የኑክሌር ደሕንነት ጉባኤ | ዓለም | DW | 04.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የኑክሌር ደሕንነት ጉባኤ

የጉባኤዉ ዓላማ የኑኬሌር ቦምብ ሥጋትን ለመቀነስ ከነበረ የኑኬሌር ጉዳይ አጥኚ ቤይዛ ኡናል እንደሚሉት ሩሲያ መካፈል፤ አለያም ጉባኤዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መዘጋጀትና መጠራት ነበረበት።በዚሕም ምክንያት ኡናል ጉባኤዉን «የአሜሪካዉያን መድረክ።» ይሉታል።ዓለም አቀፍ አይደለም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:16
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
15:16 ደቂቃ

የኑክሌር ደሕንነት ጉባኤ

ዋሽግተን-ዩናይትድ ስቴትስ ተሰብስበዉ የነበሩት የሐምሳ ሐገራት መሪዎች ዓለምን ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ሥጋት ለማላቀቅ እንደገና ወሰኑ። አርብ።የዓለም መሪዎች ሥለ ኑኩሌር ጦር መሳሪያ ምርት፤ ሥርጭትና ሥጋት፤ ሲነጋገሩ፤ ሥጋቱ የሚቃለልበትን ሥልት ሲቀይሱና ሲወስኑ ይሕ የመጀመሪያቸዉ አይደለም።የመጨረሻቸዉ አይሆንምም።ባሁኑ ጉባኤ ግን ከዓለም ሁለተኛዉን ከፍተኛ የኑክሌር ቦምብ ፤ ቦምቡን ማወንጨፊ ወይም መጣያ መሳሪያ ያከማቸችዉና ቦምቡን መስሪያ ዕዉቀት ያዳበረችዉ ትልቅ ሐገር አልተካፈለችም ።ሩሲያ። የኑኬሌር መርሐ ግብሯን ለማቆም በቅርቡ ቃል የገባቸዉ ስልታዊት ሐገርም አልታገበዘችም።ኢራን።ብዙ ኑክሌር ያላትም፤ ኑኬሌር እንዳይኖራት የወሰነችዉም ሐገራት ባልተወከሉበት ጉባኤ የተባለ፤ የተወሰነዉ ለዓለም ሠላም ይጠቅም ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ዩናይትድ ስቴትስ ሐምሌ 16 1945 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የመጀመሪያዉን የሐይድሮጂን ቦምብ ሥትሞከር የአዉዳሚዉን ቦምብ ጥፋት ምንነት ለዓለም አስታዋወቅች።የያኔዋ ሶቬት ሕብረት ቀጠለች።ብሪታንያ በ1952 አሰለሰች።አራተኛና አምስተኞቹ ፈረንሳይ እና ቻይና ናቸዉ።

ዩናይትድ ስቴትስ ሔሮሺማና ናጋሳኪን በአዉዳሚዉ ቦምብ ካወደመች በኋላ ቦምቡን ይበልጥ ብታሻሻል፤ ቁጥሩን ብትጨምርም ሶቭየት ሕብረትን ከፉክክሩ ማስወጣት አልቻለችም።አብነቱ ድርድር ሆነ። ዩናይትድ ስቴትስ እና ሶቬየት ሕብረት የሥልታዊ ጦር መሳሪያዎች መወሰን (ቅነሳም ይሉታል) ስምምነት SALT 1 ያሉትን ድርድር ጀመሩ።

ሁለቱ ልዕለ ሐያላን መንግሥታት ሕዳር 1969 የጀመሩትን ድርድር በስምምነት ለመደምደም አራት ዓመት ሊሞላዉ ወራት ሲቀሩት ነበር።

ዩናይትድ ስቴትስ ቦምቡን ለሙከራ ካፈነዳችበት ሶቬት ሕብረት እስከሞከረችበት እስከ 1949 ድረስ የፈጀዉ ጊዜ አራት ዓመት ነበር።አዉዳሚዉን ቦምብ ለመታጠቅ የአራት ዓመት ልዩነት የጠየቃቸዉ ሁለቱ

ሐገራት የአዉዳሚዉን ቦምብ ሥጋት የሚቀንስ ዉል ለመፈራረምም የፈጀባቸዉ ጊዜ አራት ዓመት ሊሞላ ትንሽ ነበር የቀረዉ።

ያም ሆኖ የሶቬት ሕብረት ኮሚንስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ሊዮኒድ ብሬዥኔቭ እና የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን ግንቦት አንድ 1972 የተፈራረሙት ሥምምነት ዓለምን ከከፋ ጥፋት ለማዳን ታላቅ እርምጃ ተደርጎ ሲወደስ ነበር።ሥምምነቱ ግንቦት 20 1972 ሲፀድቅ ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን እንዳሉት መንግስታት ለአዉዳሚ ጦር መሳሪዎች የሚያወጡትን ሐብትና ዕዉቀት ለሠላምና ልማት ለማዋል ቃል ገብተዉም ነበር።

«እንደምታዉቁት የኑክሌር ጦር መሳሪያን ለመቀነስ ሶቭየት-እና አሜሪካ ያደረጉት ድርድር ለአንድ ዓመት ቆሞ ነበር።የሁለቱ መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተካፈሉበት ድርድር ከተደረገ በኋላ ግን ድርድሩ መቀጠሉን አስታዉቃለሁ።አሁን የማነበዉ መግለጫ ዋሽግተንና ሞስኮ ዉስጥ በተመሳሳይ ሰዓት የወጣ ነዉ።ዋሽግተን ከቀኑ 6 ሰዓት፤ ሞስኮ ከምሽቱ አንድ ሰዓት።»

መግለጫዉ ሁለቱ መንግሥታት በሥልታዊ ጦር መሳሪያዎች ቅነሳ ላይ ያደረጉት ዉይይትን ካጤኑ በሕዋላ የፀረ-ሚሳዬል-መሳሪያዎችን እንዳይተክሉ የሚያግድ ዉል ለመፈራረም መወሰናቸዉን፤ አዉዳሚ ጦር መሳሪያዎችን ምርትና ሥርጭትን ለመቀነስ የሚረዳ ተጨማሪ ድርድር ለማድረግም መስማማታቸዉን ያትታል።

«ይሕ ሥምምነት ሥለኑክሌር ጦር መሳሪያዎች በሚደረገዉ ድርድር ላይ ተጋርጦ የነበረዉን እንቅፋት የሚያስወግድ ነዉ።ይሕን መግባባት ወደ ተጨባጭ ሥምምነት ለመቀየር ግን ያላሰለሠ ድርድር ያስፈልጋል።ቀደም ብሎ ያነበብኩት መግለጫ የሶቭየትና የአሜሪካ መንግሥታት መሪዎች ከዚያ ግብ ለመድረስ መቁረጣቸዉን ያረጋግጣል።ከተሳካልን መንግሥታት በሙሉ ሐብታቸዉን፤ ሐይላቸዉንና አዉቀታቸዉን ለጦር መሳሪያ ሳይሆን ለሠላማዊ አገልግሎት እንዲያዉሉት ይሕ መግለጫ የመጀመሪያ ዉል ተደርጎ ይዘከራል።»

ሁለቱ

መንግሥታት ከስምምነቱ በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት ለኑኩሌር የሚያወጡትን ገንዘብ ቀንሰዉ ነበር። የመጀመሪያዉ ሥምምነት በተፈረመ በሰባተኛ ዓመቱ ሰኔ 1979 ደግሞ ቪየና-ኦስትሪያ ዉስጥ SALT II ያሉትን ሥምምነትም ተፈራርመዋል።ፊርማ፤ መግለጫ ዘገባዉ ግን ዓለምን ከአጥፊ መሳሪያ ምርትና ሥጋት አላላቀቃትም።

ሁለቱ ልዕለ ሐያላን መንግስታት ራሳቸዉ የመጀመሪያዉን ሥምምነት ከተፈራረሙበት ሁለተኛዉን እስከ ደገሙበት በተቆጠረዉ ሰባት ዓመት ብቻ በነበራቸዉ የኑክሌር ቦምብ ላይ 12 ሺሕ ጨምረዋል። እስከመጀመሪያዉ ሥምምነት ድረስ የማይታወቁ አዳዲስ ሚሳዬሎችን በተለይ ባንድ ጊዜ ከአንድ በላይ የኑክሌር ቦምብ ማወንጨፍ የሚችሉ ሚሳዬሎችን አምርተዋል።

ሶቭየት ሕብረት ከኩባ እስከ ምሥራቅ አዉሮጳ ባሉ ሐገራት፤ ዩናይትድ ስቴትስ ከቱርክ እስከ ጀርመን፤ ከቬልጂግ እስከ ኔዘርላንድስ፤ እስከ ኢጣሊያ የኑክሌር ቦምብና ኑክሌር ተሸካሚ ሚሳዬል ያከማቹት በዚያዉ ዘመን ነዉ።

የሶቬት ሕብረት መበታተን የዩንያትድ ስቴትስና የተባባሪዎችዋን አሸናፊነት ያረጋገጠ፤ «ቀዝቃዛ» የሚባለዉ ጦርነት ማብቃቱን ያበሠረ መሆኑ በርግጥ አያጠያይቅም።ዓለም ግን ሠላም አይደለችም።የአዉዳሚ ጦር መሳሪያ ሥጋትም ናረ እንጂ አልቀነሰም።ሕንድ፤ ፓኪስታን የኑክሌር ቦምብ የታጠቁት፤ እስራኤልና ሰሜን ኮሪያ መታጠቃቸዉ የአደባባይ ሚስጥርነቱ የጎላዉ ዓለም ለጦርነት፤ ለጦር መሳሪያና ለወታደር የሚያወጣዉን ገንዘብ፤ እዉቀትና ጊዜ ቀንሶ ለልማትና ሠላም እንደሚያዉለዉ ቃል ከተገባለት ከ20 ዓመታት በኋላ ነዉ።ዛሬም ባሰ እንጂ አልቀነስም።ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ዓለም ዛሬም ለጦር መሳሪያ የሚያዉለዉ ገንዘብና ጊዜ ለጤና ከሚያዉለዉ በእጥፍ ይበልጣል።

ቻተም ሐዉስ የተሰኘዉ የብሪታንያ አጥኚ ተቋም የኑክሌር ጦር መሳሪያ ጉዳይ አጥኚ ቤይዛ ኡናል እንደሚሉት አዉዳሚ ጦር መሳሪያ ለመታጠቅ የሚደረገዉ እሽቅድምድም በቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን ከነበረዉ የከፋ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ አዉዳሚዉ ጦር መሳሪያ ለዓለም እንዳስተዋወቀች ሁሉ፤ የጦር መሳሪያን ለመቀነስ እንደራደር የሚለዉን ሐሳብ ሥትገፋ የነበረችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ነበረች።

ይሑንና በ1986 የያኔዋ ሶቭየት ሕብረት መሪ ሚካኤል ጎርቫቾቭ ሁለቱ ሐገራት ያላቸዉን የኑኬሌር መጠን 50 በመቶ እንዲቀንሱ ሐሳብ አቅርበዉ ነበር።ፕሬዝደንት ሮናልድ ሬጋን እንቢኝ አሉ።ድርድሩ እንዲደረግ ስትገፋ የነበረችዉ ዩናይትድ ስቴትስ እንደገና እንቢኝ አለኝ።ብዙ ጦር መሳሪያ በማከማቸት፤ በመሸጥና መስጠትም ዩናይትድ ስቴትስን የሚያክል የለም።

በዩናይትድ ስቴትስ ጎትጓችነት 1970ዎቹ የተደረጉትን የሥልታዊ ጦር መሳሪያ ቅነሳ ስምምነቶች ያፈረሰችዉም የፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽዋ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።ደግሞ በተቃራኒዉ አሁን የኑክሌር ደሕንነት ጉባኤ የተባለዉን ሐሳብ በ2010 ያቀረበችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ።

በዋሽግተኑ ጉባኤ የተካፈሉት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦሎንድ እንዳሉት ፕሬዝደንት ኦባማ በተለይ የኢራንን የኑክሌር መርሐ ግብር ለማስቆም ያደረጉት ጥረት ለዉጤት መብቃቱ ታላቅ ድል ነዉ።

«እዚያ ለመድረስ አስቸጋሪ እና ከባድ ድርድር መደረግ፤ ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳታመርት ባራክ ኦባማ እና ፈረንሳይም ጣልቃ መግባት ነበረባቸዉ።ይሕ የኒክሌር ደሕንነት ጉባኤም፤ አደገኛ አሸባሪዎች ለኑክሌር ተቋማት ቅርበት እንዳይኖራቸዉ፤ ለሐገራት ብቻ ሳይሆን ለመላዉ አለም አደገኛ የሆኑ ጥፋት የሚያደርሱ ንጥረ-ነገሮችን እንዳያገኙ ለማድረግ መንግሥታት በሙሉ በንቃት እንዲጠብቁ ለማድረግ ጠቃሚ ነዉ።»

ኦባማ ያስጀመሩት ጉባኤ ዘንድሮ ሲደረግ አራተኛዉ ነዉ።ጉባኤዉ ከተጀመረበት እስካሁን በነበረዉ ጊዜ ብዙ መንግሥታት የኑክሌር ተቋሞቻቸዉ አሸባሪዎች እጅ እንዳይገባ በንቃት ማስጠበቃቸዉን፤ መርዛማ ቦምቦችን ለመስራት የሚያስችሉ ንጥረ ነገሮችን ማጥፋት ወይም አስተማማኝ ወደሆኑ ቦታዎች ማዛወራቸዉን አስታዉቀዋል።ይሁንና ፕሬዝደንት ኦባማ ራሳቸዉ እንዳሉት ዓለም ዛሬም ለኑኬሌር ጥፋት እንደተጋለጠች ነዉ።

«በመላዉ ዓለም በመቶ የሚቆጠሩ ወታደራዊ ተቋማት እና ሠፈሮች ሁለት ሺሕ ያሕል የኑክሌር ቁሳቁሶች አሉ።እነዚሕ ሁሉም ተገቢዉ ጥበቃ አይደረግላቸዉም።አንዲት ቱፋሕ የምታክል በጣም ትንሽ ፕላቱኒየም በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የዋሐንን መግደልና ማቁሰል ትችላለች።ለብዙ ዓመታት የማይወገድ ዓለም አቀፋዊ ሰብአዊ፤ፖለቲካዊ፤ ኤኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ጥፋት ታደርሳለች።»

የሶሪያ መንግሥት ኬሚካዊ ጦር መሳሪያዎቹን እንዲያስረክብ የተደረገዉ መሳሪያዎቹ ከመንግሥት አልፈዉ መንግሥትን የሚወጉ አማፂያን እና አሸባሪዎች እጅ ይገባል በሚል ሥጋት ነዉ።ኢራን የኒኩሌር መርሐ-ግብሯን እንድታቋርጥ አስራ-አምስት ዓመታት የፈጀዉ የዛቻ፤ የማዕቀብ፤ ሳይንቲስቶችን የማገት፤ ማስገደል ዘመቻ፤ ድርድርም አዉዳሚዉ ጦር መሳሪያ ከቴሕራን መሪዎች አልፎ ሒዝቡላሕን በመሳሰሉ ቡድናት እጅ እንዳይገባ ነዉ።

ኢራንና ሶሪያ የኑኬሌር ወይም የኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ንጥረ ነገሮችን አስረከቡ ወይም ማምረት አቆሙ ማለት ግን አሸባሪዎች የሚርመሰመሱበት መካከለኛዉ ምሥራቅ ሚሊዮኖችን ከሚፈጀዉ ጦር መሳሪያ ነፃ ነዉ ማለት አይደለም።

ፕሬዝደንት ኦቦማ የዋሽግተኑን ጉባኤ ሲከፍቱ እንዳሉት መላዉ ደቡባዊ አሜሪካ ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ነፃ ናት።ሠሜን አሜሪካስ? ፖላንድ ኦባማ እንዳሉት፤ ቃል በገባችዉ መሠረት ያላትን መርዛማ ንጥረ ነገር በቅርቡ ካጠፋች ወይም ካስረከበች ማዕከላዊ አዉሮጳ ከኑክሌር ሥጋት ትላቀቃለች።ይሁንና የብሪታንያ፤ የፈረንሳይ፤ የሩሲያ፤ምዕራብ አዉሮጳ የተከማቹት የአሜሪካ የኑክሌር ቦምቦች እያሉ አዉሮጳ ምናልባትም አፍሪቃ ከኑክሌር ሥጋት ነፃነት ልትባል አትችልም።

ፕሬዝደንት ኦባማ ከዋሽግተኑ ጉባኤ ጎን ለጎን የቻይናዉን ፕሬዝደንት ሺ ቺ ፒንግን ሲያነጋግሩ እንዳሉት ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ቦምብ መታጠቅዋ ወይም ለመታጠቅ መጣጣርዋ ለአካባቢዉ ሠላም በጣም አደገኛ ነዉ።

የሰሜን ኮሪያ ኮሚኒስታዊ ሥርዓት ከጠፋ የጦርነት ሥጋት አይኖርም ነዉ መልዕክቱ።ትልቁ ኮሚንስት ሐገር ሶቭየት ሕብረት በጠፋ በአስራ-ስድስተኛ ዓመቱም ዓለም በጦርነት እየዳከረች የአንዲት ትንሽ ሐገር ኮሚንስታዊ ሥርዓት መወገድ በኮሪያ ልሳነ-ምድር በሙሉ ሠላም ያሰፍናል ማለት በርግጥ አጠያያቂ ነዉ።

በዚያ ላይ የቻይና፤ የሕንድ፤ የፓኪስታን ቦምቦች እስያን ለማጥፋት በቂ ናቸዉ።በኦባማ አገላለፅ አንዲት ቱፋሕ የምታክል ፕሉቱኒየም መቶ ሺዎችን ከፈጀ ሰሜን አሜሪካ፤ አዉሮጳ፤መካከለኛዉ ምሥራቅ እና እስያ የተከማቸዉ ቦምብ ከአፍሪቃ እስከ ደቡብ አሜሪካ፤ ከአዉሮጳ እስከ አዉስትሬሊያ፤ ከሰሜን አሜሪካ እስያ ድፍን ዓለም ለማጥፋት ከበቂ በላይ ነዉ።

የዋሽግተን ጉባኤተኞችን በጣም ያሳሰበዉ የአዉዳሚዉ ጦር መሳሪያ መመረት ሳይሆን እንደ ኢራን ወይም ሰሜን ኮሪያ ያሉ የምዕራባዉያን ጠላት ግን ደካማ መንግሥታት እና የአሸባሪ ቡድናት መኖር ነዉ።

«የኑኬሌር ሽብር አደጋ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።በተባበረ ጥረታችን ምክንያት እስካሁን ድረስ ግን የኑክሌር ቦምብ ወይም ከራዲዮ አክቲቭ የተሠራ ቁሻሻ ቦምብ ማግኘት ወይም ማምረት የቻለ አንድም አሸባሪ ቡድን የለም።ይሁንና አልቃኢዳ የኑክሌር ቁሳቁሶችን ለማግኘት ሲጥር እንደነበር እናዉቃለን።በፓሪሱና በብራስልሱ ጥቃት የተካፈሉ ሰዎች ቤልጂግ ኑክሌር ጣቢያ የሚሠራ ከፍተኛ ሥራ አስኪያጅ እንዳለ በቪዲዮ መልዕክታቸዉ ገልጠዋል።ISIL ሶሪያ እና ኢራቅ ዉስጥ ኬሚካዊ ጦር መሳሪያዎችን ረጭቷል።እነዚሕ እብዶች የኑክሌር ቦምብ ወይም ቁሳቁስ ከእጃቸዉ ቢገባ ብዙ ሰዎችን ለመግደል መተኮሳቸዉ አይቀርም።»

የቻተም ሐዉሳ የኑኬሌር ጉዳይ አጥኚም ቤይዛ ኡናልም በዚሕ ይስማማሉ።ይሁንና የዋሽግተኑ ጉባኤ መንግሥታትን ያገለለ፤ በተለይ ከፍተኛ የኑኬሌር ክምችት ያላትን ሩሲያን ያላሳተፈ በመሆኑ ዓለምን ከኑኬሌር ጦር መሳሪያ ሥጋት አያላቅቅም።

አዉዳሚዉን

ጦር መሳሪያ ለመቆጣጠር ከ1960ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ የተደረጉ ድርድሮች፤ ዉይይቶችና ሥምምነቶች በሙሉ የተደረጉት በሞስኮ ተሳትፎና ትብብር ነዉ።ሩሲያ ባሁኑ ጉባኤ ላለመሳተፏ የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሰጠዉ ምክንያት አጭርና ግልፅ ነዉ።«ጉባኤዉ የአሜሪካን ተፅዕኖ ለማጠናከር በአሜሪካኖች የተሰራና የተጠራ ነዉ»-የሚል።

የጉባኤዉ ዓላማ የኑኬሌር ቦምብ ሥጋትን ለመቀነስ ከነበረ የኑኬሌር ጉዳይ አጥኚ ቤይዛ ኡናል እንደሚሉት ሩሲያ መካፈል፤ አለያም ጉባኤዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መዘጋጀትና መጠራት ነበረበት።በዚሕም ምክንያት ኡናል ጉባኤዉን «የአሜሪካዉያን መድረክ።» ይሉታል።ዓለም አቀፍ አይደለም።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች