የነጻነት ታጋዩ የኢትዮጵያ ታሪክ  | ባህል | DW | 13.02.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የነጻነት ታጋዩ የኢትዮጵያ ታሪክ 

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመጓዝ አዉሮፕላን ዉስጥ ስንገባ፤ ፓይለቱ ጥቁር መሆኑን አይቼ ደነገጥኩ። በህይወቴ ሙሉ ጥቁር ሰው አውሮፕላን ሲነዳ አይቼ ስለማላውቅ ተሸበርኩ፤ ገረመኝ። ጥቁር ሰው እንዴት አውሮፕላን ሊነዳ ይችላል? እያልኩ ደጋግሜ ራሴን ጠየኩ። በኋላ ግን ሲገባኝ፤ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ አገዛዝ አስተሳሰባችንን ጭምር ቀይሮታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:05

ኢትዮጵያ የዘር ሃረግ ግንዴ የተተከለባት ትመስለኛለች

«ደቡብ አፍሪቃ ታላቅ ሃገር ሆና እንድትቀጥል ብሔራዊ እርቃቸዉም ሆነ፤ ኔልሰን ማንዴላ  የከፈሉት የነፃነት ትግል፤ ትልቅ መሰረት ነዉ። ትልቅ አርዓያ ነዉ። እኛ ኢትዮጵያዉያን ከሳቸዉም ሆነ በአጠቃላይ ሃገሪቱ ከሄደችበት ታሪካዊ የፖለቲካ ብሔራዊ እርቅ ብዙ ነገር የምንማረዉ ይኖረናል።»     

የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ነፃ የወጡበት 30ኛ ዓመት መታሰብያን በተመለከተ የሥነ-ቋንቋ ባለሞያዉ ዶክተር ገዛኸኝ ፀጋዉ ከሰጡን አስተያየት የተወሰደን ነዉ። 

አግላዩን የአፓርታይድ ሥርዓት በመታገል ወሳኝ ሚና የተጫወቱት የመጀመርያዉ ጥቁር ደቡብ አፍሪቃዊ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ፤ 27 ዓመት በእስር ቆይተዉ ከእስር ነፃ የሆኑበት 30ኛ ዓመት በዚህ ሳምንት ማክሰኞ የካቲት ሁለት ፤ 2012 ታስቦ ዉሎአል። ሐሙስ ኅዳር 26፤ 2006 ዓም በ 95 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የሰላም ኖቤል ተሸላሚዉ ሎሬት ኔልሰን ማንዴላ፤ ማዲባ በ ሚለዉ የሃገሪዉ ሰዉ የቁልምጫ አጠራርም ይታወቃሉ። በዓለም ሕዝብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅነት የሆኑትና በሃገራቸዉ ይታይ የነበረዉን መድሎን በመጠየፍ የታገሉት ደቡብ አፍሪቃዊዉ ኔልሰን ማንዴላ ነጻነትን ለደቡብ አፍሪቃዉያን ብሎም ለዓለም ሕዝብ ማዉረሳቸዉ ይነገርላቸዋል። ይሁንና ይህ ማንዴላ ያወረሱት የነፃነት ቅርስ በሃገራቸዉ ዉስጥ አለመጠበቁ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አፍሪቃ ሃገራትን ብሎም ዓለም እጅግ እያስቆጣ ነዉ። ሰሞኑን የምዕራባዉያን ጋዜጦች ኔልሰን ማንዴላ ከ 27 ዓመታት እስር በኋላ ነፃ የሆኑበትን 30ኛ ዓመት ሲያስታዉሱ በደቡብ አፍሪቃ እዉን የማዲባ የነፃነት ቅርስ እየተጠበቀ ነዉን? ሲሉ ደማቅር አርስተ ዜና አድርገዉ የተለያዩ ዘገባዎችን አስነብበዋል። 

ኔልሰን ማንዴላ በጃንሆን ዘመነ መንግሥት ከዛሬ ስድሳ ዓመት ገደማ በፊት ለወታደራዊ ስልጠና ኢትዮጵያ መተዉ እንደነበር የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። በ 1962 ዓም የካቲት ወር አራተኛዉ የፓን አፍሪቃ ስብሰባ ማለትም የአፍሪቃ ትብብርን ለማጠናከር አዲስ አበባ ላይ በተዘጋጀዉ ስብሰባ በአህጉሪቱ አሉ ከሚባሉት የነጻነት ታጋዮች መካከል ኦሊቨር ታምቦ፣  ሮበርት ሙጋቤ፣  ኬኔት ካውንዳ እና ኔልሰን ማንዴላ አዲስ አበባ ተገኝተዉ ስብሰባዉን ተካፍለዋል። እነዚህ የዛንጊዜዎቹ የአፍሪቃ ነጻነት ታጋዮች ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ በየአገሮቻቸዉ የፕሬዚዳንት ሆነዉ አገልግለዋል። ኢትዮጵያዉያን ኔልሴን ማንዴላን እንዴት ያስታዉሶዋቸዋል? የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ፤ አፓርታይድን የገረሰሱ በደቡብ አፍሪቃ ስልጣን ሲይዙም ነጭም ሆነ ጥቁር ሁሉም የደቡብ አፍሪቃ ዜጎች የሰብአዊ መብት እንዲጠበቅ ፤ ቀስተ ደመና ሰላም መቆም የሚቻልበትን ኅብረተሰብ ለመገንባት ቆርጠዉ የተነሱና በሃገራቸዉ ለሰላማዊ ፖለቲካዊ ሽግግር ያበቁ ሲሉ ይገልፁዋቸዋል።

ስለ ለዉጥ አራማጆቹ ቼ ጉቬራ ስለ ማኦ እንዲሁም ፊደል ካስትሮ የትግል ታሪክ ማንበባቸዉን ይናገሩ የነበሩት ማዲባ፤  በተለይ ፋሽስት ሞሶሎኒ ያስታጠቃቸዉን የኢጣልያ ወታደሮች፤  በጦር በጋሻ በመከቱት በየኢትዮጵያን አርበኞች ገድል መማረካቸዉን በመጽሐፋቸዉ አስፍረዋል። ሙሶሊኒ የጣልያን ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ጦርነት ሲያደርግ የ17 አመት ልጅ እንደነበሩም ጠቅሰዋል። ድርጊቱ ፋሽስቶችን እስከ መጨረሻው እንድጠላቸው ነበር ያደረገኝ፤ ምንም እንኳን ንጉሥ ኃይለ ስላሴ በጦርነቱ ምክንያት አገር ለቀው ቢሄዱም፣ ህዝቡ በአርበኝነት እየተዋጋ፤ አገሪቱ በ1941 እንደገና ነጻነቷን አስመልሳለች፤  ከዝያም ነዉ ቀደም ሲል አቢሲኒያ ተብላ ወደምትጠራዉ ወደ አሁንዋ ኢትዮጵያ ለሄድ የወሰኑት ሲሉ ተርከዋል። የቀዳማዊ ምኒልክ ሃገር ኢትዮጵያ የአፍሪካ፤ ነጻነት እና ብሔራዊ ስሜት የተወለደባት፤ በዉስጤ ሁልጊዜ ልዩ ስፍራ ያላት አፍሪካዊነት የዘር ሃረግ ግንዴ የተተከለባት አገር ትመስለኛለች፤ ሲሉ መናገራቸዉ በታሪክ ማኅደር ሰፍሮአል። የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ኔልሴን ማንዴላ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸዉ ትስስር በጎርጎረሳዉያኑ 1960 ዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዉ ወታደራዊ ስልጠና ማድረጋቸዉ ነዉ።  

ከአክራ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ባደረኩበት ወቅት ስሜታዊ ያደረገኝ ጉዳይ ተፈጠረ ይላሉ ኔልሰን ማንዴላ “Long Walk To Freedom” በተሰኘዉ መጽሐፋቸዉ። ከአክራ ወደ ካርቱም መጥተን፤ ከካርቱም ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ገባን። ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ አዉሮፕላን ስንገባ፤ ፓይለቱ ጥቁር መሆኑን አይቼ ደነገጥኩ። በህይወቴ ሙሉ ጥቁር ሰው አውሮፕላን ሲነዳ አይቼ ስለማላውቅ ተሸበርኩ። ጥቁር ሰው እንዴት አውሮፕላን ሊነዳ ይችላል? እያልኩ ደጋግሜ ራሴን ጠየኩ። በኋላ ግን ሲገባኝ፤ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርአት አስተሳሰባችንን ጭምር ቀይሮታል። ሳናውቀው አፍሪካዊ ዝቅ ያለ እና አውሮፕላን ማብረር የሚችለው ነጭ ብቻ ነው የሚል ስሜት እንዲያድርብን ሆኗል ለካ። አውሮፕላኑ በሰማይ ላይ ማንዣበብ ሲጀምር ጭንቀቴን ትቼ ስለኢትዮጵያ መልክዐ-ምድር ማንበብ ጀመርኩ። መንገዳችን ላይ የማስብ የነበረው ኢትዮጵያውያኑ በነዚህ ተራሮች እና ጫካዎች ውስጥ ተደብቀው እንዴት ከጣልያን ጋር የደፈጣ ውጊያ ያደርጉ እንደነበር ነው ብለዋል ማዲባ።

ጥቂት አስፋልት መንገድ ያላት አዲስ አበባ፤ ከመኪኖች ይልቅ በግ እና ፍየል በየመንገዱ ሞልተው ይታያሉ። ቤተ-መንግስቱ፣ እኛ ያረፍንበት ራስ ሆቴል፣ እንዲሁም ሌሎች ህንጻዎቿ ከጆሃንስበርግ የህንጻ ጋር ሲተያይ ብዙም አይማርክም። በዲሞክራሲም ቢሆን ኢትዮጵያ በምሳሌ ተርታ የምትሰለፍ አገር አይደለችም። ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሉም በንጉሱ ብቻ የምትመራ አገር ነች ሲሉ ይተርካሉ ማንዴላ በመቀጠል።

ከአፍሪክ ኮንፈረንስ መክፈቻ በፊት ወደ ትንሿ ከተማ፣ ደብረ ዘይት ሄደን ነበር። በከተማው አንድ አደባባይ አለ። እዚህ አደባባይ ላይ ከነበረው ድንጋይ ላይ እኔና ኦሊቨር ቁጭ ብለናል።  በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቁር ሰው የሚመሩ ጥቁር ወታደሮች ተመለከትኩ። የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ናቸው። ሁሉም ጥቁሮች ናቸው። አንድ ቀን አገሬ ውስጥ እንዲህ አይነት ነጻነት እንደምመለከት ተስፋ ከማድረግ ሌላ የምለው ነገር የለም ነበር አልነበረኝም ይላሉ ማንዴላ።

የኔልሰን ማንዴላን ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ያሰናዱት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ከተማ ይፍሩ ነበሩ። በወቅቱ በአፓርታይድ የዘረኝነት ቀንበር ስር የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ጥቁር ዜጎችዋ ያለፈቃድ አገሪቱን ለቀው እንዳይወጡ የሚያዝ ሕግ አውጥታ ነበር። ይህ ሕግ ለኔልሰን ማንዴላ ጉዞ አስቸጋሪ  ሁኔታን ፈጥሮ ነበር። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለኔልሰን ማንዴላ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት መሆናቸውን የሚገልፅ ፓስ ፖርት ካዘጋጁላቸው በኋላ ነበር፤ በጎርጎረሳዊዉ የካቲት ወር  1962 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ቻሉት።  ማንዴላ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፤ ወታደራዊ ስልጠና ለማድረግ ነበር ።

በወቅቱ ለኔልሰን ማንዴላ የተዘጋጀው ፓስፖርት ላይ ማንዴላ የጓደኛቸዉን ስም ይዘዉ ጋዜጠኛ እንደሆኑም ነበር የተነገረዉ። ማንዴላ የኢትዮጵያ አድማ በታኝ ፖሊስ በሚሰለጥንበት አዲስ አበባ ኮልፌ የሚባለው ሰፈር ስልጠናን ጀመሩ። ማንዴላ ስልጠና እስከጀመሩበት ጊዜ ጀማሪ ቦክሰኛ ከመሆን ውጭ ስለጦር ሜዳ ፍልሚያ የረባ እውቀት እንዳልነበራቸዉም በመጽሐፋቸዉ ጠቅሰዋል።  ወታደራዊ ስልጠናዉ ጥብቅም እንደነበር ማንዴላ አስታዉሰዋል።

መጀመሪያ ኮልፌ ከዚያም ከኮልፌ 50 ማይልስ የምትርቅ ቦታ ከወታደሮቹና ከንጉሱ የክብር ዘበኛ አባላት ጋር ሄጄ የኢላማ ተኩስ ተለማመድኩ። የሞርታር ተኩስና እንዲሁም የቦንንብ አሰራሮችን፤ ፈንጂዎችን የማክሸፍ ዘዴንም ተማርኩ። አሁን እያደር ወታደር እየሆንኩ ስሄድ ይታወቀኛል። እንደ ወታደር ማሰብ ለመድኩኝ። ወታደር መሆን እንደ ፖለቲከኛ ከማሰብ የሚለይበት የራሱ መንገድ አለው፤ ሲሉ መናገራቸዉ ን የታሪክ ማኅደራጠዉ ያሳያል።

ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት ለስድስት ወር ስልጠና ነው። ስምንት ሳምንት እንደሆነኝ ግን ከድርጅቴ ‘የአፍሪካ ኮንግረስ’ አንድ የቴሌ ግራም መልዕክት ደረሰኝ። በአስቸኳይ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንድመጣ የሚጠይቅ ነው። የዚያን ጊዜ የነፃነት ትግሉ መፋፋም ጀምሮ ነበር ሲሉ ማንዴላ በመጽሐፋቸዉ አስቀምጠዋል። እናም የግንባሩ አዘዥ እዚያው ቦታው ላይ መገኘት ስላለበት ነው የጠሩኝ። ኮሎኔል ታደሰ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካርቱም የምሄድበትን መንገድ ቶሎ አዘጋጁልኝ። ስንሰነባበት አንድ ሽጉጥና ሁለት መቶ ጥይት ስጦታ አበረከቱልኝ። ስለ ስልጠናውም ሆነ ሰጡኝ ትምህርት ትልቅ አክብሮት እንዳለኝ ገለጽኩና ጉዞዬን ጀመርኩ ሲሉ ማዲባ የህይወት ታሪካቸዉን ጽፈዋል።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ አስተያየቶንም ያስቀምጡልን!

አዜብ ታደሰ

ሸዋዩ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች