የኑሮ ውድነትና ወጣቶች | ባህል | DW | 19.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የኑሮ ውድነትና ወጣቶች

«ሌላው ቢቀር ጎመን እንኳን በጨው ነስንሼ ለመብላት እየተሳነኝ ነው» ሲል የኑሮ ውድነቱን መቋቋም እንዳቃተው ይገልፃል የኦሮሚያው ወጣት የቤተሰብ አስተዳዳሪ። የአዲስ አበባ ነዋሪው ወጣት የቤተሰብ አስተዳዳሪ ደግሞ «አምስት ለአስራ አንድ የአመጋገብ ስልት» የተለመደ ሆኗል ይለናል። ምን ማለቱ ይሆን?

default

ዘወትር ከታዛው ስር የሶስት ህፃናት ልጆቹ ከርታታ አይናኖች ይጠብቁታል። ወጣት ነው፤ ግን ቋሚ ስራ የለውም። በስራ አስኪያጅነት የትምህርት ዘርፍ በዲፕሎማ የተመረቀ ቢሆንም ቅሉ በቀን ሠራተኝነት በሚያገኘው አነስተኛ ገቢ ኑሮን ለመግፋት ላይ እታች ይታትራል። የኑሮው ውድነት ግን ፈፅሞ አልገፋ ያለው ይመስላል። ነዋሪነቱ ኦሮሚያ ውስጥ ነው።

የኑሮ ውድነቱ የኦሮሚያው ወጣት የቤተሰብ አስተዳዳሪ ላይ ብቻ አይደለም ቀንበሩን የጫነየሚመስለው። በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው ሌላኛው ወጣት የቤተሰብ አስተዳዳሪም ቢሆን ተመርቆ የያዘው ዲግሪ የህይወት አስቸጋሪ ዳገትን ከመቧጠጥ ሊታደገው አልቻለም።

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም በእንግሊዝኛ ምህፃሩ IMF በበኩሉ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ ባወጣው ዘገባ በአፍሪቃ አገራት የኑሮው ውድነት የሸቀጦች ዋጋ ላይ ንረትን ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁሟል። ንረቱ ተከስቶ፤ የኑሮ ክብደቱ ወጣቶችን ወደ አላስፈላጊ የወንጀል ድርጊቶች ሲገፋ ይታያል ሲል የአዲስ አበባው ወጣት ጠቅሷል። ኑሮን እንደአመጣጡ ለመቀበል የተገደዱ ደግሞ በአምስት ለአስራ አንድ አመጋገብ ስልት ይኖራሉ ሲልም አክሏል።

በአብዛኛው የአፍሪቃ አገራት የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መምጣቱን የዓለም አቀፍ ገንዘብ ተቋም ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2005 ዓም ገልጿል። ይሁንና በፈጣን ሁናቴ የሚያድጉ እንደ ኢትዮጵያና ታንዛኒያ ያሉ የተወሰኑ ደሀ አገራት ዕለታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ በእጅጉ እየናረ በመሄድ ላይ መሆኑን ተቋሙ አስጠንቅቋል። አያይዞም በአፍሪቃ ግጭትና የፖለቲካ አለመረጋጋት ለምጣኔ ሀብቱ እድገት አሳሳቢ ነው ብሏል።

ሙሉውን ዝግጅት ከታች የድምፅ ምልክቱን በመጫን ያዳምጡ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሠ

Audios and videos on the topic