መተማ፤ በመተማ ጋብ ብሎ የነበረው ተኩስ ማገርሸቱ
በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ጋብ ብሎ የነበረው ውጊያ ማገርሸቱን ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ተናገሩ። ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በተጠቀሰው መተማ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች በፋኖ ታጣቂዎችና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ውጊያ ሲካሄድ መሰንበቱ ነው የተገለጸው። በተለይ በመተማ ዮሐንስ ሰኞ ዕለት ጀምሮ ውጊያ የነበረ ሲሆን ትናንት ምንም እንኳ መደበኛ እንቅስቃሴዎች ባይኖሩም ጦርነቱ ጋብ ብሎ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች አመልክተዋል።
ዛሬ ሙሉ ቀን የተኩስ ድምፅ በከተማዋ አልነበረም የሚሉት እማኞች ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ በከተማዋ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተኩስ መጀመሩን አንድ የመተማ ዮሐንስ ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።
የተኩስ ልውውጡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ማምሻውን 12 ሰዓት ድረስ እንደቀጠለም ነው ነዋሪዎቹ ያመለከቱት። ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ደግሞ ሽንፋ የተባለችውን የመተማ ወረዳ ከተማ የፋኖ ኃይሎች እንደተቆጣጠሯት አንድ የከተማዋ ነዋሪ አረጋግጠዋል።
ጎንደር፤ 700 ያህል የሱዳን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው መመለስ
መንገድ ዳር ከነበሩ የሱዳን ስደተኞች 700 ያክሉ ወደ አገራቸው መመለሳቸው ተሰማ። በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ባለፈው ግንቦት ወር «መሠረታዊ ፍላጎታችን አልተሟላም፣ የፀጥታ ችግሮችም አሉብን» በሚል ይኖሩባቸው ከነበሩ ኩመርና አውላላ የስደተኛ መጠለያዎች ወጥተው 1,300 የሱዳን ስደተኞች በመንገድ ዳር ተሰባስበው ቆይተዋል። ከእነዚህ መካከል ገሚሱ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የተመ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) አስታወቋል።
ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግሥትን ጠቅሶ ለዶይቼ ቬሌ በላከው ደብዳቤ፤ ስደተኞቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት ፍላጎት እንዳልነበራቸው አመልክቷል። ቀሪዎቹም በሁለቱ ሃገራት አዋሳኝ ድንበር አካባቢ እንደሚኖሩ ገልጿል። አብዱሰመድ ናስር የተባሉ የሱዳን ስደተኛ ለዶቼ ቬለ ይህኑ በስልክ አረጋግጠዋል።
የመተማ የስደኞችና ተመላሾች አገልግሎት የፕሮግራሞች ኃላፊ አቶ ብስራት ደጉ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጠግተው የቆዩት የሱዳን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው የተመለሱት በፍላጎታቸው እንደሆነ ነው የገለጹት።
የሱዳን ስደተኞች ከሚያዝያ 2015 ዓ ም ጀምሮ ይኖሩባቸው ከነበሩት ኩመርና በአውላላ የስደተኞች መጠለያ በመሠረታዊ ፍላጎቶች እጥረትና የፀጥታ ችግሮ ምክንያት ቦታ እንዲቀየርላቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት እና የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በትብብር በመተማ ወረዳ «አፍጥጥ» ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አዲስ መጠለያ በመገንባት ወደዚያ እንዲዛወሩ መደረጉን ድርጅቶቹ አስታውቀዋል።
ቤጂንግ፤ የቻይና አፍሪቃ ጉባኤ
ቻይና በቀጣይ ሦስት ዓመታት ለአፍሪቃ ሃገራት ከ50 ቢሊየን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቷን አስታወቀች። ቤጂንግ በምታስተናግደው ትናንት በይፋ በተጀመረው የቻይና አፍሪቃ ጉባኤ ላይ የተገኙ የአፍሪቃ መሪዎች በመሠረተ ልማት፤ በግብርና፣ በማዕድን፤ በንግድ እና በኃይል ዘርፍ የበለጠ ትብብር ለማድረግ በርካታ ስምምነቶችን ከቻያን ጋር ተፈራርመዋል። ትናንት ማምሻውን 51 የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎችን እራት የጋበዙት ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ፤ የገንዘብ ድጋፉን ይፋ ባደረጉበት ንግግር በተለይ በመሠረተ ልማት እና በንግድ ዘርፍ የተጀመረውን ትብብር ለማጠናከርም ቃል ገብተዋል። ፕሬዝደንቷ ሺ ዢፒንግ የቻይና አፍሪቃን ትብብር ታሪካዊ ጊዜ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
«ከ2,8 ቢሊየን በላይ ቻይናውያን እና የአፍሪቃ ሕዝብ በተመሳሳይ አቅጣጫ ከልብ አብሮ እስከሠራ ድረስ በዘመናዊነት ጎዳና አዳዲስና ድንቅ ስኬቶችን እንፈጥራለን ብዬ አምናለሁ፤ ለደቡቡ ዓለምም የዘመናዊነት ጉዞን በማዳረስ ለግንባታው የላቀ አስተዋጽኦም ያደርጋል።»
ከዓለም ሁለተኛ የሆነው ትልቅ ኤኮኖሚ ባለቤት ቻይና የአፍሪቃ ሃገራት ዋነኛዋ የንግድ ተባባሪ ሀገር ናት። ግዙፍነቱ በተገለጸው በዚህ የቻይና አፍሪቃ ጉባኤ ላይ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽም ተገኝተዋል።
ሙኒክ፤ ፖሊስ አንድ ተጠርጣሪን ተኩሶ መግደሉ
በጀመርኗ ሙኒክ ከተማ በዛሬው ዕለት ፖሊስ አንድ ተጠርጣሪን ተኩሶ መግደሉ ተነገረ። የጦር መሣሪያ ይዞ እንደነበር የተገለጸው ግለሰብ በከተማዋ የእስራኤል ቆንስላ እና የናዚ ዘመን ታሪክ መታወሻ ቤተመዘክር አቅራቢያ በጠዋቱ መገኘቱ ነው የተገለጸው። ፖሊስ በX የማኅበራዊ መገናኛ ገጹ ተጠርጣሪው ግለሰብ በጥይት መመታቱን ከመግለጽ ያለፈ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም። ከጉዳዩ ጋር የተገናኘ ክስተትና ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን የሚያመለክት ማስረጃም እንዳላገኘ አስታውቋል። ድርጊቱ የተፈጸመው በሙኒክ መሀል ከተማ ካሮሊነን ፕላትዝ አካባቢ መሆኑን በመግለጽ ፖሊስ በአካባቢው ኃይሉን በርከት አድርጎ ማሰማራቱን ገልጿል።
አሶሲየትድ ፕረስ በላከው ዜና ዕለቱ የዛሬ 52 ዓመት በኦሎምፒክ ውድድር ወቅት 11 እስራኤላውያን ሙኒክ ላይ የተገደሉበት መታሰቢያ እንደሆነ አስታውሷል። ዛሬ ፖሊስ እርምጃ ከወሰደበት አጋጣሚ ጋር በተገናኘ በሙኒክ የእስራኤል ቆንስላ በጽሕፈት ቤቱ ማንም ስላልነበረ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ገልጿል። የእስራኤል ፕሬዝደንት የሙኒክ ፖሊስ የከፋ ነገር እንዳይከሰት አድርጓል በሚል አመስግነዋል። ዘግይተው የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱት ፖሊስ ድርጊቱን የሽብር ጥቃት ብሎታል።
ማናማ፤ በባህሪን ተሟጋቾችን ጨምሮ 457 እስረኞች በምሕረት መለቀቃቸው
የባህሪን ንጉሥ ሀሚድ ቢን ኢሳ አል ኻሊፋ 457 እስረኞችን በምህረት መፍታታቸውን አስታወቁ። ከአስከፊው የሀገሪቱ እስር ቤት ከተለቀቁት መካከል ከአስር ዓመት በላይ የቆዩ የመብት ተሟጋቾች ይገኙበታል። ንጉሥ ሀሚድ ለእስረኞቹ ምህረት ያደረጉት የ25ኛ ዓመት የንግሥና በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ መሆኑን የባህሪን መንግሥት የዜና አውታር ይፋ ማድረጉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ጠቅሷል። ከአምስት ወራት በፊትም 1,500 እስረኞች በምህረት መፈታታቸው ነው የተገለጸው። መቀመጫውን ብሪታንያ ያደረገው ለባህሪን መብትና ዴሞክራሲ ተቋም ዛሬ እንደገለጸው ከተፈቱት መካከል የፖለቲካ እስረኞችም ይገኙበታል።
ናይሮቢ፤ ጥቃት የተፈጸመባት ዩጋንዳዊት አትሌት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷ
ዩጋንዳዊቱ የረዥም ርቀት ሯጭ አትሌት ሬቤካ ቼፕቴጊ ሕይወቷ አለፈ። የቀድሞ ፍቅረኛዋ ባሳለፍነው ሰኞ ዕለት ባደረሰባት የቃጠሎ ጥቃት ተጎድታ አካሏ 80 በመቶ ተቃጥሎ በምትኖርበት ኬንያ ሆስፒታል ገብታ ነበር። የታከመችበት ሆስፒታል ቃል አቀባይ ለጋዜጠኞች እንዳረጋገጡት በደረሰባት ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት ዛሬ ማለዳ አርፋለች። በቃጠሎው የአካሉ 30 በመቶ ተጎድቷል የተባለው ጥቃት አድራሽ ግን አሁን በተረጋጋ ሁኔታ እንደሚገኝም ተገልጿል። ጥቃት ካደረሰባት የቀድሞ ፍቅረኛዋ ጋር ለቤተሰቦቿ በገዛችው መሬት ምክንያት ተጋጭተው መጨቃጨቃቸው ነው የተገለጸው። የ33 ዓመቷ ቼፕቴጊ ከመሞቷ አንድ ወር በፊት በፓሪስ ኦሎምፒክ ተሳትፋ 44ኛ ወጥታ ነበር። ልጃቸው ትደግፋቸው እንደነበር የተናገሩት አባቷ፤ ፍትህ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። የዩጋንዳ አትሌቲክስ ኮሚቴ የደረሰውን ጥቃት የፈሪ ዱላ በማለት አውግዞ፤ ድርጊቱ ሀገሪቱን ታላቅ አትሌት እዳሳጣት አመልክቷል።
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ