1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዳር 5 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 5 2015

ካታር የምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ የፊታችን እሁድ በኧል ባይት ስታዲዬም ውስጥ ሊከናወን ሽር ጉዱ ተጧጡፏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድን አሌህሳንድሮ ጌርናቾ በባከነ ሰአት ከጉድ ታድጓል። አርሰናል በመሪነቱ ሲገሰግስ ማንቸስተር ሲቲ ሽንፈት ገጥሞታል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው።

https://p.dw.com/p/4JVeX
Fifa World Cup Qatar
ምስል KIRILL KUDRYAVTSEV/AFP/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ካታር የምታዘጋጀው የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታው የፊታችን እሁድ በኧል ባይት ስታዲዬም ውስጥ ሊከናወን ሽር ጉዱ ተጧጡፏል። የተለያዩ ሃገራት የእግር ኳስ ቡድኖች እና ታዋቂ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ወደ ዶሀ ኳታር መግባታቸውም ተዘግቧል። የዛሬው የስፖርት ጥንቅራችን ዋነኛ ትኩረት ይኸው የኳታር የዓለም ዋንጫ መሰናዶ ነው። ዶሐ ኳታር ውስጥ በፊፋ የበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ የተሰማራ ኢትዮጵያዊንም አነጋግረናል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የትናንት ግጥሚያ ማንቸስተር ዩናይትድን አሌህሳንድሮ ጌርናቾ በባከነ ሰአት ከጉድ ታድጓል። አርሰናል በመሪነቱ ሲገሰግስ ማንቸስተር ሲቲ ሽንፈት ገጥሞታል። ሊቨርፑል ወሳኝ የሆነውን ድሉን ባለፈው ሳምንትም ደግሟል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን የመሪነቱን ሥፍራ እንዳስጠበቀ ነው።

የዓለም ዋንጫ መዳረሻ

WM Qatar 2022 l Logo in Doha
የኳታር ዓለም ዋንጫ መለያ ምስል እና ጽሑፍምስል Keita Iijima/the Yomiuri Shimbun/AP/picture alliance

በየአራት ዓመቱ የሚካኼደው የዓለም ዋንጫ ዘንድሮ ኳታር ውስጥ ሊጀመር ቀናት ብቻ ቀርተውታል። ውድድሩ የፊታችን እሁድ በአዘጋጇ ኳታር እና ኤኳዶር የመክፈቻ ግጥሚያ ይጀምራል። የጀርመን ቡድን ረቡዕ እለት ከዖማን ጋር በሚያደርገው የወዳጅነት ጨዋታ ይንደረደር እና በዓለም ዋንጫው በምድብ «ሠ» ከጃፓን ጋር ይጋጠማል። ኳታር ዶሐ ውስጥ የፊፋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጠው ኢትዮጵያዊው ዓሚኑ ኑሩ የመክፈቻ ጨዋታውን ጨምሮ ሰባት ግጥሚያዎች ላይ እንደሚሳተፍ ለዶይቸ ቬለ ተናግሯል። ሌሎች ኢትዮጵያውያንም በዓለም ዋንቻ ጨዋታዎች ላይ በመገኘት የበጎ ፈቃድ ለመስጠት ዝግጅት እና ስልጠናቸውን አጠናቀው ተዘጋጅተዋል።

ዓሚኑ ኑሩ በፊፋ የበጎ ፈቃደኝነት ተሳታፊ የሚሆንበት የመክፈቻው ጨዋታ የፊታችን እሁድ በአዘጋጇ ኳታር እና ኤኳዶር ግጥሚያ ይጀመራል። ዘንድሮ ዓለም አቀፉን የእግር ኳስ ግጥሚያ ለማሰናዳት ዕድሉን ያገኘችው ኳታር በርካታ ተግዳሮቶች ከፊቷ መጋረጡ እየተዘገበ ነው።

የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የሚካኼድባቸው ስታዲዬሞች ግንባታ ላይ ከ15,000 በላይ ሠራተኞች ሕይወታቸውን ማጣታቸው የፈጠረው ቅሬታ በዋናነት ይጠቀሳል። በግንባታ ወቅት ስለሞቱት ሠራተኞች ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል በ2021 ዘገባው ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ የከባቢ አየር ብክለት፤ የኮቪድ 19 ያስከተለው የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት ወደ ኳታር የሚሄዱ ደጋፊዎችን ቁጥር እንዳይቀንስሰውም አስግቷል። የኳታር የዓለም ዋንጫ አዘጋጆች ግን ከካርቦን ነጻ የሆነ ድባብ በመፍጠር የመጀመሪያው የውድድር መድረክን ለመፍጠር ዝግጅታችን ጨርሰናል ማለታቸውን አንዳንዶች «አሳሳች» መረጃ ሲሉ ነቅፈውታል። በዚህም አለ በዚያ ኳታር ዝግጅቴን አጠናቅቄ በደመቀ ሁኔታ የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያዎችን ላስጀመር ተሰናድቻለሁ ብላለች። ያለፈው የዓለም ዋንጫ የተካኼደው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 (ሩሲያ እና የዓለም ዋንጫ ዝግጅት)ሩስያ ውስጥ ነበር።

Fifa World Cup Qatar
የኳታር እግር ኳስ የፊፋ 2022 ምልክት ጋር ሰዎች ፎቶግራፍ ሲነሱምስል JEWEL SAMAD/AFP/Getty Images

እግር ኳስ

ፕሬሚየር ሊግ

የ18 ዓመቱ አዳጊ ወጣት አሌሃንድሮ ጋርናቾ አንድ እኩል ነጥብ ሊጋራ የነበረው ቡድኑ ማንቸስተር ዩናይትድን በ93ኛው የባከነ ደቂቃ ላይ በአስደናቂ ፍጥነት እና ጥበብ በመታከል ከጉድ ታድጓል። ኳስ ወደ ፉልሀም የግብ ክልል እየገፋ የመጣው አሌሃንድሮ ኳሷን አቀብሎ በተከላካዮች መሀከል ወደ ግብ ጠባቂው በፍጥነት ሲገሰግስ ተከላካዮቹ ያልጠበቁት ክስተት ስለነበር ሊቆጣጠሩት አልቻሉም። በዕለቱ ብቸኛ የፊት አጥቂው ማርቺያል ተቀይሮ የገባው አዳጊ ወጣት በጨረፍታም በፉልሀም ግብ ጠባቂ በስተግራ በኩል የላካት ኳስ ከመረብ አርፋ ማንቸስተር ዩናይትድን ለድል አብቅታለች።

የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ በደስታ ሲዋጡ፦ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለአሰልጣኙ «ክብር የለኝም» ብሏል። በተደጋጋሚ አግዳሚ ወንበር ላይ ለመቀመጥ የተገደደው የ37 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ አጥቂ ምክንያቱን ሲጠየቅም፦ «አሰልጣኙ ለእኔ ክብር ስለሌላቸው እኔም የለኝም» ሲል ተደምጧል። «የመከዳት ስሜትም ውስጤ ሠርጿል» ሲል በማንቸስተር የመጨረሻ ዘመን ቆይታው ደስተኛ አለመሆኑን ዐሳውቋል። ማንቸስተር ዩናይትድ ግን ያለ ክርስቲያኖ ሮናልዶም ለወሳኝ ድል በቅቷል።

Großbritannien | Cristiano Ronaldo
የማንቸስተር ዩናይትድ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሜዳ ውስጥ ነጭ መለያ ለብሶምስል Rui Vieira/AP/picture alliance

በዚህ ግጥሚያ ማንቸስተር ዩናይትድ ቀዳሚዋን ግብ በክርስቲያን ኤሪክሰን እንዲያስቆጥር ኳስ ያመቻቸው አማካዩ ብሩኖ ፌርናንዴሽ በፉልሀም አቻ ግብ ሲቆጠርባቸውም ስህተት ፈጥሯል። ከመስመር ልትወጣ የነበረችውን ኳስ ሲመልስ ባለመቆጣጠሩ ፈጣኑ ዊሊያምስ ወደፊት ገፍቶ ለግብ በማመቻቸት ዳንኤል ጀምስ ከመረብ አሳርፏታል።  የትናንቱ ድል ማንቸስተር ዩናይትድ በ26 ነጥብ 5ኛ ደረጃውን እንዲያስጠብቅ አስችሎታል። ቅዳሜ ዕለት ሳውዝሐምፕተንን 3 ለ1 ያሸነፈው ሊቨርፑል በ4 ነጥብ ልዩነት 6ኛ ደረጃ ላይ ይከተለዋል። አሌሃንድሮ ጋርናቾ ማንቸስተር ዩናይትድን ባለቀ ሰአት ባይታደግ ኖሮ ከሊቨርፑል ጋር የነጥብ ልዩነቱ 2 ብቻ ይሆን ነበር።

በሌሎች ግጥሚያዎች 32 ነጥብ ይዞ በፕሬሚየር ሊጉ የሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት በሜዳው ተጫውቶ በብሬንትፎርድ የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል። መሪው አርሰናል በዎልቭስ ሜዳ ተጫውቶ የ2 ለ0 ድል ተቀዳጅቷል። ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነትም ወደ 5 ከፍ ማድረግ ችሏል። በ29 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሀም ቅዳሜ ዕለት 15ኛ ግጥሚያውን ከሊድስ ጋር አድርጎ 4 ለ3 ማሸነፍ ችሏል። በ30 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኒውካስልም 15ኛ ግጥሚያውን ቅዳሜ ዕለት ቸልሲን 1 ለ0 በማሸነፍ በድል አጠናቋል። አርሰናል፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል እስካሁን ያከናወኑት 14 ጨዋታዎችን ነው። ዌስትሀም በላይስተር 2 ለ0 ሲሸነፍ፤ በርመስ ኤቨርተንንን 3 ለ0 ድል አድርጓል። 18ኛ ደረጃ ወራጅ ቃጣና ውስጥ የሚገኘው ኖቲንግሀም ፎረስት ክሪስታል ፓላስን 1 ለ0 አሸንፏል። ብራይተን ትናንት በአስቶን ቪላ የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል።

ቡንደስሊጋ

Bundesliga - SC Freiburg v 1. FC Union Berlin
በቡንደስሊጋው የፍራይቡርግ ተጨዋቾች ዑኒዬን ቤርሊን ላይ ጎል አስቆጥረው ሜዳ ውስጥ ተሰባስበውምስል Thomas Kienzle/AFP/Getty Images

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ የ4 ለ2 ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል። 25 ነጥብ ይዞም ደረጃው 6ኛ ነው። እስካለፉት ሦስት ሳምንታት ድረስ ቡንደስሊጋውን ሲመራ የቆየው ዑኒዮን ቤርሊን ትናንት በፍራይቡርግ ሜዳ የ4 ለ1 ሰፊ ሽንፈት ገጥሞታል። ፍራይቡርግ በ30 ነጥብ የሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በ34 ነጥብ የሚመራው ባየርን ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት ወደ ሻልከ ሜዳ አቅንቶ 2 ለ0 አሸንፏል። 28 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲሽ ቬርደር ብሬመንን በሜዳው 2 ለ1 አሸንፏል። ከማይንትስ ጋር አንድ እኩል የተለያየው አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ27 ነጥብ የ4ኛ ደረጃን ይዟል።  ሽቱትጋርት፤ ቦሁም እና ሻልከ ወራጅ ቃጣናው ውስጥ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ደረጃ ላይ ተደርድረዋል። 16ኛ ዙር የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች የዓለም ዋንጫ ከተገባደደ በኋላ ጥር ወር ውስጥ ይጀምራሉ። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎችም የታኅሣስ ወር አጋማሽ ላይ ዳግም ይጀምራሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

በጋምቤላ ክልል የባሮ ወንዝ ሙሌት፤ ኢትዮጵያ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW
ዋናዉን ገፅ ተመልከት