በተሳሳተ ጊዜ እና ሂደት የመጣ ድርጅት ነው ማለት ይቻላል። ሆኖም በናይጀሪያ የሚቀሰቀስ ማንኛውም ግጭት መሰረቱ ሐይማኖታዊ ይሁንም ሌላ የሚተረጎመው የሀይማኖት ግጭት ተደርጎ ነው።»   

የናይጄሪያው ግጭት መሰረቱ ሀይማኖት ላለመሆኑ አንዳንዶች ትንታኔያቸውን ሲያጠናቅሩ ቦኮሐራም ካደረሰው ጥቃት በኋላ የተቀሰቀሰውን አዲስ ግጭት ያነሳሉ። በናይጀርያ በጎርጎረሳዉያኑ አዲስ አመት መባቻ በሁለት ቡድኖች መካከል በተነሳ ግጭት ከሃምሳ በላይ ሰዎች መገደላቸዉ  ይታወቃል።  ሁለት የናይጄርያ ቡድኖች በመሪት ይዞታ እንደተጣሉ እና አዲሱ ግጭት  በዕለተ ገና ቦኮሐራም ካደረሰው ጥቃት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለዉ ተዘግቧል። የናይጀሪያው ፕሬዚዳን ጉድላክ ጆናታን ቦኮሐራምን ለመታገል ሁሉም ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አስተላልፈዋል።

«የሁሉም እምነቶች፣ ባህሎች እና  አስተሳሰብ መሪዎች እንዲሁም የወጣቶች እና የሴቶች ቡድኖች አመራር መንግስትን ብሎም ፖለቲከኞችን ለመደገፍ በአንድነት ሊቆሙ ይገባል።»

በናይጀሪያ የተባባሰውን ውጥረት ተከትሎ በሐገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። ሐገሪቱ በሰሜን ምስራቅ ከሌሎች ሀገራት የሚያጎራብታትን ድንበር ለደህንነት በሚል መዝጋቷም ታውቋል። የቦኮሐራም ታጣቂ ቡድን ቃል አቀባይ በበኩላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የናይጄሪያ መንግስት ንፁሐን ሙስሊሞችን ሊያጠቃ ስለሚችል እኛም የአፀፌታ ርምጃ እንወስዳለን ሲሉ መዛታቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። ቦኮሐራም የተሰኘው የናይጀሪያ እስላም ፅንፈኛ ቡድን ከተመሰረተ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ የቡድኑ መስራች ሞሐመድ ዩሱፍ  ከሁለት ዓመት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ እስከአሁንም ድረስ ግልፅ ባልሆነ መልኩ መሞታቸው ይታወቃል።

ቦኮሐራም የተሰኘው የናይጀሪያ እስላም ፅንፈኛ ቡድን በናይጀሪያ ክርስቲያኖች ላይ ያደረሰውን የቦንብ ጥቃት ተከትሎ በሐገሪቱ የሰፈነውን ስጋት አስመልክተን ያስቃኛናችሁ የማኅደረ-ዜና ጥንቅራችን በዚህ ይጠናቀቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic