የኑሮ ውድነት፣ ረሃብና የታዳጊው ዓለም የግብርና ይዞታ | ኤኮኖሚ | DW | 27.08.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የኑሮ ውድነት፣ ረሃብና የታዳጊው ዓለም የግብርና ይዞታ

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በሰፊው እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነት ይበልጡን የታዳጊውን ዓለም ሕዝብ ነው የጎዳው። የምግብ ዋጋ ባለፈው ዓመት ብቻ አርባ በመቶ በሚሆን መጠን በመናር በተለይ የአፍሪቃን አርሶ አደር ከባሰ የሕልውና ፈተና ላይ ሲጥል ዛሬ በዓለም ላይ በረሃብ የሚሰቃየው ሕዝብ ቁጥር አንድ ሚሊያርድ ገደማ ተጠግቷል።

የኑሮ ውድነት የተጫነው የታዳጊው ዓለም አርሶ-አደር

የኑሮ ውድነት የተጫነው የታዳጊው ዓለም አርሶ-አደር

ለአርሶ አደሩ መከራ መባባስ እርግጥ መንስዔው ይህ ብቻ አይደለም። የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላለመቻሉ፤ ረሃብ አስከፊ ገጽታ እየያዘ ለመቀጠሉ ምክንያቶቹ ብዙዎች ናቸው። ችግሩ አሁንም ማነጋገሩን የቀጠለ ጉዳይ ነው። ችግሩን ለመፍታት ከእርሻው ዘርፍ መዋቅራዊ ተሃድሶ እስከ ዓለም ንግድ ፍትሃዊነት ጉዳይ ድረስ ብዙ መሰናክሎችን ማስወገድ ማስፈለጉ ነው የሚነገረው። ዓለምአቀፍ የአደጋና የቀውስ ኮንፈረንስ፤ በአሕጽሮት IDRC የተሰኘ ክፍት የመድረክ ጉባዔ ዛሬ ስዊትዘርላንድ-ዳቮስ ላይ ተከፍቷል። ጉባዔው አተኩሮ ከሚሰነብትባቸው ጉዳዮች ዓበይቱ የምግብ እጥረትና የረሃብ ስደት ናቸው።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት የምግብ ዋጋ ንረት ባለፈው ዓመት ብቻ አርባ በመቶ ገደማ ተጠግቷል። የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት FAO እንደሚገምተው በምግብ ዋጋ ንረት ሳቢያ በረሃብ የሚሰቃየው ሕዝብ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ነው የጨመረው። በዓለምአቀፍ ደረጃ ለረሃብ የተጋለጠው ሕዝብ ቁጥር በጠቅላላው ወደ አንድ ሚሊያርድ ተጠግቷል ማለት ነው። የምግብ ዋጋ መናር፣ ድርቅ፣ ዓመጽና ቤት ሰራሽ ችግር ታክሎበት በወቅቱ በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ብቻ እንኳ ከ 13 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ ነው። አፍሪቃ ጊዜ እየቆጠረ ከሚፈራረቅ ከረሃብ አዙሪት ልትወታ አልቻለችም። ለልማት እጦት፤ እንዲያም ሲል ለምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ አንዱና ዋናው ምክንያት ሆኖ የቀጠለው አግባብ ያለው የመሬት ስሪት አለመከናወኑ ነው።
አርሶ አደሩ የመሬቱ ባለቤት ለመሆን አልበቃም። ምርታማነቱ ጊዜው በጠየቀው መጠን እንዲጨምርና የገበያ ተጠቃሚነቱም እንዲዳብር አልተደረገም። ከ 80 በመቶ የሚበልጠው ሕዝብ በግብርና በሚተዳደርባት በአፍሪቃ የአርሶ አደሩ መደህየት የመላው ሕብረተሰብም መኮስመን ነው። የዛሬው የኑሮ ውድነት ነባሩ ችግር ሳያንስ ለብዙዎች በእንቅርት ላይ ጆር ደግፍ መሆኑ አልቀረም። እንግዲህ በተለይ የችግሩ ሰለባ የሆነው ይሄው ከዕጅ ወደ አፍ ከሆነች ዝቅተኛ ገቢው ሰፊውን ድርሻ ለምግብ ማውጣት ግድ የሆነበት ድሃው የሕብረተሰብ ክፍል ነው። ለምግብ ዋጋ መናር መንስዔዎቹ በርካቶች እንደመሆናችው መጠን እርግጥ የመፍትሄ ሃሣቦች መቅረባቸው ወይም መጠቆማቸውም አልቀረም። ችግሩ ይሁንና ተከታይ ማጣታቸው ላይ ነው።
የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ፋኦ እንደታዘበው በዓለምአቀፉ የምግብ ምርቶች ገበያ ላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሁለት ሂደቶች በተለይ ጎልተው ታይተዋል።

አንደኛው የፍላጎቱ ወይም የፍጆቱ መጨመር ሲሆን ሌላው ደግሞ የአቅርቦቱ እያቆለቆለ መሄድ ነው። ይህም እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ንረትን ነው ያስከተለው።
ለለውጡ መከተል ብዙ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ዋነኞቹ የችግሩ መንስዔዎች ያሉት ደግሞ በአቅርቦቱ አኳያ ነው። የኤነርጂ ዋጋ መናርና የምግብ እርሻ መርት ለምሳሌ በባዮ-ኤነርጂ የተክል እርሻ መገፋት አንዱ ነው። ለምሳሌ የኤነርጂ ተክሎች በሚመረቱበት ቦታ ሩዝም ሆነ በቆሎ መዝራት አይቻልም። በጀርመን የልማት ፖሊሲ ኢንስቲቲዩት DIE የእርሻ ኤኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ሱዛነ ኖይበርት እንደሚሉት ይህ ለውጥ በረጅም ጊዜ የሚያስከትለው ተጽዕኖ መጠን ምን ያህል እንደሚሆን በወቅቱ እንዲህ ብሎ መናገሩ ያዳግታል። የምግብ ፍጆት መጨመሩ ሂደት የሚያስከትለው ችግር ግን ጭብጥና ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው።

“የፍላጎቱ መጨመር ሂደት ያለው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ የተለወጠው የፍጆት ዘይቤ እንጂ የሕዝብ ቁጥር መጨመር አይደለም። ለምሳሌ የሥጋ ፍጆት ያለማቁዋረጥ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው የሚገኘው”

አንዲት ኪሎግራም ሥጋ ለማምረት በብዙ ኪሎ የሚገመት እህልና የከብት ቀለብ ነው የሚፈጀው። ብዙ ውሃና የእርሻ መሬትም ያስፈልጋል። ይህም ለሕዝብ ቀለብ የሚሆነውን የምግብ ተክል ዝቅ የሚያደርግ ነው የሚሆነው። ሱዛነ ኖይበርት እንደሚያስገነዝቡት ስጋን ይበልጥ የመፍጀቱ ሂደት በፍጥነት እያደገ ሲሄድ የሚታይ ነገር ነው። ዛሬ ስጋን በሰፊው የሚፈጁት የበለጸጉት አገሮች ብቻ አይደሉም። ቻይናን የመሳሰሉት በሕዝብ ብዛት ቀደምት የሆኑና በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ አገሮችም ከዚሁ የአመጋገብ ዘይቤ ራሳቸውን እያጣጣሙ መሄዳቸው በግልጽ የሚታይ ነው። ይህ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ እንደሚያባብስ አንድና ሁለት የለውም።

የዚህ ሁሉ ለውጥ መከራ ተሸካሚ በአፍሪቃ፣ በላቲን አሜሪካና በእሢያ የሚኖረው ብዙሃኑ የታዳጊው ዓለም ሕዝብ ሲሆን በተለይ የአነስተኛው ገበሬ መከራ እጥፍ ድርብ እየሆነ በመሄድ ላይ ነው። በአንድ በኩል ራሱ ከሚያመርተው ውጭ ምግብ የመግዛት አቅም የለውም። በሌላም Food First “ምግብ በቅድሚያ” በመባል የሚታወቀው ለምግብ መብት የሚታገል የመረጃና የተግባር ሕብረት ድርጅት ባልደረባ አርሚን ፓሽ እንደሚሉት ገበሬው በወቅቱ የዋጋ ንረትም ተጠቃሚ ወይም አትራፊ ሊሆን አልቻለም። በመሆኑም አነስተኛውን ገበሬ በአገሩ መርዳቱና ማራመዱ የጊዜው አጣዳፊ ተግባር ነው።

“እነዚህ ገበሬዎች ማምረትና ምርታቸውን አግባብ ባለው ዋጋ መሸጥ እንዲችሉ ሁኔታው መመቻችት ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ መዋቅራዊ ለውጦች የግድ አስፈላጊዎች ናቸው። ለምሳሌ የታላላቅ ባለርስቶችን መሬት ለትናንሽ ገበሬዎች ማከፋፈል፣ የበለጠ መንግሥታዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግና ዘላቂነት ያለው የምርት ዘይቤን ማራመድ”

አርሚን ፓሽ አያይዘው እንደሚያሳስቡት እርግጥ እነዚህን መከናወን የሚኖርባቸውን መዋቅራዊ ለውጦች ለማሳካት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ረዳት ሆነው መቆማቸው ግድ ነው። የፋኦ ባልደረባ ቩልፍ ኪልማንም በእርሻው ዘርፍ በሚደረገው ትብብር ይህንኑ ዓላማው ያደረገ አዲስ ስልት መስፈኑ ጠቃሚ ነው ባይ ናቸው።

“ዓለምአቀፉ የልማት ማሕበረሰብ እነዚህን ሃገራት ጠንከር ባለ መልክ እንደገና መደገፍ ይኖርበታል። የዓለምአቀፉ ትብብር የፊናንስ መጠን እ.ጎ.አ. ከ 1980 እስከ 2006 ዓ.ም. ከ 17 ወደ 3 በመቶ ነው ያቆለቆለው። አንድ ዕርምጃ መከተል አለበት ማለት ነው”

በዕውነትም የታዳጊው ዓለም አነስተኛ ገበሬ የአካባቢ ደህንነትን የጠበቀ የእርሻ ዘይቤን እንዲያዳብር በገንዘብ መርዳት የሚቻለው ይሄው ዕርምጃ መከተል ሲችል ነው። ገበሬው በሚነራል ማዳበሪያ ፈንታ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም ከቤንዚን ዋጋ ተጽዕኖ ሊላቀቅ ይችላል። የልማት ዕርዳታው ዓላማ ከዚህ በተጨማሪም ለአነስተኛው ገበሬ የእርሻ ልማት ዕውቀትን ወይም ዘዴን ማስተላለፍና የመሸጥ ዕድሉ እንዲጨምር ማድረግም ነው። ሆኖም ሱዛነ ኖይበርት እንደሚሉት የበለጸገው ዓለም ሚና በልማት ዕርዳታ ብቻ ሊወሰን አይገባውም።

“ከልማት ትብብሩ ውጭ የዓለም ንግድ ግዴታዎች ፍትሃዊ መሆን አለባቸው ብዬ አስባለሁ። ከዚያ በኋላ ነው የልማት ዕርዳታው ፍሬያማ ውጤት ሊያስከትል የሚችለው”

ምክንያቱም በወቅቱ በእርሻው ዘርፍ የታዳጊ አገሮችን የገበያ ተሳትፎ የሚወስኑት የዓለም ንግድ ግዴታዎች የድሆቹን ጥቅም የሚያስከብሩ ሆነው አይገኙም። ትልቁ ፍትህ-ዓልባነት ጎልቶ የሚታየውም በዚሁ የዓለም ንግድ አወቃቀር ላይ ነው።

“ታዳጊ አገሮች በአንድ በኩል ከ 80ኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ አንስቶ ገበዮቻቸውን ለውጭ ምርት እንዲከፍቱ ሲገፉ ነው የቆዩት። በሌላ በኩል በበለጸጉት አገሮች በአሜሪካና በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ የእርሻው ልማት፤ በተለይም የውጭ ንግዱ በመንግሥት ይደጎማል። ገበሬው ለተትረፈረፈ ምርት ድጎማ ያገኛል ማለት ነው”

ይሄው የእርሻ ድጎማና ሰሜኑ ዓለም በታዳጊ አገሮች ምርት ላይ የደነቀረው የገበያ መሰናክል የደቡቡ ዓለም ገበዮች በበለጸገው ሰሜን የምግብ ምርቶች እንዲጥለቀለቅ ነው ያደረገው። በዚህም ለታዳጊው ዓለም አነስተኛ ገበሬ የተረፈው ከራሱ ገበዮች መፈንቀሉ ነው። ታዳጊ አገሮች ከሰባት ዓመታት በፊት ዶሃ ላይ በተካሄደ የምጣኔ-ሐብትና የንግድ ሚኒስትሮች ስብሰባ የበለጸጉት መንግሥታት የእርሻ ድጎማቸውን እንዲቀንሱና ገበዮቻቸውን ለደቡቡ ዓለም የእርሻ ምርቶች እንዲከፍቱ ሲጠይቁ ዓላማቸው ይህን ሆኔታ ለመቀየር ነበር። ይሁንና ከዚያው የተነሣው የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር በተደጋጋሚ መክሽፉ ይታወቃል።
በጅምሩ እንደታለመው ለልማት የሚበጅ ፍትሃዊ ስርዓትን ሊያስከትል አልቻለም። ድርድሩን መልሶ ለማንቀሳቀስ በዚህ ዓመት በቅርቡ ጀኔቫ ላይ የተካሄደው ሙከራም ቢሆን እንደገና ከንቱ ሆኖ ነው የቀረው። የፋኦ ባልደረባ ቩልፍ ኪልማን በተለይም በበለጸጉት መንግሥታት ግትርነት የከሽፈውን ድርድር የቅንነት ድህነት ነው ብለውታል።

“የአፍሪቃን፣ የላቲን አሜሪካንና የእሢያን አገሮች መርዳት መፈለጋችን በዕውነት ከምር ከሆነ በመጀመሪያ በራሳችን የእርሻ ድጎማ ላይ ማተኮር ይኖርብናል። ከዚያ በኋላ ነው እንዴት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንደምናደርግ ማሰብ ያለብን”

የሆነው ሆኖ የበለጸገው ዓለም በአጭር ጊዜ ውስጥ ድጎማውን በግባብ ለመቀነሱ በወቅቱ የሚታይ ምልክት የለም። በዓለም ላይ የረሃብ አደጋ ከመቼውም በላይ እያንዣበበ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሃቁ ይህ መሆኑ በጣም ያሳዝናል። በሌላ በኩል ዛሬ ዳቮስ ላይ የተከፈተው ጉባዔም ችግሮቹን ከማንሳትና እስካሁን የተባሉትን የመፍትሄ ሃሣቦች ከመደርደር ባሻገር የረባ ዕርምጃ ማስገኘቱ ሲበዛ የሚያጠራጥር ነው።