የነዳጅ ዘይት ዋጋ ንረትና የዓለም ኤኮኖሚ | ኤኮኖሚ | DW | 10.01.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የነዳጅ ዘይት ዋጋ ንረትና የዓለም ኤኮኖሚ

የነዳጅ ዘይት ዋጋ ባለፈው ሣምንት በበርሚል፤ ማለትም በ 159 ሊትር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አንድ መቶ ዶላር በማውጣት አዲስ ወሰን ላይ ደርሷል። የዋጋው መናር በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ አለው?

default

ዓለምአቀፉ አምራች ኩባንያዎች በያመቱ በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠር ትርፍ ቢያስገቡም በመስኩ እንደሚጠራው የዚህን ጥቁር ወርቅ ዋጋ እንዲንር ከማድረግ ወደ ኋላ አለማለታቸው ትችትን አስከትሎ የቆየ ጉዳይ ነው። ኩባንያዎቹ የነዳጅ ዘይት ፍጆት ከአቅርቦቱ መጠን ባለፈ ሁኔታ መጨመሩ ለዋጋው መናር ዋናው መንስዔ እንደሆነ ይናገራሉ። እርግጥ ነው ዛሬ ቻይናን የመሳሰሉት በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ አገሮች የኤነርጂ ጥም የፍጆቱን መጠን በሰፊው ለውጦታል። ታዲያ የምዕራባውያኑ የቅንጦት ኑሮና የቻይና ፍጆት መጨመር በተለይ ለታዳጊው ዓለም መዘዝ ነው የሆነው።

የአሜሪካ መዋዕለ-ነዋይ ባንክ ቀደምት የጥሬ ሐብት አዋቂ ጎልድማን ሣክስ በሚያዚያ 2005 ዓ.ም. ባቀረቡት ጥናት የበርሚል ነዳጅ ዘይት ዋጋ ሩቅ ባልሆነ ጊዜ መቶ ዶላር ይደርሳል ሲሉ አንዳንድ ታዛቢዎች ጉዳዩን እንደቀልድ ነበር የተመለከቱት። ያኔ የነዳጁ ዋጋ የዛሬው ግማሽ ነበር። አሁን ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ታዲያ የተነበዩት ዕውን ሆኗል። የነዳጅ ዘይት ዋጋ ባለፈው ሣምንት ረቡዕ ኒውዮርክ ውስጥ በበርሚል አንድ መቶ ዶላር ሲያስመዘግብ ከዚህ ወሰን ሲደርስ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነበር።

ለዋጋው መናር ምክንያቶችን ለመደርደር ብዙ ጊዜ አልወሰደም። በናይጄሪያ ዘይት ማውጫዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃትና ቀዝቃዛው የሰሜን አሜሪካ ክረምት፤ የምርቱ ክምችት ማቆልቆልና በእንዲህ ዓይነት ጊዜ የተለመደው ሃያ በመቶ የዋጋ ንረት በመንስዔነት ተጠቅሰዋል። በክረምት ወራት ነዳጅ ዘይት መወደዱ አዲስ ነገር ባይሆንም ይህ ብቻውን ግን ምክንያት መሆኑ ያጠያይቃል። እንደ አንዳንድ የመስኩ አዋቂዎች ስሌት ከሆነ የወደፊቱም ሂደት እፎይ የሚያሰኝ አይሆንም። እነዚሁ እንደሚሉት የነዳጅ ዘይት ዋጋ በሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት ወደ 150 ዶላር፤ በአሥር ዓመታት ደግሞ ወደ 200 ዶላር ማደጉ ነው። ማለት የዛሬውን ሁለት ዕጅ!

ይሁንና ግምቱን የተጋነነ አድርገው የሚመለከቱትም አይታጡም። አጠቃላይ ሃቅ ቢኖር መጠንና ፍጥነቱ በውል አይታወቅ እንጂ የመናሩን ሂደት ቀጣይነት የሚጠቁሙ ሁኔታዎች አለመታጣታቸው ነው። ባለፈው ዓመት ብቻ እንኳ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በእጥፍ ነበር የጨመረው። በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የምትገኘው የቻይና ፍጆት በሰፊው ማደግ ለዚሁ በየጊዜው እንደ ምክንያት ይጠቀሳል። በእርግጥም አንዱ መንስዔ መሆኑ ሰፊ ተቀባይነት አለው። ግን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታትስ ብልጽግና በምን ላይ ተመስርቶ የተገኘ ነው? ይህም እያደገ የመጣው ብልጽግና ለዋጋው መናር የራሱ ድርሻ ይኖረዋል። ለነዳጅ ዘይት በወቅቱ መጠን መናር የዓለም ኤኮኖሚ በተፋጠነ ሁኔታ መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

ሌሎች ምክንያቶችም ሊጠቀሱ የሚችሉ ሲሆን ከነዚሁም አንዱ ለምሳሌ የዶላር መዳከም ነው። የአሜሪካው ምንዛሪ መዳከም ነዳጅ ዘይት በዓለምአቀፍ ደረጃ በዶላር የሚገበይ በመሆኑ አውሮፓ ውስጥ የቤንዚን ዋጋ መናር ተጽዕኖን ለጊዜው ለዘብ ማድረጉ አልቀረም። ኤውሮ ከዶላር አንጻር እጅግ እያደገ መምጣቱ በዚህ ረገድ በጅቷል። በሌላ በኩል የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት በአጠቃላይ ሲታይ በነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ገና ብዙም ታውኳል ለማለት አይቻልም። ምክንያቱም በኤነርጂ ቁጠባና ፍቱን አጠቃቀም ረገድ ዕርምጃ መታየቱ ነው። ዛሬ ተመሳሳይ ለሆነ ዕድገት ከሰላሣ ዓመታት በፊት ይፈልግ ከነበረው ፍጆት ግማሹ እንደሚበቃ ነው የሚነገረው።

ይሁን እንጂ ይህ የወደፊቱ አዝማሚያ አሳሳቢ መሆኑን አይለውጠውም። ፍጆቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ በተፋጠነ ሁኔታ እያደገ መሄዱ እንደማይቀር ሁሉም የተገነዘበው ጉዳይ ነው። የሚያዳግት ነገር ቢኖር የመጨረሻዋ ጠብታ ተመጣ የምትወጣበትን ሰዓት በትክክል መናገሩ ይሆናል። ዓለምአቀፉ የኤነርጂ ኤጀንሲይ የአቅርቦቱን ቀውስ ለማየት አሥር ዓመት እንኳ አይፈጅም ሲል የነዳጅ ዘይት አምራቾቹ ሃገራት ማሕበር ኦፔክ ደግሞ የሃያ ዓመታት ጊዜ ነው የሚሰጠው። ከሆነ የሚደርሰውን ችግር ለማሰብ ብዙም አያዳግትም። እንግዲህ ነዳጅ ዘይት አንዴ ተሟጦ የሚያልቅ መሆኑ እርግጠኛ ነገር በመሆኑ ከረጅም ጊዜ አንጻር እንዴት ተተኪ እናግኝለት ብሎ ማሰቡ፤ በዚህ አቅጣጫም ጥረትን ማጠናከሩ ግድ ነው።

ዛሬም ቢሆን ዓለም ከሚፈጀው ጥቃሚ የኤነርጂ ምንጭ ሲሶው ነዳጅ ዘይት ነው። ጀርመንን የመሳሰሉ የበለጸጉ አገሮች ለምሳሌ መላውን ነዳጅ ዘይት ከውጭ ገዝተው ነው የሚያስገቡት። ይህ ደግሞ ከባድ ጥገኝነትን ይፈጥራል። ግን ታዲያ ከዚህ ወጥመድ ለመውጣት አማራጩ መንገድ ማተኮሪያ መሆኑ አልቀረም። የነዳጅ ዘይት ምንጭ እየደረቀ ሲሄድ በጸሃይ፣ በነፋስና በውሃ ኤነርጂ ቀዳዳውን ለመሸፈን ነው የሚታሰበው። ለጊዜው እነዚህ ምንጮች የሚፈለገውን ያህል ያልተስፋፉና ወድ ቢሆኑም የነዳጅ ዘይት ዋጋ እየናረ በቀጠለ ቁጥር የተሻሉት መገልገያዎች እንደሚሆኑ ነው የሚታመነው። ከዚሁ ተያይዞም እነዚሁ ታዳሽ የኤነርጂ ምንጮች እርግጥ በአካካቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ረገድም የወደፊቱ አማራጮች ናቸው።

በወቅቱ በጀርመን በተለይና በጥቅሉም በአውሮፓ እየጨመረ የሄደውን የነዳጅ ዘይት ጥገኝነት ለመቋቋም ወደ ሌላ ምንጮች የማሸጋሸግ አዝማሚያ ነው የሚታየው። ሆኖም ይህ የጀርመን የአካባቢ የተፈጥሮ ጥበቃና የኤነርጂ ጥናት ኢንስቲቲቱት ባልደረባ ፕሮፌሰር ፔተር ሄኒከ እንደሚሉት በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ የሚኖረው የነዳጅ ዋጋ መናር ወደፊትም ችግር መፍጠሩ የማይቀር ነው።

“በአብዛኛው በጀርመን፤ በአውሮፓም እንዲሁ የሚያሳዝን ሆኖ ነዳጅ ከውጭ የማስገባቱ ጥገኝነት እየጨመረ ነው። በዚሁ የተነሣ ከነዳጅ ዘይት ወደ ተፈጥሮ ጋዝ፣ ወደ ማዕድን ከሰልና በከፊልም ወደ አቶም ሃይል ማዘንበል ግድ መሆኑ አልቀረም። ታዲያ ይህን ሂደት በፍጥነት መግታት ያስፈልጋል። ትክክለኛ ከሆነ ግብ መድረስ የሚቻለው ከነዳጅ ዘይት ጥገኝነት በፍጥነት የመላቀቁ ጥረት ከአካባቢ አየር ጥበቃ ጋር ሲጣመር ብቻ ነው”

የነዳጅ ዘይትም ሆነ የሌላው ጥሬ ሃብት ዋጋ እየሰፋ በሄደው ፍጆት ሳቢያ በዓለም ገበያ ላይ መጨመሩ በታዳጊው ዓለም ለጥቂቶች መታደል ሲሆን ለብዙሃኑ ግን በችግር ላይ ችግር መሆኑ አልቀረም። በነዳጅ ዘይት ጸጋ የታደሉት ናይጄሪያን የመሳሰሉት አገሮች ሁኔታው በፈጠረው አመቺ አጋጣሚ ገቢያቸውን ለማጠናከር በቅተዋል። በሌላ በኩል በተፈጥሮ ሃብት እምብዛም ላልታደሉት በርካቶቹ አገሮች የነዳጅ ዘይቱ መወደድ ለዕድገታቸው ተጨማሪ መሰናክል ነው የሚሆንባቸው። አማራጭ ዘዴ ለመሻት አቅም ካላቸው በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉት ሃገራት ይበልጥም ተጎጂ መሆናቸው አያጠራጥርም።